"በወሲብ ወቅት በድብቅ ኮንዶም ማውለቅ መደፈር እንደሆነ አላውቅም ነበር"

ሜጋን ባርተን

በወሲብ ግንኙነት ወቅት አጋርን ሳያሳውቁ በድብቅ ኮንደም ማውለቅ በመድፈር ወንጀል መፈረጁን ማወቋ "እንዳስደነገጣት" ላቭ አይላንድ የተሰኘው የቴሌቪዥን 'ሪያሊቲ ሾው' የቀድሞ ተዋናይ ተናገረች።

በወሲብ ግንኙነት ወቅት ኮንዶምን በድብቅ ማውለቅ በእንግሊዝኛው 'ስቴልዚንግ' የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

ይህም ማለት የወሲብ አጋርዎ ሳያውቁ ወይም ሳይስማሙ በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወቅት ኮንዶምን ማውለቅ ማለት ነው።

ተዋናይቷ ሜጋን ባርተን ይህ ሁኔታ ስድስት ጊዜ እንዳጋጠማት ተናግራለች።

አንደኛው አጋሯ ኮንዶሙ ተቀዶ ነው የሚል ተደጋጋሚ ምክንያት በመፍጠር ኮንዶሙን በማውለቁ አርግዛለች፤ ጽንስ ለማቋረጥ ተገዳለች።

ይህ ድርጊት "ወንጀል እንደሆነ አላውቅም ነበር" ስትል ነው የ30 ዓመቷ ተዋናይት የተናገረችው።

"ይህ ጉዳይ ከአጋርዎት ጋር ብቻ መወያየት ያለባችሁ ጉዳይ ይመስለኝ ነበር" ትላለች።

ማሳሰቢያ፦ ይህ ጽሑፍ አንዳንድ አንባቢዎችን ሊያሳዝኑ የሚችሉ ዝርዝሮችን ይዟል።

ሜጋን ድርጊቱ "ትክክል ያልነ እና ኢፍትሃዊ" መሆኑን 'ዊ ኒድ ቱ ቶክ' ለተባለ ፖድካስት ተናግራለች። የፖድካስቱ አዘጋጅ ፖል ሲ ብሩንሰን ስቴልዚንግ ስለተሰኘው ወንጀል ሲነግራት ነበር የሰውየው ድርጊት መድፈር መሆኑን የተገነዘበችው።

"ስለ ስቴልዚንግ (በወሲብ ወቅት አጋርን ሳያሳውቁ ወይም ሳይስማሙ በድብቅ ኮንዶም ማውለቅ) በጭራሽ ሰምቼ አላውቅም" ትላለች።

"ወሲብ መፈጸም ስንጀምር ኮንዶሙ አለ። ሁሉ ነገር ጥሩ ነበር። ወደ መጨረሻው አካባቢ ሆን ብሎ ያወልቀዋል እናም የሚሰጠው ሰበብ ተቀዶ እንዲሁም ተሰንጥቆ የሚል ነው" ብላለች።

አክላም "አስደንጋጭ ነበር" ስትል ተናግራለች።

የሜትሮፓሊታን ፖሊስ በተለምዶ (በአራዳ ቋንቋ) ስቴልዚንግ የተሰኘው ቃል ድርጊት በሕግ እንደ መድፈር ወንጀል ይቆጠራል ሲል ያስረዳል። በርካቶች ወንጀል መሆኑን ስለማይገነዘቡ በዝቅተኛ ሁኔታ ሪፖርት ከመደረጉ ጋር ተያይዞ ክሶች የተለመዱ አይደሉም።

ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ለንደን በጥቅምት ወር ያደረገው ጥናት እንደሚያሳየው ከ18 አስከ 25 ዓመት ባሉ ወጣቶች መካከል ከአስሩ ከአንድ በላይ የሚሆኑት በወሲብ ወቅት ያለ ስምምነት ኮንዶም ማውለቅን እንደ ወሲባዊ የጥቃት ወንጀል አድርገው አይመለከቱትም።

ኮንዶም እያወጣ ያለ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በታዳጊዎች እና በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቆም የተቋቋመው 'ኢንድ ቫየለንስ ኤጌይንስት ውሜን ኤንድ ገርልስ' የተሰኘው ተቋም ዳይሬክተር አንድሪያ ሲሞን፣ ምንም እንኳን ወሲብ በስምምነት ሊጀመር ቢችልም ግለሰቡ ኮንዶሙን ያለ መነጋገር በድብቅ ካወለቀ ያንን ፍቃድ ጥሷል። ይህም እንደ መድፈር ይቆጠራል፤ በመድፈር ወንጀል ሊከሰስ ይችላል ይላሉ።

