የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ልጅ ባለቤት በማጭበርበር ተጠርጥሮ እየተፈለገ ነው

የፎቶው ባለመብት, ICPC
የናይጄሪያ የሙስና መርማሪዎች እንዳሳወቁት የፕሬዚዳንቱ ልጅ ባለቤት ጊምባ ያው ኩሞ 65 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ በማጭበርበር ተጠርጥሮ እየተፈለገ መሆኑን ነው።
ማጭበርበሩ ከቤቶች ጋር የተያያዘ እንደሆነም መርማሪዎቹ ገልፀዋል።
ቤቶች ለመስራት ብድር በማበደር የሚታወቀው ፌደራል ሞርጌጅ ባንክ ኦፍ ናይጄሪያ የቀድሞ ዳይሬክተር የነበረው ይህ ግለሰብ በጥብቅ ከሚፈለጉ ዋነኛ ሰው መሆኑንም የአገሪቱ ኢንዲፔንደንት ኮረፕት ፕራክቲስስ ኮሚሽን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ከዚህ ግለሰብ በተጨማሪ ሌሎች ሁለት ሰዎችንም እያደነ መሆኑን አስታውቋል።
የግለሰቡ ፎቶም በየቦታው የተበተነ ሲሆን "ተፈላጊና እየታደነ መሆኑም ተገልጿል።
"በፎቶው ላይ የምታዩዋቸው ታሪ ሩፈስ፣ ጊምባ ያው ኩሞና ቦላ ኦጉንሳለ ይባላሉ። በጣም ተፈላጊ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ግለሰቦች የአገሪቱን ብሄራዊ የቤቶች ፈንድ በማይገባ በመጠቀም ከ65 ሚሊዮን ዶላር በላይ አጭበርብረዋል" በማለት የኮሚሽኑ ቃለ አቀባይ አዙካ ኦጉጋ በመግለጫቸው ተናግረዋል።
"ግለሰቦቹ ያሉበትን የሚያቅም ሆነ ስለነሱ ጠቃሚ ጉዳዮች ካላችሁ አቡጃ ወደሚገኘው የኮሚሽኑ ዋና ቢሮ ወይጀም ወደተለያዩ ቅርንጫፎቻችንና ፖሊስ ጣቢያ ልታሳውቁ ትችላላችሁ" በማለትም ስልኮች የተቀመጡባቸው ወረቀቶች ተበትነዋል።
ጊምባ ያው ኩሞ የፕሬዚዳንት ሙሃመዱ ቡሃሪን ሁለተኛ ልጅ ፋጢማን ያገባው በአውሮፓውያኑ 2016 ነበር።
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ሶስቱ ግለሰቦች ምንም አይነት አስተያየት ከመስጠት የተቆጠቡ ሲሆን የፕሬዚዳንቱ ቃለ አቀባይ ምርመራውን በተመለከተ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
በሚያዝያ ወር የናይጄሪያ ምክር ቤት አንድ ኮሚቴ ጊምባ ኩሞ የባንኩ ዳይሬክተር በነበረበት ወቅት መደበኛ ባልሆነ የተፈረመ ውል ጋር በተገናኘ ጥያቄዎች እንዲመልስ ተጠርቶ እንደነበር የናይጄሪያ ፕሪምፕየም ታይምስ ሪፖርት አስነብቧል።
የቀድሞ ወታደራዊ አመራር የነበሩት ፕሬዚዳንት ቡሃሪ ለሁለተኛ ጊዜ ተመርጠው በስልጣን ላይ ያሉትም በአገሪቷ ውስጥ ያለውን ስር የሰደደ ሙስና እታገላለሁ በሚል በገቡት ቃል ነው።
የናይጄሪያ ኢንዲፔንደንት ኮረፕት ፕራክቲስስ ኮሚሽን በመንግሥትና በህዝብ ተቋማት ላይ የተፈፀሙ የሙስና ወንጀሎችን አጣራለሁ የሚል ድርጅት ነው።












