ቻይና መንኩራኩሯን ማርስ ላይ በማሳረፍ ከአሜሪካ ቀጥሎ ሁለተኛዋ አገር ሆነች

የዙህሮንግ ሮቦት ምስል ተሰርቶ

የፎቶው ባለመብት, CNSA

ቻይና መንኩራኩሯን ማርስ ላይ ስኬታማ በሆነ ሁኔታ ማሳረፏን የአገሪቱ ብሔራዊ መገኛ ብዙኀን ዘገበ።

ባለስድስት እግሩ እና ዙሁሮንግ የተሰኘው ሮቦት ወደ ማርስ የተላከው በፕላኔቷ ሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ላይ የሚገኝ አንድ ክፍልን ዒላማ አድርጎ ነው።

ይህ ሮቦት የመከላከያ እቃዎችን፣ ፓራሹት እንዲሁም ወደ ምድር ለመመለስ የሚረዳ ሮኬት ይዟል።

በማርስ ላይ መንኩራኩር ለማሳረፍ ያለውን ፈታኝ ሂደት በመጥቀስ ሮቦቱ የማርስን ምድር በስኬት በመርገጡ ተደንቋል።

እስካሁን ድረስ በማርስ ላይ መንኩራኩሯን በማሳረፍ ስኬታማ የነበረችው አሜሪካ ብቻ ነበረች።

ይህ ማርስን እየተሽከረከረ የሚቃኝ ሮቦት መንኩራኩር ቻይናን ሁለተኛ ያደረጋታል ተብሏል።

ዙህሮንግ ማለት የእሳት አምላክ ማለት ሲሆን ወደ ማርስ የተወነጨፈው ከፕላኔቱ በላይ በየካቲት ወር ከደረሰችው ታይናዌን-1 ኦርቢተር ነው።

ማርስን ለመርገጥ ረዥም ጊዜ የፈጀው አካባቢው ላይ ቅኝት ሲደረግ፣ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምስል ሲወሰድ እና ለማረፍ ምቹ የሆነ ስፍራ ሲመረጥ ነው ተብሏል።

የዚህ ሁሉ ዓላማው በተቻለ መጠን ሸለቆዎችን እና ትልቅ ቋጥኞችን ለማስወገድ በማሰብ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።

ታይንዌን -1 ኦርቢተር ከደረሰችበት ጊዜ አንስቶ የማርስን ገጽታ ስትቃኝ ቆይታለች

የፎቶው ባለመብት, CNSA

በአሁኑ ሰዓት ማርስ የምትገኝበት ርቀት 320 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ሲሆን አንድ የሬዲዮ መልዕክት ከፕላኔቷ ምድር ላይ ለመድረስ 18 ደቂቃ ይፈጅበታል።

ዙህሮንግ ማርስ ላይ እየቀረበች በነበረበት ወቅት እያንዳንዱ ሂደት በተናጥል መታየት እንደነበረበት መሃንዲሶቹ ይናገራሉ።

ሮቦቱ ወደ ማርስ ከባቢ አየር ሲገባ ፣ ያለመንገራገጭ እንዲያርፍ እንዲሁም መመለሱን በሚመለከትም ተመሳሳይ የሆነ ቅደም ተከተል እና ሂደትን ይከተላል።

በሚመረጥ ቅጽበትም ይህ ማርስን የሚዞር ሮቦት ከታይናዌን ኦርቢተር ወደታች እንዲምዘገዘግ ይደረጋል።

ወደ ምድር በሚመጣበት ወቅት ፍጥነቱን ለመቀነስ የሚረዳ ሙቅን የሚቋቋም ልባስ የተገጠመለት ሲሆን፣

የያዘውም ፓራሹት ቢሆን ይህንኑ ይረዳዋል።

በስተመጨረሻም ሮቦቱ ላይ የተገጠመው ሮኬት በመወንጨፍ ወደ ምድር የሚያደርገውን ጉዞ ያሳልጣል።

ቻይና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፈታኝ የሆነውን የሕዋ ላይ ምርምር በስኬት እየተወጣችው ትገኛለች።

በቅርቡ ሁለት መንኮራኩሮችን በጨረቃ ላይ በማሳረፍ ብቃቷን ያስመሰከረችው ቻይና አሁን ደግሞ በማርስ ላይ መንኮራኩሯን አስቀምጣለች።

አሁን ተመራማሪዎች 90 ቀናት አላቸው።

ማርስ ላይ አንድ ቀን ማለት 24 ሰዓት ከ39 ደቂቃ ነው።

ሮቦቱ ፎቶ የሚያነሳበት ካሜራ የማርስን ምድር በማሰስ የማዕድን ሃብቷን ማጥናት የሚያስችለው እና ከመሬት በታች ያለን ውሃ ለመፈተሽ የሚያግዝ መሳሪያዎች ተገጥመውለታል።