አርሴናልን መሪነቱን ሲያጠናክር ሳውዝሃምፕተን ግርጌ ላይ ተቀመጠ

በኳታር የዓለም ዋንጫ ለ 40 ቀናት ያህል ተቋርጦ የነበረው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በቦክሲንግ ዴይ ጨዋታዎች ተመልሷል።
ሰኞ ምሽት በተደረጉ ሰባት ጨዋታዎች 25 ጎሎች ተቆጥረዋል።
አርሴናል መሪነቱን ያጠናከረበትን ድል ዌስት ሃም ላይ አስመዝግቧል።
ሳውዝሃምፕተን በሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል።
የዕለቱን ዋና ዋና ጨዋታዎች እንደሚከተለው ቃኝተናቸዋል።
በዓለም ዋንጫው ያልደበዘዙት መድፈኞች
ሊጉ በዓለም ዋንጫው መቋረጡ የአርሴናልን ጠንካራ ጉዞ ሊያስቆም ይችላል የሚለው ግምት አንዳልተሳካ ትላንት ምሽት ታይቷል።
የሚኬል አርቴታ ተጫዋቾች ከመመራት ተነስተው ዌስትሃምን ማሸነፍ ችለዋል።
የመድፈኞቹን ጎሎች ቡካዮ ሳካ፣ ጋብርኤል ማርቲኔሊ እና ኤዲ ንኪታ አስቆጥረዋል።
“አንድ ጎል ካስቆጠርን በኋላ የስታዲሙን ድባብ ስንጋራ ነበር። ከደጋፊዎች ድንቅ ውህደት አለን” ሲል ንኪታ ተናግሯል።
አርሴናል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ኒውካስል በሰባት ነጥብ ለመራቅ ችሏል።

ኒውካስል ትክክለኛ ተፎካካሪ ነው
ሌስተርን ያሽነፈው ኒውካስል ቢያንስ ማንቸስተር ረቡዕ ዕለት እስኪጫወት ድረስ የሁለተኝነቱን ደረጃ ይዘው ይቆያሉ።
ኒውካስል በ32 ደቂቃዎች ውስጥ ነው 3 ለ 0 መምራት የቻለው። ክሪስ ዉድ፣ ሚጉዌል አለሚሮን እና ጆይሊንተን ደግሞ ኳስ እና መረብ አሳርፈዋል።
የቡድኑ ደጋፊዎች “የሊጉን ዋንጫ እናነሳለን” እያሉ ሲዘምሩ አምሽተዋል። አሰልጣኝ ኤዲ ሆዊም ተመሳሳይ ሃሳብ አላቸው?
“ምንም ነገር ማድረግ እንችላለን። ውድድር ዓመቱ ገና በመሆኑ ሁሉንም ነገር ማድረግ ይቻላል” ብለዋል።
ለአዳዲስ አሰልጣኞች ድብልቅልቅ ያለው ምሽት
አዳዲስ አሰልጣኞች አሻራቸውን ለማሳረፍ ጥረት እያደረጉ ነው። ጁሊየን ሎፕቴጉ፣ ናታን ጆንስ እና ኡናይ ኤምሬ አዲስ ተሿሚዎች ናቸው።
ሎፕቴጉ አስደናቂ ጅማሮ አድርገዋል። በኤቨርተን ከመመራት ተነስተው በተጨማሪ ሰዓት ባስቆጠሩት ጎል 2 ለ 1 አሸንፈዋል።
ድሉ ቡድናቸውን ከደረጃ ግርጌ ወደ 18ኛ ከፍ እንዲል አስችሏቸዋል።
ናታን ጆንስ ሳውዝሃምፕተንን እየመሩ ወደ ብራይተን ቢያቀኑም 3 ለ 0 መሸነፍ እና ከደጋፊዎች ተቃውሞ ነው የገጠማቸው።
ቡድኑ ላለመውረድ የሚያደርገው ጥረት ይበልጥ ፈተና ውስጥ ገብቷል።
ኤምሬም በቪላ አሰልጣኝነታቸው በሊጉ የመጀመሪኣውን ሽንፈት በሊቨርፑል አስተናግደዋል።
ጫና የበዛበት ላምፓርድ
ላምፓርድ ኤቨርተን ማሸነፍ ነበረበት ቢልም ቡድኑ ላለመውረድ ትግል ውስጥ ገብቷል።
የቀድሞው የዌስት ሃም አጥቂ ካርተን ኮል “ለላምፓርድ አዝናለሁ። ከዚህ ቡድን የሚፈልገውን ያውቃል” ሲል ለፋይናል ስኮር ተናግሯል።
“አንዳንድ ነገሮችን ማስተካከል እና የተረጋጋ አማካይ ሊሠራ ይገባል። ከዚያ ጎሎችን ያስቆጥራሉ። የሚያገኙትን የጎል ዕድል እየተጠቀሙበት አይደለም። ይህ ነው የምርጥ አጥቂ መለያ” ብሏል።
ላምፓርድ ከዚህ በኋላ ተከታታይ ሁለት ሽንፈት ካስተናገደ በኤቨርተን ያለው ቆይታ ያበቃል ያለው የቀድሞው እንግሊዝ አጥቂ ዲዮን ደብሊን ነው።
ድንቅ አጀማመር
ከዓለም ዋንጫ በኋላ በተደረገው የሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ብሬንትፎርድ እና ቶተንሃም ሁለት አቻ በመለያየት በድንቅ ሁኔታ ሊጉን አስጀምረዋል።
ቪታሊ ያኔልት እና ኢቫን ቶኒ ብሬንትፎርድን ቀዳሚ አደረጉ። ሃሪ ኬን ቶተንሃምን ወደ ጨዋታው የመለሰች ጎል አስቆጠረ።
ፒዬር-ኤሚል ሆቢየርግ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ቶተንሃምን አቻ አደረገ።
“ሊጉን ያስጀመረ ምርጥ ጨዋታ” ሲሉ የብሬንትፎርዱ አሰልጣኝ ቶማስ ፍራንክ ተናግረዋል። የቶተንሃሙ አንቶኒዮ ኮንቴ በበኩላቸው “አስደሳች ጨዋታ” ሲሉ ገልጸውታል።
የቪዲዮ ዳኝነትስ? ሰኞ ምሽት ቴክኖሎጂው እንዴት ተተገበረ?
አዲሱ የፕሪሚየር ሊግ ዳኞች አለቃ ሃዋርድ ዌብ የዳኝነት ስርዓቱን እና የቪዲዮ ዳኝነት (ቫር) እንደሚያሻሽሉት ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
አርሴናል እና ዌስት ሃም ባደረጉት የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ዊሊያም ሳሊባ በፈጸመው ጥፋት የመሃል ዳኛው ማእክል ኦሊቨር ፍጹም ቅጣት ምት ሰጡ። ሳይድ ቤንርሃማ ዕድሉን ተጠቀመበት።
በኋላም አሮን ክሮስዌል በእጅ ኳስ ነክቷል በሚል ፍጹም ቅጣት ምት ተማክረው እና ቪዲዮውን ተመልክተው ሽረውታል።
በትክክልም ኳሷ የዌስት ሃሙን ተከላካይ ፊት ነበር የመታችው።












