“ዋንጫውን አሳልፈን ከሰጠን በኋላ ከሕመማችን ማገገም አለብን” ሚኬል አርቴታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአርሰናሉ አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ ምንም እንኳ “አስገራሚ የውድድር ዘመን ብናሳልፍም ቁስላችን መሻር አለበት” ብሏል።
የፕሪሚዬር ሊጉን ዋንጫ ለማንቸስተር ሲቲ ‘አሳልፈው የሰጡት’ አርሰናሎች ከዚህ ሕመም ማገገም እንዳለባቸውም አሠልጣኛቸው ተናግሯል።
አርሰናል ቅዳሜ ዕለት ከኖቲንግሃምር ፎረስት ገጥሞ በመረታቱ ማንቸስተር ሲቲ ቀጣይ ጨዋታውን ሳያደርግ የዋንጫ ባለቤት መሆኑን አረጋግጧል።
በዚህ የውድድር ዘመን በድል እየተንበሸበሹ የጀመሩት አርሰናሎች በአንድ ወቅት ከማንቸስተር ሲቲ በስምንት ነጥብ ርቀው ተቀምጠው ነበር።
ነገር ግን ካለፉት ስምንት ጨዋታዎች ሁለቱን ብቻ በማሸነፍ የዋንጫውን እጀታ ለሲቲ አስከርበዋል።
“አሁን ስለእሱ ማሰብ አልችልም። ለማንቸስተር ሲቲ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት ብቻ ነው የምችለው” ብሏል ሚኬል አርቴታ።
“ባለፉት 10 ወራት ከሲቲ ጋር መተናነቃችን የሚገርም ጉዞ እንደነበረን ማሳያ ነው። ብዙ ተምረናል። ብዙ ለውጥ አምጥተናል። ነገር ግን ድካማችን ፍሬ የሚኖረው ዋንጫ ብናገኝ ነበር፤ እሱ አልሆነም።”
አርሰናል፤ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ታሪክ ከውድድር ዘመኑ 248 ቀናትን ሊጉን እየመራ ዋንጫ ያላነሳ የመጀመሪያው ክለብ ሆኗል።
አርቴታ አሁን ቡድናቸውን አዋቅረው ሞራላቸውን በመመለስ ለመጨረሻው የሊጉ ጨዋታ እያዘጋጁ ይገኛሉ።
“ይህ እግር ኳስ ነው። በጣም አሳዛኝ ቀን ነው ለእኛ። ለ11 ወራት ዓላማ ይዘን ስንሠራ ነበር። በሊጉ አናት ላይ ለበርካታ ወራት ከርመናል። አጠናቀናል ግን የሠራነው በቂ አይደለም” ሲሉ ለስካይ ስፖርት ቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።
“አሁን ማገገም አለብን። በጣም ከባድ ነው። ተጫዋቾቼን ለማነሳሳት እሞክራለሁ። ከባድ ሳምንት ነው የሚጠብቀን።”
ምንም እንኳ ማንቸስተር ሲቲ ያለፉት 11 የሊግ ጨዋታዎችን ቢያሸንፍም “ጥፋቱ የራሳችን ነው” ይላል የአርሰናሉ ግብ ጠባቂ አሮን ራምስዴል።
“ካለፉት ስድስት የውድድር ዘመኖች አንድ ቡድን ብቻ ነው ሲቲን በልጦ የተገኘው። ወጣም ወረደ ጥፋቱ የራሳችን ነው። ማሸነፍ የሚገባንን ፍልሚያ በግለሰብ ጥፋት ሳናሸንፍ ቀርተናል።”

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“ሲቲ ደም ሸተተው ማለት ጨዋታው አልቋል ማለት ነው”
ባለፈው የውድድር ዘመን አምስተኛ ሆነው ያጠናቀቁት አርሰናሎች ዘንድሮ ለዋንጫ መፎካከራቸው ብዙዎች ያልጠበቁት ነው።
ነገር ግን የሊጉ መሪ ሆነው የከረሙት የሚኬል አርቴታ ልጆች በመገባደጃው ምን ገጠማቸው?
“ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ሁኔታዎች እንደከበዷቸው መናገር ይቻላል። ጉዳዩ የአእምሮ ጥንካሬ ይመስለኛል” ይላል የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ ተጫዋች ጋሪ ኔቪል።
“ሁሌም ይህ የአርሰናል ቡድን ጫና ሲበረታበት መቋቋም የሚችል ነው የሚል እምነት አልነበረኝም።”
የቀድሞው የስኮትላንድ አማካይ የነበረው ቻርሊ አዳምስ ደግሞ አርሰናል ባለቀ ሰዓት ዋንጫውን አሳልፎ መስጠቱ የሚያሳዝን መሆኑን ይናገራል።
ምንም እንኳን አርሰናል ዋንጫው አሳልፎ እንደሰጠ ባይካድም ተቀናቃኛቸው ደግሞ ማንቸስተር ሲቲ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።
የሊቨርፑሉ ተከላካይ ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ በ2018/19 የውድድር ዘመን በተመሳሳይ ከቡድኑ ጋር ሊጉን ሲመራ ቆይቶ በሲቲ መነጠቁ ይታወሳል።
ትሬንት “ማንቸስተር ሲቲ ደም ሸተተው (ዋንጫውን አየ) ማለት ጨዋታው አልቋል ማለት ነው” ይላል።












