ባልተለመደ መልኩ በቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ላይ የተቃውሞ ድምጽ በአደባባይ ተሰማ

የተቃውሞ ድምጽ የተሰማበት አካባቢ

ከቻይናው ኮሚኒስት ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ በፊት ባልተለመደ መልኩ ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ እና የቻይናን የኮቪድ-19 ክልከላን የሚተች የተቃውሞ ድምጽ በአደባባይ ተሰማ።

በስፋት የተሰራጩ ምስሎች ሁለት ሰዎች በቤጂንግ ከተማ በሚገኝ ድልድይ ላይ ሆነው የተቃውሞ መልዕክት ይዘው አሳይተዋል። ባለሥልጣናት የተቃውሞ እንቅስቃሴውን በጥፍት እንደቀጩት ተገልጿል።

የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ታሪካዊ የተባለው ጉባኤ ሊካሄድ ቀናት በቀሩበት ወቅት በመዲናዋ ቤይጂንግ የሕዝብ ብሶት አይሏል ይባላል።

ከስበሰባው በፊት የተጣለው ጥብቅ የደኅንነት እርምጃዎች እና የኮቪድ ክልከላዎች በርካቶች ቁጣቸውን በኢንተርኔት ላይ እንዲገልጹ እያደረጋቸው ነው። 

የከተማዋ ባለሥልጣናት ወደ ከተማዋ መግባት እና መውጣት ላይ ገደብ የጣሉ ሲሆን፣ ይህም ነዋሪዎች መግባት እና መውጣት ተስኗቸዋል። ሌሎች ደግሞ የኮቪድ ስርጭትን ለመግታት ከቤት እንዳይወጡ ታዘዋል።

በስፋት በተሰራጩት ምስሎች ላይ ተቃዋሚዎች ካስተላለፏቸው መልዕክቶች መካከል፡ “የኮቪድ ምርመራ አንፈልገም፤ ምግብ ነው የምንፈልገው፣ ክልከላ ሳይሆን ነጻነት እንፈልጋለን። ውሸት አንፈልግም ክብር እንጂ፣ መሪዎች ሳይሆን የምንፈልገው ድምጽ መስጠትን ነው” የሚሉት ይገኙበታል።

የኮሚኒስት ፓርቲውን ጉባኤ በሚመለከት የተለያዩ ዝግጅቶች ለሕዝብ እየቀረቡ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኮሚኒስት ፓርቲውን ጉባኤ በሚመለከት የተለያዩ ዝግጅቶች ለሕዝብ እየቀረቡ ነው

ሌላኛው ተቃውሞ መልዕክት ደግሞ ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ላይ ያነጣጠረ ሲሆን፣ ለሕዝብ መልዕክት ያስተላለፈም ነበር።

“በትምህር ቤት እና መሥሪያ ቤቶች አድማ አድርጋችሁ አምባገነን እና ብሔራዊ ካሃዲውን ዢ ጂንፒንግን አስወግዱ” ይላል።

የታውሞ ድምጽ ወደተሰማበት ቦታ የቢቢሲ የጋዜጠኞች ቡድን ቢንቀሳቀስም፣ በስፍራው ምንም አይነት የተቃውሞ መልዕክት ለማየት ባይችልም፣ የፖሊስ አባላት ግን በቦታው ሲንቀሳቀሱ ተመልከተዋል።

የፊታችን እሑድ በሚጀምረው የቻይና ገዢ ፓርቲ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወደ 2 ሺህ 300 የሚጠጉ ከፍተኛ የፓርቲው እና የመንግሥት ባለሥልጣናት ወደ መዲናዋ ቤይጂንግ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የፓርቲው ጉባኤ ፕሬዝዳንት ዢ ለሦስተኛ ዙር በሥልጣን እንዲቆዩ ይሁንታውን ይሰጣል ተብሎም ይጠበቃል።

ጉባኤው ሊጀመር ጥቂት ቀናት በቀሩበት በአሁኑ ወቅት ቻይና በዢ አስተዳደር ስር ያመጣቻቸውን ስኬቶች የሚያስመለክቱ ኤግዚቢሽኖት በቤይጂንግ ዙሪያ ለሕዝብ ክፍት የተደረጉ ሲሆን፣ የቻይናን የባለፉ 10 ዓመታት ጉዞን የሚያሳዩ የቴሌቪዥን ዘጋቢ ፊልሞችም እየቀረቡ ነው።

ይህ ብቻ አይደለም፣ ባኤውን ምክንያት በማድረግ ባለ ቀይ ቀለም ምንጣፎች ብቅ ማለት ጀምረዋል። ብዙ ተጠቃሚ ያላቸው የስልክ መተግበሪያዎችም ቀለማቸውን ወደ ቀይ ቀይረዋል።