'ልጆቼን ሳይሆን እኔን ድፈሩኝ' - አስፈሪው የሱዳን ጦርነት

የፎቶው ባለመብት, BBC/Mohanad Hashim
ሱዳን በቋፍ ላይ ናት።
ለ17 ወራት የዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት አገሪቱን አሽመድምዷል። የአገሪቱ ጦር በመዲናዋ ካርቱም በተቀናቃኛቸው በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) እጅ የሚገኙ አካባቢዎችን ዒላማ በማድረግ ከፍተኛ ጥቃት መፈጸም ጀምሯል።
ጦርነቱ ሲጀመር አርኤስኤፍ አብዛኛውን የካርቱም አካባቢዎች ሲቆጣጠር የአገሪቱ ጦር ደግሞ ከአባይ/ናይል ወንዝ ማዶ የምትገኘውን ኦምዱርማን ከተማን ተቆጣጥሯል።
ይሀም ቢሆን ግን ሰዎች ከአንዱ ስፍራ ወደ ሌላኛው የሚሻገሩባቸው መንገዶች አሉ።
ኦምዱሩማን ላይ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ ረከስ ይላል። ምግብ ለመግዛት ለአራት ሰዓታት በእግር ተጉዘው ወደ ከተማዋ የገቡ አራት ሴቶችን አገኘናቸው።
ሴቶቹ የመጡት በአርኤስኤፍ ቁጥጥር ስር ከምትገኘው ዳሬ ሳላም አካባቢ ነው።
ባሎቻቸው ከቤት እንደማይወጡ ይናገራሉ። ከወጡ የአርኤስኤፍ ተዋጊዎች ይደበድቧቸዋል። ገንዘባቸውን ይወስዱባቸዋል። ወይም ያስሯቸው እና ለመፍታት ክፍያ ይጠይቃሉ።
"ይህን ችግር የምንታገሰው ልጆቻችንን መመገብ ስለምንፈልግ ነው። ተርበናል፣ ምግብ እንፈልጋለን” ብላለች አንዷ።
ማስጠንቀቂያ፡ በታሪኩ ውስጥ ያሉት አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮች ለአንባቢዎችን ሊከብዱ ይችላሉ።
እናንተስ ከባሎቻችሁ በተሻለ ደህንነት አላችሁ? መደፈርስ የለም?
ድምጻቸው ጠፋ።
ከዚያ አንዷ መናገር ጀመረች።
"ቀሪው ዓለም የት አለ? ለምን አትረዱንም?" አለች። መናገር ስተጀመር እንባዋ በጉንጯ ላይ ይፈስ ጀመር።
"እዚህ ጥቃት የደረሰባቸው በጣም ብዙ ሴቶች አሉ። መናገር ግን አይፈልጉም። መናገር ምን ለውጥ ሊያመጣ?”
ቀጠለች፤ "የአርኤስኤፍ አባላት አንዳንድ ልጃገረዶችን በምሽት ጎዳና ላይ እንዲተኙ ያደርጓቸዋል። ከዚህ ገበያ ዘግይተው ከተመለሱ ለአምስት ወይም ለስድስት ቀናት ያቆዩዋቸዋል።"
እሷ ስታወራ እናቷ ጭንቅላቷን በእጇ ይዛ ተቀምጣ ማልቀስ ጀመረች። በዙሪያዋ ያሉ ሌሎች ሴቶችም ማልቀስ ጀመሩ።
"በአንተ አገር ልጃችሁ ወጥታ ከቀረች በዛው ትተዋታላችሁ?" ብላ ጠየቀች።
“አትፈልጓትም እንዴ? ንገሩን ምን ማድረግ እንችላለን? በእጃችን ላይ ምንም ነገር የለም። ማንም አያስብልንም። ቀሪው ዓለም የት አለ? ለምን አትረዱንም!"