"ኮንዶምን ያለ ስምምነት ማውለቅ (ስቴልዚንግ) ምን ያህል እንደተስፋፋ ማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም በርካቶች እንደ ወሲባዊ ጥቃት ወይም ወንጀል መሆኑን ስለማይረዱት ነው" ይላሉ።

"በተለይም ወንዶች በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወቅት ያለ ፈቃድ ሆን ብሎ ኮንዶምን ማውለቅ ወንጀል መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። ወንዶች በሴቶች አካል ላይ መብት አለን የሚለውን የሚያሳይ ሲሆን፣ የሴቶችን በራስ የማዘዝ መብት የሚጥስ ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወቅት ኮንዶሙን በድብቅ ያወለቀ አንድ ግለሰብ በዩናይትድ ኪንግደም የአራት ዓመት እስር ተፈርዶበታል።

በደቡባዊ ለንደን ብሪክስተን ነዋሪ የሆነው የ39 ዓመቱ ጋይ ሙኬንዲ ወሲብ ለመፈጸም ተስማማታ የነበረችው ሴት ላይ ነው ሳታውቅ ኮንዶሙን ያወለቀባት።

በችሎቱ ላይ ሙኬንዲ ይህንን ያደረገው ለረጅም ጊዜ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ስላልፈጸመ እንደሆነ መግለጹን ተዘግቦ ነበር።

ቢቢሲ በአውሮፓውያኑ 2020 በሠራው 'አይ ሜይ ዲስትሮይ ዩ' ተከታታይ ፊልም ላይ ይህ ጽንሰ ሃሳብ በአራተኛው ክፍል ተዳሷል።

ዋና ገጸ ባህርይዋ አራቤላ ወሲብ እየፈጸሙ በነበረበት ወቅት አጋሯ ሳታውቀው ኮንዶሙን አውልቆታል።

አራቤላ ጉዳዩን በአንድ ፖድካስት ላይ ከመስማቷ በፊት መደፈር መሆኑን አታውቅም ነበር። ፊልሙ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ነው። የታዋቂዋ ተዋናይት፣ ፀሐፊ እንዲሁም የፊልም አዘጋጅ ሚኬላ ኮኤልን ታሪክን ዋቢ አድርጎ የተሠራ ነው።

የዚህ ዓይነት ወሲባዊ ጥቃት አሳሳቢነት የሚንጸባረቀው በምንጠቀመው ቋንቋ ነው ሲሉ 'ሬፕ ክራይሲስ' የተሰኘው ተቋም የእንግሊዝ እና የዌልስ ቢሮ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሲአራ በርግማን ይናገራሉ።

"ስቴልዚንግ የተሰኘው ጉዳይ በእንግሊዝ እና በዌልስ ሕግ የመድፈር ዓይነት ነው" ይላሉ።

አክለውም "የግብረ ሥጋ ግንኙነት ለመፈጸም የተስማሙት ኮንዶም በመጠቀም ከሆነ እና አጋራቸውን ሳያሳውቁ ወይም ሳይስማሙ ኮንዶሙን በድብቅ ካወለቁ ፈቃዱ እንደተነጠቀ ነው የሚቆጠረው" ሲሉ ያስረዳሉ።

ይህ ነገር ስጋት ለሆነባቸው ሰዎች ተዋናይቷ ሜጋን ምክሯን ትለግሳለች።

"የምትጠራጠሩት ነገሮች ካጋጠሟችሁ፣ ስጋት ከሆነባችሁ ለጓደኞቻችሁ ተናገሩ። ለአንድ ሰው ተናገሩ እና አብራችሁ ፖሊስ ጣቢያ መሄድ ትችላላችሁ" ትላለች።

"ነገሩ ከከበዳችሁ በቤታችሁም ሆናችሁ ስልክ መደወል ትችላላችሁ። ነገር ግን በእርግጠኝነት ለሰዎች መናገር አለባችሁ። ምክንያቱም የተደረገባችሁ ነገር ፍትሃዊ እንዲሁም ትክክል አይደለም" ስትል ምክሯን ለግሳለች።