የአሜሪካ እና ኢራን ድርድር "ተጨባጭ ለውጥ" ማሳየቱን አደራዳሪዎች ተናገሩ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ እና የኢራን ባለሥልጣናት በጄኔቫ ባካሄዱት ድርድር "ተጨባጭ ለውጦች" መታየታቸውን የኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ።

አደራዳሪው ጦርነትን የሚያስቀር ስምምነት የመድረሱ ዕድል ግን አሁንም ግልጽ አይደለም ብለዋል።

ሁለቱ ወገኖች ባደረጉት ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይት አደራዳሪ የነበሩት የኦማን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አልቡሳዲ፣ አሜሪካ እና ኢራን ተደራዳሪዎች ከመሪዎቻቸው ጋር ከተመካከሩ በኋላ ንግግራቸውን "በቅርቡ" ለመቀጠል መወሰናቸውን እና በሚቀጥለው ሳምንት በቪየና የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ ውይይቶች እንደሚካሄዱ ተናግረዋል።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ "ጥሩ ዕድገት" መታየቱን ተናግረው በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ቢኖርም፣ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ግን አሁንም ልዩነቶች መኖራቸው ተነግሯል።

የሚቀጥለው ድርድር ከአንድ ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል ተጨማሪ ውይይቶች መካሄዳቸው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጥቃት ለመፈጸም ያሰሙትን ማስጠንቀቂያ ተግባራዊ የማድረግ ዕድላቸውን ሊቀንስ ይችላል።

ትራምፕ እአአ በ2003 አሜሪካ ኢራቅን ከወረረች ወዲህ በመካከለኛው ምሥራቅ ትልቁን ወታደራዊ ኃይል እንዲሰማራ አዝዘዋል።

ኢራን በበኩሏ ጥቃት የሚፈጸምባት ከሆነ ምላሽ እንደምትሰጥ አስጠንቅቃለች።

አሜሪካ እና እስራኤል ለብዙ አስርት ዓመታት ኢራን በድብቅ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ለማምረት እየሞከረች ነው ሲሉ ሲከሱ ቆይተዋል።

ኢራን ምንም እንኳን አገሪቱ ጦር መሳሪያ ለማምረት ብቁየሆነ ዩራኒየምን ብታበለጽግም በተደጋጋሚ ይህን አስተባብላ የኒውክሌር ፕሮግራሟ ለሰላማዊ ዓላማ ብቻ የሚውል እንደሆነ ትገልጻለች።

የኢራን የመንግሥት ሚዲያ እንደዘገበው፣ ተደራዳሪዎቹ ኢራን ሰላማዊ የኒውክሌር ኃይል የመገንባት መብት እንዳላት አጥብቀው በመግለጽ፣ አሜሪካን ዩራኒየም ሙሉ በሙሉ እንዳታበለጽግ ያቀረበችውን ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል።

ከዚህም ባሻገር 400 ኪ.ግ የበለፀገ የዩራኒየም ክምችት ከአገሪቱ እንዲወጣ አሜሪካ ያቀረበችውን ትያቄም ውድቅ ማድረጋቸውም መገናኛ ብዙላኑ ዘግበዋል።

ነገር ግን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ምንም እንኳን ሀሳቦቹ ይፋ ባይሆኑም የመግባቢያ ሃሳብ ለአሜሪካ አቅርበዋል ተብሎ እታመናል።

ከተዘገቡት አማራጮች አንዱ ኢራን ከሥስት እስከ አምስት ዓመታት የሚቆይ እገዳ ከተጣለባት በኋላ ዩራኒየምን በዝቅተኛ ደረጃ እንድታበለጽግ መፍቀድ ሲሆን ይህም በዓለም አቀፉ የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ክትትል ስር የሚሆን ነው።

አራግቺ ለኢራን ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ድርድሩ የኢራንን ኢኮኖሚ ያዳከመውን ማዕቀብ እንዲነሳላቸው ጠይቀዋል።

የአገዛዙ ተቃዋሚዎች ማንኛውም እፎይታ ለኢራን አብዮታዊ መሪ ሥልጣንን የሚያራዝም ነው ሲሉ ይኮንናሉ።