የማቋረጫ ስፍራው ወደ ተስፋ መቁረጥ እና የተስፋ ቢስነት ዓለም የሚያስገባ መስኮት ነበር።
ሴቶቹ ህገወጥነት፣ ዝርፊያ እና ጭካኔ መስፋፋቱን ይገልጻሉ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ ከ10.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ተገደዋል ብሏል።
በጦር ሠራዊቱ እና በፈጥኖ ደራሹ መካከል የተፈጠረውን የስልጣን ግጭት ተከትሎ የተቀጣጠለው ጦርነት ታጣቂ ቡድኖች ብቻ ሳይሆን ከጎረቤት አገራት የመጡ ተዋጊዎችን ከማሳተፉም በላይ መለያ ባህሪው ጾታዊ ጥቃት ሆኗል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮከር ተርክ እንደተናገሩት ከሆነ መድፈር እንደ "ጦርነት መሳሪያ" እያገለገለ ነው።
በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አጣሪ ቡድን በአገሪቱ ጦር አባላት የሚደርሱ የመድፈር እና የመድፈር ዛቻዎችን በሚመለከት በርካታ ጉዳዮችን መዝግቧል። ነገር ግን መጠነ ሰፊ የሆነ የጾታ ጥቃት በአርኤስኤፍ እና ተባባሪው በሆኑ ሚሊሻዎች መፈጸሙንና ይህም የዓለም አቀፍ ህግን የጣሰ ሊሆን እንደሚችል አረጋግጧል።
ቢቢሲ ያነጋገረቻት አንዲት ሴት አርኤስኤፍ ደፍሮኛል ስትል ከሳለች።
ሱክ አል-ሃር (የሙቀት ገበያ እንደማለት ነው) ተብሎ በሚጠራው መተላለፊያ ነው ያገኘናት።
ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ገበያው ከኦምዱርማን ወጣ ብሎ በሚገኘው በረሃማ መሬት ላይ ከመስፋፋት ባለፈ ምርቶች በዝቅተኛ ዋጋ ስለሚቀርብ ድሆችን እየሳበ ነው።

የፎቶው ባለመብት, BBC/Ed Habershon
ሚርየም (ስሟ ተቀይሯል) ዳሬ ሳላም ከሚገኘው ቤቷ ሸሽታ ከወንድሟ ጋር መጠለያ ውስጥ ትገኛለች።
አሁን ሻይ ቤት ውስጥ ትሠራለች። ጦርነቱ እንደጀመረ አካባቢ ሁለት የታጠቁ ሰዎች ቤቷ ገብተው የ17 እና 10 ዓመት ሴት ልጆቿን ሊደፍሯቸው ሞክረው ነበር።
“ልጆቼን ከኋላዬ እንዲቆሙ አድርጌ “ለመድፈር ከፈለጋችሁ እኔ ድፈሩኝ” ስል ለአርኤስኤፍ አባላቱ ነገርኳቸው።”
“መቱኝና ልብሴን እንዳወልቅ አዘዙኝ። ከማውለቄ በፊት ልጆቼን እንዲወጡ ነገርኳቸው። ሌሎቹን ልጆች ወስደው በአጥሩ ዘለሉ:: ከዚያም አንዱ በላዬ ላይ ተከመረብኝ።”
ወሲባዊ ጥቃትን እና ሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመከላከል አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ መውሰዱን አርኤስኤፍ ለዓለም አቀፍ መርማሪዎች ተናግሯል።
በርካታ እና ተመሳሳይ የወሲብ ጥቃት ምስክርነቶች ተሰምተዋል። ተጽዕኖውም ቢሆን ቀላል የሚባል አይደለም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዛፎች ስር በርጩማ ላይ ተቀምጣ የነበረችው ፋጡማ (ስሟ ተቀየረ) መንታ ልጆችን ለመውለድ ወደ ኦምዱርማን እንደመጣች ነገረችን እና እዛው ለመቆየት እንዳቀደች አጫወተችን።
የ15 ዓመት ጎረቤቷ ማርገዟን ተናገረች። እሷና የ17 ዓመት እህቷ በአራት የአርኤስኤፍ ወታደሮች ከተደፈሯት ነበር ያረገዘችው።
ሰዎች በጩኸት በመስማታቸው የሆነውን ለማየት ወጡ ትላለች። ሆኖም ወደ ቤታቸው ካልተመለሱ በጥይት እንደሚመቱ በታጣቂዎች ነገራቸው።
በማግስቱ ጠዋት ሁለቱን ሴት ልጆች በሰውነታቸው ላይ የመጎዳት ምልክት ነበራቸው። ታላቅ ወንድማቸው ደግሞ በአንደኛው ክፍል ውስጥ ተቆልፎበት ተገኘ።
"አርኤስኤፍ ከመጣ ጀምሮ ስለአስገድዶ መድፈር ወንጀል መስማት ጀመርን። በኋላም በጎረቤታችን አየነው። መጀመሪያ ላይ [ስለ ሪፖርቶቹ] ጥርጣሬ የነበረን ቢሆንም ሴቶቹን የደፈረው አርኤስኤፍ መሆኑን እናውቃለን።"
ሌሎቹ ሴቶች በአርኤስኤፍ ቁጥጥር ስር ወደሚገኙት አካባቢዎች የሚያደርጉትን ጉዞ ለመጀመር መሰባሰብ ያዙ። ልክ እንደሚርየም ሁሉ ዳሬ ሳላምን ለቀው በመውጣት አዲስ ህይወት ለመጀመር የነጡ ደሃዎች መሆናቸውን ይናገራሉ።
ይህ ጦርነት እስካለ ድረስ ወደ አስፈሪው ህይወት ከመመለስ ውጪ ሌላ አማራጭ የላቸውም።












