ውብ ጽጌረዳዎችን ወደ አውሮፓ ለመላክ በእርሻዎች ውስጥ ከባድ ሕይወት የሚመሩት ሴቶች

አበባ

የፎቶው ባለመብት, Kate Stanworth

ውጪን የጨረቃ ብርሃን የሌለበት ደቅድቅ ጨለማ ውጦታል። አን ለጊዜው ተብላ በተቀለሰች ቤቷ ውስጥ ተቀምጣለች። አድካሚው የአበባ መሰብሰብ እና ድረደራ ሥራዋን አጠናቃ መግባቷ ነበር።

አን (ስሟ የተቀየረ) ብቻዋን ልጇን ታሳድጋለች። ከመዲናዋ ናይሮቢ በ90 ኪሜ ርቀት ላይ በኬንያ አበባ እርሻዎች በምትታወቀው ናይቫሻ ሐይቅ ዳርቻ በርካታ እርሻዎች ይገኛሉ። አን እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ኬንያውን ሴቶች አበባዎችን በመልቀም እና በማዘጋጀት ያሳልፋሉ።

ሙቀታቸው በመሣሪያዎች ቁጥጥር በሚደረግባቸው እና አነስተኛ ሜዳ በሚያካክሉት በርካታ የአበባ ማብቀያ ድንኳኖች (ግሪን ሃውስ) ውስጥ አን እና ባልደረቦቿ ለገበያ የሚቀርበውን አበባ ይንከባከባሉ።

የማይበቅል የጽጌረዳ ዓይነት የለም። አብዛኛውም ባሕር አቋርጦ ለአውሮፓ ገበያ የሚቀርብ ነው።

አን ከ15 ዓመታት በላይ በአበባ እርሻ ላይ በመሥራት አሳልፋለች። ኢንደስትሪው ከኬንያ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ አንዱ ነው።

ኢንደስትሪው ከ150 ሺህ በላይ ሰዎችን እንደሚቀጥር ይገመታል። ለአገሪቱም በየዓመቱ ወደ 1 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስገኝ ይነገራል።

ሕይወቷን ለኢንደስትሪው ብትሰጥም፣ ወርሃዊ ክፍያዋ ከ100 ዶላር ፈቀቅ ሳይል ዓመታት እንደተቆጠሩ ትናገራለች።

ይህ ደግሞ በኬንያ እየተባባሰ ለሚገኘው የኑሮ ውድነት በቂ አይደለም። እንደ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ሩዝ እና ስኳር ያሉ የመሠረታዊ ፍጆታዎች ዋጋ ጨምሯል።

በየወሩ መገባደጃ ሲደርስ አስቤዛዋም ይገባደዳል። አን በቂ ምግብ ስለማይኖራት ብዙ ጊዜ ላለመብላት ትገደደላች።

የ23 ዓመት ልጇ ናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ እንዲማር ብድር ለመውሰድ ተገዳለች። “ለመኖር ዕዳ ውስጥ መግባት አለብህ” ትላለች።

ፀሐይ ወገግ ስትል አን በመቶዎች ከሚቆጠሩ ሌሎች ሠራተኞች ጋር ተሰልፋ ወደ እርሻው የሚወስዳቸውን የኩባንያውን አውቶቡሶችን ትጠብቃለች።

አን በሳምንት ስድስት ቀን ጠዋት 1፡30 ሰዓት ጀምሮ እርሻው ላይ መሥራት ትጀምራለች። እሑድ ደግሞ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ታሳልፋለች።

በአበባ እርሻው ለስምንት ሰዓት መሥራት ይጠበቅባታል። ብዙ ጊዜ ግን ለተጨማሪ ሦስት ሰዓታት ለመሥራት ትገደደላች። የትርፍ ሰዓት ክፍያ እንደማታገኝ ግን ትናገራለች።

