የሱዳኑ ክለብ ከጊዮርጊስ ጋር ያለው ግጥሚያ ከኢትዮጵያ ውጪ ይሁንልኝ አለ

የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ደጋፊዎች

የፎቶው ባለመብት, Saint George S.A

የምስሉ መግለጫ, የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ደጋፊዎች

የሱዳኑ እግር ኳስ ክለብ ከኢትዮጵያው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚያደርገው የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ከኢትዮጵያ ውጪ ይሁንልኝ ሲል ካፍን ጠየቀ።

አል-ሂላል ኦምዱርማን እግር ኳስ ክለብ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ሊደረግ የታሰበው ውድድር ከኢትዮጵያ ውጪ እንዲሆን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንን (ካፍ) የጠየቀው በደኅንነት ስጋት ነው።

በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ዳግም ማገርሸቱ የደኅንነት ስጋት እንዳሳደረበት ክለቡ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ የገለጸ ሲሆን ካፍም ለጥያቄው ምላሽ እንደሚሰጠኝ ተስፋ አለኝ ብሏል።

ከአንድ ሳምንት ገደማ በፊት ለወራት ከዘለቀ ውጥረት በኋላ የሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በእርስ ጦርነት ለሦስተኛ ዙር ዳግም መቀስቀሱ ይታወሳል።

ምንም እንኳ የሱዳኑ ክለብ የደኅንነት ስጋት ስላለብኝ ጨዋታው ከኢትዮጵያ ውጪ ይሁን ብሎ ይጠይቅ እንጂ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን በቀለ በባህር ዳር ጨዋታ ለማድረግ ምንም አይነት የደኅንነት ስጋት የለም ብለዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው በሱዳኑ ክለብ የቀረበው ጥያቄ በይፋዊ መንገድ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የደረሰው ነገር እንደሌለ ከገለጹ በኋላ፤ መስከረም 1/2015 ዓ.ም. ለማድረግ ከታቀደው ጨዋታ ጋር በተያያዘ ምንም አይነት የደኅንነት ስጋት የለም ብለዋል።

“ኤልሜሪክ የተባለው የሱዳን ክለብ ከጂቡቲ ክለብ ጋር ያለው የመልስ ጨዋታ በባህር ዳር ስታዲየም እንዲደረግለት እየጠየቀ ያለው” ካሉ በኋላ ጨዋታውን ለማካሄድ ምንም አይነት የደኅንነት ስጋት እንደሌለ ተናግረዋል።

ከአገር ውጪ የሚጫወቱ ኢትዮጵያን ተጫዋችን ለብሔራዊ ቡድን በመመልመል የሚታወቁት ፋርሃን ሞሐመድ ደግሞ የሱዳኑ ክለብ ይህን ጥያቄ ለካፍ ያቀረበው በኢትዮጵያ መጫወት ስላልፈለገ እንጂ በትክክል የደኅንነት ስጋት ኖሮበት አይደለም ብለዋል።

“ግብጾች ከዚህ ቀደም እንዳደረጉት በኢትዮጵያ ላለመጫወት ፍላጎት ስለሌላቸው እንጂ ትክክለኛ ስጋት ኖሯቸው አይደለም” ብለዋል።

በተመሳሳይ ፋርሃን ከአል-ሂላል ጋር የአንድ ከተማ ክለብ የሆነው አልሜሪክ ከጂቡቲው ክለብ ጋር ግጥሚያውን በጂቡቲ ካደረገ በኋላ በሜዳው ማድረግ የነበረበትን የመልስ ጨዋታውን በባህር ዳር ስታዲየም ለማድረግ ጥያቄ ማቅረቡን ተናግረው የአል-ሂላል ክለብ ጥያቄ ምክንያታዊ እንዳልሆነ ያስረዳሉ።

ፋርሃን ሞሐመድ ለክለቡ ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል ብዬ አልጠብቅም ብለዋል።

የባለፈው ዓመት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ በካፍ ቻምፒዮንሲ ሊግ ተሳታፊ ሲሆን፤ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ፋሲል ከነማ ደግሞ አፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ውድድር ተሳታፊ ነው።