የአርሰናልን ሽንፈት ተከትሎ ማንቸስተር ሲቲ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን ሆነ

ማንቸስተር ሲቲ ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ቻምፒዮን መሆኑን አረጋግጧል።
የዋንጫ ተቀናቃኝ የነበረው አርሰናል በኖቲንግሃም ፎረስት መረታቱን ተከትሎ ነው ሲቲ ባልድል መሆኑን ያረጋገጠው።
አብዛኛውን የውድድር ዘመን ሊጉን ሲመሩ የነበሩት መድፈኞቹ አንድ ጨዋታ እየቀራቸው ከባለድሉ ሲቲ በአራት ነጥብ ርቀው ተቀምጠዋል።
የፔፕ ጉዋርዲዮላ ቡድን ባለፉት አምስት ዓመታት አራት ጊዜ የዋንጫ ባለቤት መሆን ችሏል።
አልፎም የቻምፒዮንስ ሊግ እና ኤፍ ኤ ዋንጫን ካነሱ ታሪክ መፃፍ ይችላሉ። ከዚህ ቀደም ማንቸስተር ዩናይትድ ብቻ ነው በፈረንጆቹ 1999 ይህን ድል ማሳካት የቻለው።
ሁለቱ የማንቸስተር ከተማ ተቀናቃኞች በኤፍ ኤ ዋንጫ ፍፃሜ ከመገናኘታቸው በፊት ሲቲ በቱርክ ኢስታንቡል በቻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ጨዋታ ኢንተር ሚላንን ይገጥማል።
ማንቸስተር ሲቲ እሑድ [ዛሬ] ከቼልሲ ከተጫወተ በኋላ በሜዳው ዋንጫውን ያነሳል።
ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አራት ጎሎች ያስቆጠረው ጀርመናዊው የሲቲ አምበል ኢካይ ጉንዶዋን “ፕሪሚዬር ሊግ ያለምንም ጥርጥር የዓለማችን ከባዱ ውድድር ነው። ይህ ድል ምን ማለት ነው የሚለውን የሊጉ ክብደት ይገልጠዋል” ብሏል።
“በፍፁም የምረሳው የውድድር ዘመን አይደለም።”
ማንቸስተር ሲቲ መጋቢት 29/2015 ዓ.ም. አንድ ጨዋታ እየቀረው ከአርሰናል በስምንት ነጥብ ርቆ ተቀምጦ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንድ ቡድን 28 ጨዋታዎች አድርጎ [ሊጉን ሊያገባድድ 10 ጨዋታ እየቀረው] በ8 ነጥብ ሊጉን እየመራ ዋንጫ ሳያነሳ ሲቀር በሊጉ ታሪክ አርሰናል አራተኛው ቡድን ነው።
ልክ እንደ አርሰናል፤ ሊቨርፑል በ2018/19 የውድድር ዘመን 10 ጨዋታዎች እየቀሩት ሊጉን በ69 ነጥብ እየመራ ዋንጫውን አሳልፎ ሰጥቷል።
ማንቸስተር ሲቲ 11 የሊጉን ጨዋታዎች በተከታታይ አሸንፏል። ማግኘት ከሚችሉ 42 ነጥብ ሁለት ነጥብ ብቻ ነው የጣሉት። በዚህ ግስጋሴ አርሰናልን ከሊጉ አናት አፈናቅለው የዋንጫ ባለቤት ሆነዋል።
“ለአርሰናል ክብር እንሰጣለን። እስከ መጨረሻው ድረስ ተፋልመውናል። ነገር ግን እኛም በአስደናቂ ሁኔታ ገስግሰን ነው እዚህ የደረስነው” ያለው ደግሞ የሲቲ የቀኝ ተመላላሽ ካይል ዎከር ነው።
ሲቲ በሊጉ ታሪክ ለሦስት ተከታታይ ጊዜ ዋንጫውን ያነሳ አምስተኛው ቡድን ሆኗል። ከዚህ ቀደም ሃደርስፊልድ፣ አርሰናል፣ ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ዩናይትድ ይህን ታሪክ መፃፍ ችለዋል።
ማንቸስተር ዩናይትድ በሰር አሌክስ ፈርጉሰን የአሠልጣኝነት ዘመን ይህ ታሪክ ሁለት ጊዜ መፃፍ ችሏል።
ፔፕ ጉዋርዲዮላ በስፔን ከባርሴሎና ጋር በጀርመን ደግሞ ባየር ሙኒክን ይዞ ለሦስት ተከታታይ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት መሆን ችሏል።
በሃላንድ የተመራው ማንቸስተር ሲቲ ካለፉት ስድስት የውድድር ዘመኖች በአምስት ዋንጫ በማንሳት ኃያልነቱን እያስመሰከረ ነው።
የከተማ ተቀናቃኛቸው ማንቸስተር ዩናይትድ በፈርጉሰን ዘመን ይህን ማድረጋቸው አይዘነጋም። አልፎም የኤፍ ኤ እና የቻምፒዮንስ ሊግ ባለድል በመሆን ‘ሦስትዮሽ’ ድል የተቀዳጁ ናቸው።
በድል እየተንበሸበሹ ያሉት ማንቸስተር ሲቲዎች ከ100 በላይ ሕጎችን ጥሰዋል ተብለው በፕሪሚዬር ሊጉ ክስ ቀርቦባቸው ክሳቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።












