ዚምባብዌ የዋጋ ንረትን ለመግታት የወርቅ ሳንቲሞችን አስተዋወቀች

በሮበርት ሙጋቤ በስልጣን ግዜ የጀመረውን የኢኮኖሚ ቀውስ አሁንም ድረስ ቀጥሏል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዚምባብዌ ማዕከላዊ ባንክ ከአገሪቱ ኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ጋር ተደምሮ እየናረ የመጣውን የዋጋ ንረት ለመግታት የወርቅ ሳንቲሞችን በመገበያያነት ለመጠቀም ይፋ አድርጓል።

የአገሪቱ ዓመታዊው የዋጋ ግሽበት ከ190 በመቶ በላይ ማደጉን ተከትሎ የማዕከላዊ ባንቡ በያዝነው ወር የወለድ ተመኑን ከእጥፍ በላይ በማሳደግ 200 በመቶ አድርሷል።

እያንዳንዱ ሳንቲም በዓለም አቀፍ ገበያ አንድ አውንስ ወርቅ የሚኖረውን ዋጋ ብሎም 5 በመቶ ሳንቲሙን ለማምረት የወጣውን ተጨምሮ ያወጣል።

ባሳለፍነው አርብ አንድ አውንስ ወርቅ 1,724 ዶላር ያወጣ ነበር።

የዚምባብዌ ሪዘርቭ ባንክ ገዥ ጆን ማንጉዲያ እንዳሉት ሳንቲሞቹ የሚጠበቀውን ለውጥ ካመጡ በቀጣይ በሱቆች ውስጥ መጠቀም ሊጀመር ይችላል።

ሳንቲሙ "ሞሲ-ኦአ-ቱኒያ" የሚል ጽሑፍ ያረፈበት ሲሆን ትርጉሙም "የነጎድጓድ ጭስ" ማለት ነው። ይህም በዚምባብዌ እና ዛምቢያ ድንበር ላይ የምትገኘውን ቪክቶሪያ ፏፏቴ የሚያመነጨውን ጭስ ያመለክታል።

ለዓመታት ሲያሽቆለቁል የቆየው የዚምባብዌ ዶላር በዚህ ዓመት ከዋና ዋና ምንዛሬዎች አንጻር ዋጋው የበለጠ ወድቋል።

አገሪቱ ለአራት አሥርት ዓመታት ያህል በሥልጣን ላይ በነበሩት ሟቹ ሮበርት ሙጋቤ የሥልጣን ዘመን መፈጠር የጀመረውን የኢኮኖሚ ቀውስ አሁንም ድረስ እያስተናገደች ትገኛለች።

በዚሁ የዋጋ ግሽበት ምክንያት እአአ በ2009 የዚምባብዌ ዶላርን ለመገበያያነት ላለመጠቀም ተገዳለች። በምትኩ የውጭ ምንዛሬዎችን በተለይም የአሜሪካን ዶላር በሰፊው ጥቅም ላይ ይውላል።

የአገር ውስጥ ምንዛሪ ከአሥር ዓመታት በኋላ እንደገና ወደ ሥራ ገብቷል። ነገር ግን በፍጥነት ዋጋውን እንደገና አጥቷል።