ዚምባቡዌ ውስጥ የእግር ጣት በዶላር እየተሸጠ ነውን?

የእግር ጣቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዚምባቡዌ ውስጥ ካለው የኑሮ ውድነት የተነሳ ሰዎች የእግር ጣቶቻቸውን እየሸጡ ነው ተብሎ የተናፈሰው ወሬ ናይጄሪያ ደርሷል።

አንድ ዚምባቡያዌ ጦማሪ ነው በዋና ከተማዋ ሐራሬ በሚገኝ አንድ የገበያ ማዕከል የእግር ጣት እየተቸበቸበ ነው ሲል ወሬ ያናፈሰው።

ይህ ጦማሪ፤ ሰዎች ጣቶቻቸውን ደቡብ አፍሪካ ለሚገኝ የባሕል ሐኪም እስከ 40 ሺህ ዶላር ድረስ እየሸጡ ነው ይላል።

ይህን ተከትሎ በዚምባብዌ የእግር ጣት በዶላር እየተሸጠ ነው የሚለው መረጃ በስፋት ተሰራጭቷል።

ወሬው ናይጄሪያ ውስጥ የሰረፀው የሰውነት አካላትን መሸጥ ሃብትን ያመጣል ተብሎ ስለሚታመን ነው።

ባለፈው ጥር ናይጄሪያ ውስጥ ሶስት ሰዎች ታዳጊ ሴቶችን ለባሕላዊ እምነት ገድለዋል ተብለው ታስረው ነበር። 

የባሕል ሐኪሞች የሰውነት አካላትን “ለፈውስ” መጠቀማቸው አዲስ ክስተት አይደለም።

ነገር ግን እኚህ ሐኪሞች “ከጥንቆላ” ጋር የሚያያዙና ከአንዳንድ የተከበሩ የባሕል ሐኪሞች ለየት ያለ መንገድ ነው የሚከተሉት። 

ቢሆንም 40 ሺህ ዶላር ለትልቁ ጣት፣ ለመሃል ጣት 25 ሺህ ዶላር፣ ለትንሿ ጣት 10 ሺህ የተባለው ሃሰት ሆኖ ተገኝቷል።

ዚምባቡዌያዊን ማሕበራዊ ድር አምባዎች ላይ ጉዳዩን ቀልድ አድርገው ይዘውታል።

መረር ያሉ ዜናዎችን የሚያስነብቡ የሐራሬ ጋዜጣዎች ግን ይህን ታሪክ ከማተም ተቆጥበዋል።

አንዳንድ የትዊተር ተጠቃሚዎች ይህ ቧልት በሃገሪቱ ያለውን ኮስተር ያለ የምጣኔ ሃብት ቀውስ ለመሸፋፈን የተፈጠረ ነው ይላሉ።

ጋምባክዌ በተሰኘው አውታር ነው ሐራሬ በሚገኘው ዚሜክስ መገበያያ ማዕከል “የእግር ጣቶች እየተሸጡ ነው” ተብሎ ወሬ የተነዛው።

ይህ ከተናፈሰ ከጥቂት ቀናት በኋላ አንድ ጋዜጣ ሰዎች ይህን የቧልት ወሬ ሰምተው ለማጣራት ወደ ገበያ ማዕከሉ እየመጡ እንደሆነ ዘግቧል።

እንደ ዩጋንዳና ናይጄሪያ ያሉ ሌሎች ሃገራትም ዚምባቡዌ ውስጥ የእግር ጣት በረብጣ ዶላር እየተሸጠ ነው ሲሉ ወሬውን አናፍሰዋል።

አንድ የኬንያ ሬድዮ ጣቢያ በትዊተር ገፁ “ባልተረጋገጠ ወሬ ዚምባቡዌያን ጣቶቻቸውን እየቸበቸቡ ነው” ሲል ፅፏል።