ዚምባብዌ፡ ሙስና በማጋለጡ ለእስር የተዳረገው ጋዜጠኛ

የዚምባብዌው ጋዜጠኛ ሀፕዌል ቺኖኖ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የዚምባብዌው ጋዜጠኛ ሀፕዌል ቺኖኖ ተፈጽሟል የተባለ የሙስና ወንጀልን ማጋለጡን ተከትሎ ለእስር መዳረጉን ለቢቢሲ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ገለጸ።

"ችግር ሊያጋጥመኝ እንደሚችል ቀድሜ አውቄ ነበር፤ ክላሺንኮቭ ጠመንጃ ያነገቡ ስምንት ሰዎች ታርጋ በሌላው ተሽከርካሪ ተጭነው ወደ መኖሪያ ቤቴ ሲመጡ አልገረመኝም ነበር'' ይላል።

ሆፕዌል ዘገባውን መስራቱን ተከትሎ ከሰባት ሳምንታት በፊት አንድ ማስጠንቀቂያ ደሶት ነበር።

የገዢው ፓርቲ ቃል አቀባይ አንተ "ውሸታም" ነህ ብለው ከጠሩኝ በኋላ የፕሬዝዳንቱን ቤተሰብ ስም በማጥፋት ከሰውኛል ይላል።

ይህ የሆነው ሆፕዌል ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዘ ግዢን በተመለከተ ስለተፈጸመ ሙስና የምርመራ ዘገባ ከሰራ በኋላ ነው። እሱ እንደሚለው ወረርሽኙን ለመዋጋት የሚያግዙ ቁሳቁሶችን በተጋነነ ዋጋ ለመግዛት በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ባክኗል።

በወቅቱ የጤና ሚኒስትሩ ከኃላፊነታቸው የተባረሩ ሲሆን በቀረበባቸው ክስ ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት እየተከተተሉ ይገኛሉ።

ሰዎቹ መኖሪያ ቤቴ ድረስ መጥተው እንድወጣ ሲጠይቁኝ መታወቂያቸውንና የፍርድ ቤት ማዘዣ እንዲያሳዩኝ ጠይቄያቸው ነበር፤ ነገር ግን ማናቸውም ምንም ሊያሳዩኝ አልፈቀዱም።

እንደውም የሳሎኑን መስኮት በጥይት ከሰባበሩት በኋላ በመኝታ ቤቴ በኩል አድርገው ወደውስጥ ገቡ። እኔም ስልኬን ይዤ ሁኔታውን በቀጥታ ስርጭት እያስተላለፍኩ ጠበቅኳቸው።

በወቅቱ ባዶ እግሬን እየጎተቱ አስወጡኝና በተሰባበረው መስታወት በኩል እንዳልፍ አስገደዱኝ። ይሄኛው ለ45 ቀናት በገሀነም የማሳልፈው አስቸጋሪ ጊዜ እንደ ማስጀመሪያ ነበር።

በአስር ቤቱ ውስጥ ብቻዬን አልነበርኩም። በቀዝቃዘው ጠዋት እኔ በቁጥጥር ስር ስውል ታዋቂው የፖለቲካ አቀንቃኝና ሙስናን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ መካሄድ አለበት ሲል የነበረው ጄኮብ ንጋሪቩም በቁጥጥር ስር ውሎ ነበር።

ሁለታችንም የቀረበብን ክስ አመጽ ለማስነሳት አሲራችኋል የሚል ነበር። እሱ የጠራውን የተቃውሞ ሰልፍ እኔም ደግፌው የነበረ ሲሆን ፕሬዝደንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ እና መንግስታቸው ግን እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴ አያስደስታቸውም።

በዋና ከተማዋ ሀራሬ ማዕከላዊ ሬማንድ ማረሚያ ቤት ውስጥ ሳለን የዚምባብዌ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የሆኑት ኔልሰን ቻሚሳ መጥተው እኛን መጠየቃቸው ደግሞ የፕሬዝዳንቱን ቢሮ ሳያበሳጭ አልቀረም።

ስለዚህ በቀጣዩ ቀን ከፍተኛ ጥበቃ ወደሚደረግበት ቺኩሩቢ ማረሚያ ቤት ተዘዋወርን። በዚህ ማረሚያ ቤት ታራሚዎች ከክፍላቸው ውጭ እልፍ ብለው ከተንቀሳቀሱ እግራቸውና እጃቸው በሰንሰለት እንዲታሰር ይደረጋል።

ምንም እንኳን ማረሚያ ቤቱ የተሰራው ለ1360 ታራሚዎች ቢሆንም በውስጡ ግን ከ2600 በላይ ታራሚዎችን ይዟል።

እኔ የገባሁበት ክፍል ለ16 ታራሚዎች ተብሎ የተሰራ ቢሆንም በወቅቱ የነበርው ሰዎች ግን 44 ነበርን። ስንተኛ እንኳን መገላበጥ የምንችልበት ትርፍ ቦታ አልነበረም። ነገሮችን ይበልጥ አስከፊ የሚያደርገው ደግሞ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በየቀኑ ሺዎችን በሚገድልበት ሰአት መሆኑ ነው።

ታራሚዎቹ ከነጭራሽ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ አያደርጉም። በክፍሎቹ ውስጥም ምንም አይነት ውሃም ሆነ ሳሙና አልነበረም። በተጨማሪ ደግሞ በአንድ ቀን ውስጥ ለ17 ሰዓታት ተቆልፎብን ነው የምንውለው።

ወደ ውጪ ስንወጣ ደግሞ 500 ታራሚዎች በጋራ የሚጠቀሟቸው ሁለት መጸዳጃ ቤቶች አሉ። አሁንም ቢሆን ግን እነዚህ መጸዳጃ ቤቶች ውሃ የሚባል ነገር የላቸውም።

የሚቀርብልን ምግብም ቢሆን ንጽህናውን ያልጠበቀና በክራቶችን የሚያሳምም ነበር። ከአንድ ወር በፊትም በእጅጉ ታምሜ ነበር። ከፍተኛ ትኩሳት የነበረኝ ቢሆንም የማረሚያ ቤቱ ሆስፒታል ግን ህመም ማስታገሻ እንኳን አልነበረውም።

ያለው ሁኔታ በጣም ከባድ ስለሆነ በርካታ ታራሚዎች ፊታቸውን ወደ ፈጣሪያቸውና ሀይማኖታቸው አዙረው ነበር።

መስከረም ወር ላይ በዋስ እንድፈታ ሲወሰንልኝ አብረውኝ የነበሩት ታራሚዎች በጣም ደስተኞቹ ነበሩ። ''ከዚህ ከወጣህ በኋላ አትርሳን እሺ'' ሲሉኝ እንባ ተናነቀኝ።

በቁጥጥር ስር በዋልኩበት ወቅት የመንግስት ቃል አቀባዩ የትኛውም የሥራ አይነት ከሕግ በላይ አይደለም ሲሉ ነበር። ይሄ ጋዜጠኖች ላይ ፍርሀትን ለመንዛትና አፍ ለማስዘጋት ሆን ተብሎ የሚደረግ ነገር ነው።

በቅርቡ እጃቸው ላይ ትልቅ መረጃ ያለ ወጣት ጋዜጠኞችን ተዋውቄ ነበር። ለምን መረጃውን ለህዝብ ይፋ አታደርጉም ስላቸው ''ለሕይወታችን እንፈራለን'' ነበር ያሉኝ።