በአበባ ማሸጊያ ክፍል ውስጥ ትሠራ ነበር። አበቦቹ የሚጸዱበት፣ የሚሰበሰቡበት እና የሚደረደሩበት ክፍል ነው።

በክፍሉ የነበሩ ሁኔታዎች ከባድ እንደነበሩ ትናገራለች።

የአበባው ኩባንያ በየቀኑ ማሳካት የሚገባቸውን የምርት ግብ ያስቀምጣል። ሠራተኞቹ ይህንን እንዲያሳኩ በተቆጣጣሪዎች ግፊት ይደረግባቸዋል።

“በቀን 3 ሺህ 700 የአበባ ዘንጎች ደረጃ መስጠት ነበረብን” ትላለች።

ለአን ይህ ቁጥር ከእውነታው የራቀ እንደነበር ይሰማታል። እንደ እሷ ያሉ ሠራተኞች የሚጠበቅባቸውን ከማሳካት ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ተናግራለች። ካልሆነ ግን ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

የቀን ተቀን ግቧን ካላሳካች ምክንያቷን የሚገልጽ ደብዳቤ ለኃላፊዋ መጻፍ ይጠበቅባታል።

“ካላሳካህ ልትባረረም ትችላለህ” ብላለች።

ኬንያ ወደ አውሮፓ አበባ በመላክ ወዳሚ ከሆኑ አገራት አንዷ ናት

የፎቶው ባለመብት, Kate Stanworth

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አን እአአ በ2023 መጀመሪያ ላይ ከደም ጋር በተያያዘ ካልታከመች ገዳይ ሊሆን በሚች በሽታ ተያዘች።

በህመሟ ምክንያት ከድካም በተጨማሪ የትንፋሽ እጥረት ስላጋጠማት ሥራዋ እጅግ እየከበደባት ሄደ።

በእርሻ ውስጥ ወደሚገኝ ነርስ ሄዳ መድኃኒት ተሰጣት። ለጥቂት ሰዓታት እንድታርፍ ከፈቀደላት በኋላ ወደ ሥራ እንድትመለስ ተነገራት።

“'ታውቃለህ፣ ለመሥራት አልችልም። በጣም ታምሜያለሁ' አልኩት” ስትል አን ታስታውለች።

ነርሱን በትክክልም ስለመታመሟ ለማሳመን ከባድ ነበር። መጨረሻ ላይ ተሳክቶላት ከእርሻው ውጪ ወደሚገኝ ዶክተር እንድትሄድ ተስማሙ።

ከታከመች በኋላ ህመሟ ከባድ እንደሆነ ተነግሯትም የተፈቀደላት የአንድ ቀን እረፍት ብቻ ነው።

“ታምሜ ስለነበር በጣም ተሰምቶኝ ነበር” ትላለች።

አስገራሚው ነገር ደግሞ የዚያን ዕለትም ለምን ዕለታዊ ዒላማዋን ማሳካት እንዳልቻለች ደብዳቤ መጻፍ ነበረባት።

አን በአበባ እርሻ ላይ ስትሠራ ጤንነቷን ሊጎዳ ስለሚችልባቸው መንገዶች በማሰብም ትጨነቃለች። ለምሳሌ ጽጌረዳዎቹን እንድትረጭ ስለሚሰጣት ኬሚካሎች በማሰብ ትጨነቃለች።

ሌሎች ሠራተኞችም ይህንን ስጋት በተመሳሳይ መልኩ ይጋራሉ።

በሌላ የአበባ እርሻ ላይ የምትሠራው ማርጋሬትም ያለምንም የመከላከያ ልብስ በአበቦች ላይ ኬሚካል ለመርጨት እንደሚገደዱ ተናግራለች።

ማርጋሬት (ስሟ ተቀይሯል) ከናይቫሻ ሐይቅ ዳርቻ ብዙም በትርቀው በአነስተኛዋ የጓደኛዋ መኖሪያ ቤት በምሽት ብቻ እንድናገኛት ጠይቃናለች።

ከአበባው ኢንደስትሪ የሚደርስባትን ቅጣት በመፍራት ለመናገር አትደፍርም። የእርሻዎቹ ባለቤቶች ናይቫሻ ላይ ሙሉ ለሙሉ ተጽዕኖ አላቸው ብላለች።

