በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ስምምነት ላይ ሶማሊላንድ አቋሟን ገለጸች

በምርጫ አሸንፎ ሥልጣን የያዘው ነጻነቷን ያወጀችው የሶማሊላንድ መንግሥት በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና በሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ መካከል ቱርክ ውስጥ የተደረሰውን ስምምነት በሚመለከት አቋሙን አስታወቀ።
ሐሙስ ታኅሣሥ 3/2017 ዓ.ም. ሐርጌሳ ውስጥ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ቃለ መሃላ ፈጽመው ሥልጣን የተረከቡት ተመራጩ አዲሱ የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ ዋዳኒ ፓርቲ ቃል አቀባይ ሞሐመድ ፋራህ አብዲ በሁለቱ አገራት ስምምነት ላይ የመንግሥታቸውን አቋም ለቢቢሲ ሶማሊኛ ተናግረዋል።
ስምምነቱን በተመለከተ በሶማሊላንድ በኩል ያለውን አስተያየት ቃል አቀባዩ እንደተናገሩት በሁለቱ አገራት መካከል አንካራ ላይ የተደረሰው ስምምነት የሁለቱ አገራት ጉዳይ መሆኑን እና ሶማሊላንድ ሌላ አገር በመሆኗ ይህ ጉዳይ የሚመለከታት እንዳልሆነ አስረድተዋል።
"የፈረሙት ሁለቱ አገራት ናቸው፣ እኛ ሶማሊላንድ ነን። ሁለቱ ወንድማማች አገራት የራሳቸውን ስምምነት ነው የተፈራረሙት። እነሱ ተነጋግረው ከስምምነት ላይ መድረሳቸው የተለመደ ነገር ነው። እኛን የሚመለከት አይደለም" ሲሉ የገዢው ዋዳኒ ፓርቲ ቃል አቀባይ ሞሐመድ ፋራህ አብዲ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ቀደም ሲል በሶማሊላንድ ሥልጣን ላይ የነበረው መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመው የመግባቢያ ሰነድ ያለበትን ሁኔታን በተመለከተ ሲናገሩ አዲሱ መንግሥት ገና ሥልጣን መረከቡ በመሆኑ ጊዜ ወስዶ እንደሚመለከተው እና የሚወስንበት መሆኑን ገልጸዋል።
"ገና ሥልጣን መረከባችን ነው፤ ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገውን ስምምነት አልተመለከትነውም። ነገር ግን የምናየው ይሆናል፤ አይተነው የሶማሊላንድን ጥቅም የሚያስጠብቅ ከሆነ እንሠራበታለን፤ ካልሆነ ግን የሚቀር ይሆናል። ስለዚህ ምን እንሚሆን ለማወቅ መጠበቅ አለብን፣ ከዚያ በኋላ ውሳኔ ይሰጥበታል" ብለዋል ቃል አቀባዩ።
ባሕር በር አልባዋ ኢትዮጵያ ለወደብ ፍላጎቷ ምላሽ ለማግኘት በምታደርገው ጥረት ውስጥ ባለፈው ዓመት ከሶማሊላንድ ጋር ከደረሰችው ስምምነት በተጨማሪ ከሶማሊያ ጋር አስተማማኝ እና ዘላቂ የባሕር መተላለፊያ ለማግኘት የሚያስችላት ነው የተባለ ስምምነት አንካራ ላይ ፈርማለች።
በዚህም በሉዓላዊ የሶማሊያ መንግሥት ስር ኢትዮጵያ አስተማማኝ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ዘላቂ የባሕር መተላላፊ እንድታገኝ የሚያስችል ስምምነት ላይ ሁለቱ አገራት የደረሱ ሲሆን፣ ይህንንም ተግባራዊ የሚያደርግ ስምምነት በጥቂት ወራት ውስጥ እንደሚፈረም ተገልጿል።
በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል በተደረሰው ስምምነት ላይ እና ከዚያም በኋላ ከሶማሊላንድ ጋር ቀደም ሲል ስተለደረሰው ስምምነት በሁለቱ አገራት በኩል እስካሁን በግልጽ የተባለ ነገር የለም።
ስምምነቱን ተከትሎ የሶማሊያ የማስታወቂያ ሚኒስትር ዳውድ አዌይስ እንደተናገሩት ግን ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ሙሉ በሙሉ ውድቅ ተደርጓል ቢሉም በአንካራው ሰነድ ላይም ሆነ በመሪዎቹ በኩል ይህንን የሚያመለክት ነገር አልተጠቀሰም።
ዳውድ አዌይስ ግን የሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መሪዎች ስምምነትን በተመለከተ የተሠራጨው ሰነድን በመጥቀስ የሶማሊላንድ ስምምነት ቀሪ መሆኑን ይናገራሉ።
"የወጣውን መግለጫ በመረዳት በኩል ችግር እንዳለ ግልጽ ነው። ሰነዱ ቀደም ሲል የነበሩ ሁሉም ነገሮች ውድቅ እንደሚሆኑ ጠቅሷል፤ ይህም የቀደመው ስምምነት አይኖርም ማለት ነው" ብለዋል የማስታወቂያ ሚኒስትሩ።
ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. በአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት ዕለት አዲስ አበባ ላይ በቀድሞው የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መካከል የባሕር በር አጠቃቀምን በተመለከተ የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙ ይታወቃል።
በስምምነቱ ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ የንግድ እና የባሕር ኃይል አገልግሎት የሚውል የባሕር ጠረፍ ስትሰጥ፣ በምላሹም ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅና ትሰጣለች ተብሎ ነበር።
ይህ ስምምነትም በወቅቱ በአንድ ወር ውስጥ ተግባራዊ እንደሚሆን የተነገረ ቢሆንም የደረሰበት ደረጃ ሳይታወቅ አንድ ዓመት ሊሞላው በተቃረበበት ጊዜ ነው ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በመሪዎቻቸው አማካይነት ሌላ ስምምነት የተፈራረሙት።
ሶማሊያ በኢትዮጵያ እና የግዛቴ አካል ናት ከምትላት ሶማሊላንድ ጋር የደረሰችው ስምምነት ሉዓላዊነቴን የሚጥስ ነው በማለት አጥብቃ ስትቃወመው ቆይታለች።
በተጨማሪም በሁለቱ አገራት መካከል የነበረው ግንኙነት ከመበላሸት አልፎ ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል በሚል በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ከባድ ስጋት ተፈጥሮ ቆይቷል።
በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ተከትሎም ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ ያለችው ግብፅን ጨምሮ ሌሎችም አገራት ለሶማሊያ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ ከስምምነት ደርሰዋል።
ይህም ሶማሊያን የእጅ አዙር የፍልሚያ ሜዳ በማድረግ የአፍሪካ ቀንድን አለመረጋጋት የበለጠ ሊያባብሰው ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።















