የካታሩ ቱጃር ማንቸስተር ዩናይትድን ጠቅልሎ ለመግዛት የተሻሻለ ገንዘብ አቀረቡ

ማንቸስተር ዩናይትድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሼኽ ጃሲም ቢን ሃማድ አል ታኒ የእንግሊዙን ክለብ ማንቸስተር ዩናይትድ ለመግዛት የተሻሻለ ገንዘብ አቅርበዋል።

ምንጮች ለቢቢሲ ስፖርት እንደገለጡት የካታሩ ቱጃር ማክሰኞ ዕለት ሬይን ግሩፕ ለተሰኘው ድርጅት አዲስ ጨረታ አቅርበዋል።

የኦልድ ትራፈርዱን ክለብ ለመግዛት የካታሩ ባንከር እና ኢኔዎስ ግሩፕ የተሰኘው ድርጅት ባለቤት የሆኑት ጌታ ጂም ራትክሊፍ እየተፎካከሩ ይገኛሉ።

ሁለቱም ባለሃብቶች ባለፈው የፈረንጆቹ ወር መጨረሻ ለሦስተኛ ጊዜ የጨረታ ዋጋቸውን አሻሽለው ቀርበዋል።

የካታሩ ቱጃር ዩናይትድ የሚገዙት ከሆነ መቶ በመቶ ባለቤት የሚሆኑ ሲሆን ክለቡ ያለበትን ዕዳ ከፍለው አዲስ ፈንድ በማቋቋም ክለቡንና የአካባቢውን ማኅበረሰብ ማገዝ ይችላሉ።

ባለፈው መጋቢት የወጡ ቁጥሮች እንደሚያሳዩት ማንቸስተር ዩናይትድ 969.9 ሚሊዮን ፓውንድ ውዝፍ ዕዳ አለበት።

የባንክ ዕዳ፣ የተጨዋቾች ዝውውር ተያያዥ ክፍያዎች የክለቡ ዕዳ ምንጭ ናቸው።

የወቅቱ የማንቸስተር ዩናይትድ ባለቤት የሆኑት የግሌዘር ቤተሰብ ባለፈው ኅዳር ነው ማንቸስተር ዩናይትድን ለመሸጥ ሐሳብ እንዳላቸው ይፋ አድርገው ጨረታ የከፈቱት።

ምንም እንኳን የግሌዘር ቤተሰብ እስካሁን ስለጨረታው ያሉት ነገር ባይኖርም ጌታ ጂም ራትክሊፍ ቡድኑን ሊገዙት እንደሚችሉ እምነት አለ።

ራትክሊፍ መጀመሪያ መግዛት ይፈልጉ የነበረው 69 በመቶ ድርሻ ሲሆን አሁን ግን ዝቅ አድርገው ከ50 በመቶ ትንሽ ከፍ ያለ ድርሻ ለመግዛት እንደወሰኑ ተሰምቷል።

ይህ ማለት ጆዌልና አቭራም ግለዜር ያላቸውን ድርሻ ሙሉ በሙሉ ሳይሸጡ መቆየት ይችላሉ።

አቭራም ግለዜር ባለፈው ሰንበት በሴቶች የኤፍ ኤ ዋንጫ ፍፃሜ ማንቸስተር ዩናይትድ በቼልሲ ስትሸነፍ ዌምብሊ ስታድየም ተገኝተው ታድመዋል።

አልፎም ለንደን ውስጥ የሼኽ ጃሲም አባት ንብረት የሆነ ሆቴልንም ሲጎበኙ ታይተዋል። ጉብኝት ያደረጉት ሼኹን ለማነጋገር ነው ቢባልም ቢቢሲ ስፖርት የተጨበጠ መረጃ አላገኘም።

የግሌዘር ቤተሰብ በማንቸስተር ዩናይትድ ጉዳይ የመጨረሻውን ውሳኔ መች እንደሚያስተላልፉ ግልጥ አይደለም።

ቤተሰቡ ማንቸስተር ዩናይትድን በፈረንጆቹ 2005 በ790 ሚሊዮን ፓውንድ ሲሆን የገዛው አሁን ክለቡ እስከ 6 ቢሊዮን ፓውንድ ይገመታል።

በርካታ የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች “የግሌዘር ቤተሰብ ይውጣልን” የሚል መፈክር ይዘው ጨዋታ ሲታደሙ ይስተዋላል።

የአውሮፓ ተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ከአንድ ወር በኋላ ይከፈታል። ይህን ተከትሎ በዚህ ሳምንት የማንቸስተር ዩናይትድ ዕጣ ፈንታ እውን ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለ።

ይህ ከሆነ አሠልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ለአዳዲስ ተጫዋቾች ማውጣት የሚችሉትን ገንዘብ ማወቅ ይችላሉ።

ነገር ግን ይህ በእርግጠኝነት ይሆናል ብሎ መናገር ከባድ ነው።