ሊቃጠል ወራት የቀሩት ከ2000 በላይ የዲቪ ሎተሪ ባለዕድል ኢትዮጵያውያን ጉዳይ

የአሜሪካ ግሪን ካርድ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, HTTPS://HR.USEMBASSY.GOV/

የአውሮፓውያኑ 2023 የዲቪ ሎተሪ ደርሷቸው ወደ አሜሪካ የሚያደርጉት የጉዞ ሂደት የዘገየባቸው ኢትዮጵያውያን ዕድለኞች ስጋት ላይ መሆናቸውን ለቢቢሲ ገለፁ።

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር 2700 ኢትዮጵያውያን የ2023 የዲቪ ሎተሪ ዕድለኞች ሆነው መመረጣቸው ተነግሯቸው ነበር።

የዚሁ የዲቪ ሎተሪ ዕድለኞች የሆኑ ሰዎችም በአዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በኩል የተለያዩ መስፈርቶችን ካሟሉ በኋላ ቪዛ በማግኘት ወደ አሜሪካ ያቀናሉ።

ይህንን የዲቪ ሎተሪ ማሸነፋቸው ከተነገራቸው ከአንድ ዓመት በኋላም ከ2000 የሚበልጡ ኢትዮጵያውን ዕድለኞች በቀረው አጭር ጊዜ “ኤምባሲው ሂደቱን ጨርሶልን ወደ አሜሪካ የምንጓዝ አይመስለንም” በማለት ስጋት ውስጥ መግባታቸውን ተናግረዋል።

የአዳማ ከተማ ነዋሪ የሆነው አያና ከበደ የ2023 ዲቪ ሎተሪ ዕድለኛ ከሆኑት ወስጥ አንዱ ሲሆን፣ የዚህን ዓመት የዲቪ አሸናፊዎች ኮሚቴ አባል ነው።

አያና እንደሚለው ከሆነ የዲቪ ሎተሪ ዕድለኛ መሆኑን ካወቀ አንድ ዓመት የሞላው ቢሆንም “አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የሚያስፈልገውን መስፈርት በጊዜ አንድንሟላ ስላላደረገን ስጋት ውስጥ ገብተናል” ይላል።

የጂንካ ከተማ ነዋሪ የሆነው ሌላኛው የ2023 ዲቪ ሎተሪ ዕድለኛ አቶ ሙሉቀን ጣሰው በበኩሉ ያገኘነው ዕድል ወደ መቃጠል እየተቃረበ ስለሆነ “ምናለበት ባይደርሰኝ ኖሮ” በማለት ማሰብ መጀመሩን ይናገራል።

አያና በበኩሉ “በ2023 አሜሪካ የዲቪ ሎተሪ ዕድልን ለ2761 ኢትዮጵያውያን ሰጥታ ነበር። ከእነዚያ መካከል አንዱ እኔ ነኝ። በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ግን እስካሁን ድረስ ሂደቱን ሊያስጀምረን አልቻለም” ይላል።

በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ለቢቢሲ በኢሜል እንደገለጸው ከሆነ “የዲቪ ሎተሪ የደረሳቸው በሙሉ ቪዛ ያገኛሉ አልያም ቪዛ ለማግኘት ይችላሉ ማለት አይደለም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አያና እንደሚለው ያገኘው የዲቪ ሎተሪ ዕድል ከመስከረም 30/2023 በኋላ የሚቃጠል በመሆኑ በቀሩት አጭር ወራት የቪዛ ማመልከቻ ጥያቄያቸው የሚታይበት ዕድል እየጠበበ መሆኑን በመግለጽ ስጋት ውስጥ እንደገቡ አመልክቷል።

ከእነሱ ቀደም ብለው ባሉት ዓመታት ውስጥ የዲቪ ሎተሪ ደርሷቸው የነበሩ ባለዕድሎች የቪዛ ጥያቄያቸው በኤምባሲው "በጊዜ ስላልተስተናገደ ብዙዎቹ ጊዜው አልፎ ዕድላቸው ተቃጥሏል። የእኛም ወደዚያው እየሄደ ነው” ብሏል።

የዚህ ዓመት የዲቪ ሎተሪ ባለዕድል ከሆኑት መካከል እስካሁን ኤምባሲው ለ123 ሰዎች ሂደቱን ጨርሶ ቪዛ እንደሰጠ፣ የ130 ሰዎች የቪዛ ጥያቄያቸው እየታየ መሆኑን እንዲሁም ሌሎች 130 ባለዕድሎች ደግሞ ሂደቱን መጀመራቸውን አያና ገልጿል።

“. . .ስለዚህ ከ2761 ዕድለኞች ውስጥ ለ383 ሰዎች ብቻ ነው ሂደቱ የተጀመረላቸው ወይንም ያለቀላቸው። ኤምባሲው በወር ውስጥ እያስተናገደ ባለው የሰው ቁጥር መሰረት 2200 የሚሆኑት ሰዎች ዕድላቸው ወደ መቃጠል እየሄደ ነው” ይላል አያና።

አቶ ሙሉቀን ጣሰው በበኩሉ የዲቪ ሎተሪ ዕድለኛ መሆኑን ባወቀ ጊዜ እርሱም ሆነ ቤተሰቦቹ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷቸው እነደነበር ያስታውሳል።

የባንክ ማናጀር የነበረው ሙሉቀን የዲቪ እንደደረሰው ካወቀ በኋላ “ወደ አሜሪካ በቅርቡ እሄዳለሁ በሚል ተስፋ ሥራዬን ለቅቄ በግል ሥራ ላይ አትኩሬ ነበር” በማለት አሁን ግን ይህ ዕድል ወደ ሊቃጠል ይችላል በሚል ስጋት ውስጥ መሆኑን ተናግሯል።

“አሁን አሁን ሳስበው ምናለበት የዲቪው ሎተሪው ባይወጣልኝ ብዬ እያሰብኩ ነው። ቤተሰቦቼ እና ጓደኞቼ መቼ ነው የምትሄደው እያሉ ይጠይቁኛል። ይህ ዕድሌ ከተቃጠለ እዚህ ከተማ ውስጥ መኖር አልችልም” ይላል ሙሉቀን።

በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ፣ ላለፉት ሦስት ዓመታት በኮቪድ እና በሌሎች ችግሮች ምክንያት በርካታ ውዝፍ ሥራዎች ስለነበሩበት በሚፈለገው ሁኔታ የዲቪ ሎተሪ ዕድለኞችን ለማስተናገድ እንዳልቻለ ገልጿል።

ለዲቪ ዕድለኞች የቪዛ መስጠት ሂደት “በአጭር ጊዜ ውስጥ በአስቸኳይ የሚከናወን ሥራ ስላልሆነ” በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ሁሉንም የዲቪ ዕድል አሸናፊዎች ማስተናገድ እንደማይቻልም ገልጿል።

በዲቪ ሎተሪ አማካይነት ለተለያዩ አገራት ዜጎች በተለያየ መጠን በሚደለደል የዕጣ ዕድል መሠረት በየዓመቱ 50 ሺህ ቪዛዎች ይሰጣሉ።

የዲቪ ሎተሪ ዕድለኞች ምርጫ ሂደት በኮምፒውተር የሚከናወን ሲሆን ቪዛ ተቀባዮች አሜሪካ ውስጥ ስፖንሰር፣ ሥራ ወይም ደግሞ ቤተሰብ እንዲኖራቸው አይጠበቅባቸውም።