“ማንም አያስብልንም” ብላም አክላለች።

ባለፈው ዓመት መስከረም ላይ ናይሮቢ መቀመጫውን ያደረገው ሩት ቱ ፉድ ኢንሺየቲቭ የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት፣ በጣም አደገኛ ፀረ ተባይ መድኃኒቶች በኬንያ እርሻ ውስጥ በመደበኛነት ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ባወጣው ሪፖርት ገልጿል። አንዳንዶቹ ካንሰር እንደሚያስከትሉ ይታወቃል።

ማርጋሬት ስለጉዳዩ ለማንሳት ከአለቆቿ ጋር በተደጋጋሚ እንደተገናኘች ተናግራለች።

“ወንዶችም፣ ሴቶችም ላይ ይጮኻሉ” ብላለች። “ሁሉም ላይ ይጮኻሉ፤ ኬንያውያን ቢሆኑም ግድ የላቸውም።”

ሴቶችም ሠራተኞች በወንድ ባለደረቦቻቸው ፆታዊ ትንኮሳ ሊደርስባቸው እንደሚችልም ትናገራለች። በዚህ ዙሪያ ኢንደስትሪው ከፍተኛ ቅሬታ ይቀርብበታል።

የፆታዊ ትንኮሳ ክሶችን፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያ፣ አስቸጋሪ የሥራ ሁኔታ እና የመከላከያ አልባሳት እጥረትን በተመለከተ ለኬንያ የአበባ ምክር ቤት እና ለኬንያ እጽዋት ጤና ቁጥጥር አገልግሎት ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ አልሰጡንም።

ብዙዎቹ ሠራተኞች ሌላ ሥራ የማግኘት ዕድላቸው ጠባብ ነው

የፎቶው ባለመብት, Kate Stanworth

የኬንያ የአበባ እርሻዎች በአካባቢው ላይም ትልቅ ስጋት ፈጥረዋል።

የአበባ እርሻዎች ብዙ ውሃ ይፈልጋሉ። የአውሮፓን ገበያ በርካሽ አበቦች ለመሙላት ሲባልም አበባዎቹ በማቀዝቀዣ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የሚጓጓዙት አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ በሚውሉ ፕላስቲኮች ተጠቅልለው በአውሮፕላኖች ይላካሉ። እንዳይበላሹ በማለትም ብዙውን ጊዜ በመርዛማ ስፖንጆች ላይ ይደረደራሉ።

ኬንያ ከ40 በመቶ በላይ የሚሆነውን አበባዋን ለአውሮፓ ገበያ ታቀርባለች። አብዛኞቹ አበባዎች የአውሮፓ የአበባ ኢንዱስትሪ ማዕከል ወደ ሆነችው ኔዘርላንድስ ይላካሉ።

አበቦች በየቀኑ በአውሮፕላን ይላካሉ። አልስሜር ከተማ ወደሚገኘው ግዙፉ እና ማራኪው የአበባ ገበያ ቀርበው ከተሸጡ በኋላ በመላው አውሮፓ ይሠራጫሉ።

የጭነት መኪናዎችም ሆኑ ጎብኚዎች አበባ ይዘው ሲንቀሳቀሱ መመልከት አዲስ አይሆንም።

በመላው አውሮፓ በሚገኙ ሱፐርማርኬቶች እና የአበባ ሱቆች ውስጥ አበባውን በርካሽ የሚገዙ ሸማቾች እንደ አን እና ማርጋሬት ያሉ ሠራተኞች ያሳለፉትን ድካም አይሰሙም።

ብቻዋን ልጇን ለቁም ነገር ለማብቃት ለምትፍጨረጨረው አን በአበባ ኢንዱስትሪው ውስጥ ከመሥራት ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላት ይሰማታል። ናይቫሻ ውስጥ ያሉት የሥራ ዕድሎች ጥቂት ናቸው። ሥራውን ካጣች ያለምንም ገቢ እንዳትቀር ትፈራለች።

“እግዚአብሔር ከረዳኝ ይህንንም አልፋለሁ” ትላለች አን።