ኤቢሲ ኒውስ ስሜን አጥፍቷል ብለው የከሰሱት ዶናልድ ትራምፕ 15 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈላቸው ተወሰነ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኤቢሲ ኒውስ የተባለው የአሜሪካው ሚድያ የዶናልድ ትራምፕን ስም በማጥፋቱ ለተመራጩ ፕሬዝደንት 15 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማማ።

ታዋቂው የኤቤሲ ኒውስ ዜና አንባቢ ዶናልድ ትራምፕ "በመድፈር ወንጀል ተጠያቂ ናቸው" ማለቱን ተከትሎ ነው ክስ የተከፈተው።

ጆርጅ ስቴፋኖፖለስ ባለፈው ዓመት መጋቢት በተላለፈ ፕሮግራም ላይ ነው በተደጋጋሚ ዶናልድ ትራምፕን የተመለከተ አስተያየት ሲሰጥ የተሰማው።

ዶናልድ ትራምፕ ላይ የቀረበውን የፍትሕ ብሔር ክስ ተከተሎ ባለፈው ዓመት ከሕዝብ የተውጣጣ ችሎት [ጁሪ] ፕሬዝደንቱ "በወሲብ ጥቃት ተጠያቂ ናቸው" ማለቱ ይታወሳል።

ኤቢሲ ኒውስ 15 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ከመስማማቱ በተጨማሪ በዜና አንባቢው ንግግር "መፀፀቱን" የሚገልፅ መግለጫ ይለቃል።

ውሳኔው የገንዘብ ካሳው በእርዳታ መልክ "ለፕሬዝደንታዊ ፋውንዴሽን አሊያም ለከሳሹ ይሰጣል" ይላል።

ከዚህ በተጨማሪ የዜና ጣቢያው ትራምፕ ላወጡት የጠበቃና ሌሎች ወጪዎች መሸፈኛ የሚሆን 1 ሚሊዮን ዶላር ይከፍላል።

አልፎም ባለፈው ዓመት መጋቢት ከታተመው ዘገባ ግርጌ ሥር የዋና አዘጋጁ መግለጫ እንደሚሰፍር ውሳኔው ያሳያል።

መግለጫው "ኤቢሲ ኒውስ እና ጆርጅ ስቴፋኖፖለስ፤ መጋቢት 10/2024 ጆርጅ ስቴፋኖፖለስ ከናንሲ ሜስ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ፕሬዝደንት ዶናልድ ጄ ትራምፕን በተመለከተ ባቀረበው ዘገባ መፀፀታቸውን ይገልፃሉ" ይላል።

የኤቢሲ ነውስ ቃል አቀባይ በመግለጫቸው ኩባንያው "ሁለቱ ወገኖች ጉዳዩን በስምምነት ለመፍታት በመወሰናቸው" ደስተኛ ነው ብለዋል።

በአውሮፓውያኑ 2023 የኒው ዮርክ ፍትሐ ብሔር የሕዝብ ችሎት ትራምፕ በ1996 በአንድ አፓርትማ የመልበሻ ክፍል ውስጥ ኢ ጂን ካሮል የተባለችው ግለሰብ ላይ ወሲባዊ ጥቃት አድርሰዋል ማለቱ ይታወሳል። በተጨማሪ ትራምፕ የግለሰቧን ስም በማጥፋት ጥፋተኛ ሆነዋል።

ዳኛ ሉዊስ ካፕላን በወቅቱ ኢ ጂን ካሮል ትራምፕ እንደደፈራቸው የሚያሳይ በቂ ማስረጃ ለሕዝባዊው ችሎት ማቅረብ አልቻሉም ብለው ነበር።

እኒሁ ዳኛ ዶናልድ ትራምፕ ከሳሿ ኢ ጂን ካሮል ላይ ላደረሱት የስም ማጥፋት 83.3 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ መወሰናቸው አይዘነጋም።

መጋቢት 10 በተላለፈው የኤቢሲ ኒውስ ዘገባ ላይ ስቴፋኖፖለስ የሳውዝ ካሮላይና ሪፐብሊካን የኮንግረስ አባል የሆኑት ናንሲ ሜስ እንዴት ትራምፕን ይደግፋሉ ሲል ይጠይቃል።

ዜና አንባቢው በሐሰት "ዳኞች እና ሁለት የተለያዩ የሕዝብ ችሎቶች ትራምፕን በመድፈር ወንጀል ተጠያቂ ናቸው ብለዋል" ሲሉ ወቅሰዋል።

ስቴፋኖፖለስ በዚህ ፕሮግራም ላይ በተደጋጋሚ ይህንን አስተያየት ሲሰጥ ተሰምቷል።

ትራምፕ ከኤቢሲ ኒውስ በተጨማሪ የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስን ከካማላ ሐሪስ ጋር በነበረው ቃለ-ምልልስ ምክንያት ከሰዋል።

በ2023 ትራምፕ ሲኤንኤን የተባለው የዜና ጣቢያ ከአዶልፍ ሂትለር ጋር አመሳስሎኛል ብለው ቢከሱም ጉዳዩ ችሎቱን በሚመሩት ዳኛ ውድቅ ሆኗል።

ተመራጩ ፕሬዝደንት ኒው ዮርክ ታይምስ እና ዋሺንግተን ፖስት የተባሉት ጋዜጣዎች ላይ ያቀረቡት ክስም ውድቅ ሆኖባቸዋል።