"ሊቢያ ውስጥ በርካታ ስቃይ ባሳልፍም፤ በአይኤስ የተቀጠፉትን ወንድሞቼን በፍጹም አልረሳም" ዳንኤል አብርሃ

የንባብ ጊዜ: 8 ደቂቃ

ባለፈው ሳምንት "ሃያ ሦስት" የተሰኘ መጽሐፍ ተመርቆ ለንባብ በቅቷል። መጽሐፉ ከአዲስ አበባ ተነስቶ በሱዳን፣ በሊቢያ አድርጎ ወደ አውሮፓ የተሻገረ ወጣት የስቃይ እና የስኬት ታሪክ ነው።

ይህ መጽሐፍ የ'አሉ፣ ተባለ' ታሪክ አይደለም። እውነታውን ከፈረሱ አፍ የሚሰማበት መጽሐፍ ነው።

ዳንኤል አብርሃ ታሪኩን ሲጽፈው ቢኒያም አቡራ ደግሞ የአርትዖት እና የማሰናኘት ድርሻውን ተወጥቷል።

ይህ 262 ገጾች ያሉት የዳንኤል የስደት ታሪክ ከሊቢያ እስር ቤት፣ ከአይኤስአይኤስ ጭፍጨፋ፣ ከጀልባ መገልበጥ የሚያመልጥባቸውን አጋጣሚዎች የያዘ ነው።

ዳንኤል አዲስ አበባን ለቅቆ ሲሄድ እንደማንኛውም ስደተኛ ፖለቲካዊ ጥያቄ ኖሮት ወይንም ኢኮኖሚያዊ ምክንያት አንግቦ አልነበረም።

እናቱን በልጅነቱ ያጣው እና በአሳዳጊዎች ቤት ያደገው ዳንኤል፣ አባቱን የመፈለግ ጥያቄ በልቡ አዝሎ ነው ለስደት እግሩን ያነሳው።

የዳንኤል ስደት ጉዞ በዓለም ላይ ካሉት አደገኛ የስደት መስመሮች መካከል በአንዱ የተካሄደ ነው።

ከአዲስ አበባ ባሕር ዳር ወደ ድንበር ከተማዋ መተማ ከዚያም ወደ ሱዳን እና ሊቢያ መጓዝ ቀዳሚው ምዕራፍ ነበር።

በመንገዱ ላይ ከጨካኞች የሰው አዘዋዋሪዎች ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቷል፣ ረሃብ እና በሽታ የማያቋርጥ አጋር በሆኑበት መጋዘን ውስጥ ታስሮ ተርፏል።

ከሰላሳ በላይ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ወገኖቹ በታጠቁ ቡድኖች ሲገደሉ በቅርብ ርቀት ሆኖ ዜናውን ሰምቷል።

ተርቦ፣ ታሞ፣ ተደብድቦ በሕይወት ተርፎ የሜዲትራኒያን ባሕርን በጀልባ ተሻግሯል።

የዳንኤል የስደት መንገድ አውሮፓ ከደረሰም በኋላ በቶሎ አልተቋጨም። በጣሊያን፣ በጀርመን እና በቤልጂየም አቋርጦ በመጨረሻ ዩናይትድ ኪንግደም ከትሟል።

ዛሬ በትልቅ ሬስቶራንት ውስጥ የሚሠራ የሰለጠነ የምግብ ባለሙያ ሲሆን፣ ትምህርቱን ተከታትሎ ለመመረቅ በቅቷል።

ዳንኤል ከአዲስ አበባ ተነስቶ የሜዲትራኒያን ባሕርን እስኪሻገር ድረስ አምስት ወር ያህል ፈጅቶበታል፤ የተለያዩ ደላሎች ተፈራርቀውበታል።

የተቀበለውን ገንዘብ የሚክድ፣ ለሌላ አዘዋዋሪ የሚሸጥ፣ ምግብ በመንፈግ የሚቀጣ፣ ወጠምሻ ቀጥሮ የሚያስገርፍ ደላላ በዓይነት በዓይነቱ ያለባት፣ የጥይት ድምጽ ሙዚቃ በሆነባት ሊቢያ በተስፋ ማጣት እና በችግር ብዙ አሳልፏል።

'ጎጆ ተሰደጂ'

ዳንኤል የመጀመርያ የስደት ጉዞውን ሲያስታውስ "ከኢትዮጵያ ብቻዬን ነው የወጣሁት። ብቻዬን የምሰደድ ዓይነት ስሜትም ተሰምቶኝ ነበር። ለካ ሰዉ እየተሰደደ ነው ያልኩት መተማ ስደርስ ነው። ሰዉ በተናጠልም፤ በቡድንም ይጎርፋል" ይላል።

ከአዲስ አበባ ጥቂት ገንዘብ እና የሚለብሳቸውን ጨርቆች ሸክፎ ብቻውን የወጣው ዳንኤል፣ መተማ እስኪደርስ ድረስ ብቻውን የነበረ ቢሆንም በሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ውስጥ፣ ከአገር ለመውጣት እንደርሱ ጉዞ የጀመሩ ወጣቶችን ተመልክቶ ወዛቸው ከተሰራበት አፈር፣ ህዋሳቸው ከተበጀበት ትቢያ ተነቅለው የሚተምሙ የሰው ጅረቶች አስደንቀውታል።

ስደተኛ መንገዱ ይመሳሰል እንጂ ጥያቄው ግን ቡራቡሬ ነው። የተወሰነው ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ያነሳል። ሠርቶ የመለወጥ ፍላጎቱን ያስቀድማል።

የተወሰኑት ደግሞ ፖለቲካዊ ቅራኔ ኖሯቸው ከእስራት እና ከእንግልት ለመሸሽ ስደትን ይመርጣሉ።

ዳንኤል ግን ከእነዚህ ሁሉ በተለየ አባቱን ለመፈለግ ነው የወጣው። በመጽሐፉ ገጽ 67 ላይም ይህ ሃሳብ እንዲህ ሰፍሯል።

". . . እኔ ከተሰደድኩ ቆየሁ። አካሌ ነው መጻተኛ ያልኾነው፤ መንፈሴ ግዞተኛ ከኾነ ሰነባብቷል። ወላጅ እናቴ በልጅነቴ እንደሞተች እና አባቴም እንድ ልጁን ማሳደግ እንደማይፈልግ ካወቅኩ ጀምሮ ነፍሴ አልሰከነችም። አንዳንዴ ክፉ ሰዎች ቦታዬን ካሳዩኝ እና ጥያቄ መጠየቅ ከጀመርኩ ጀምሮ ነፍሴ በስደት ላይ ነች። ነበረች … ሰው ማየት የሚችለው አካሌን ነውና አሁን ገና ስደት የወጣሁ ይመስለዋል … እውነታው ግን ስደት ከወጣሁ ብዘ ዓመታትን አስቆጥሬያለሁ። . . . "

ዳንኤል አባቴ ኤርትራዊ ነው፤ ግን "የት እንዳለ አላውቅም" ሲል ከቢቢሲ ጋር ቃለ ምልልስ ባደረገበት ወቅት ተናግሯል።

". . . የቤተሰብ፣ የማንነት ጥያቄ ውስጥ ስለወደቅኩ ሽሽት ላይ ነበርኩ። በአሳዳጊዎች ነው ያደግኩት። አባቴ የት እንዳለ፣ በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳለ አላውቅም። እና እርሱን መፈለግ እና ሽሽት ውስጥ ነበርኩ።"

ዳንኤል ለስደት የወጣበትን ምክንያት ማንነትን ፍለጋ ሽሽት ማለት ይመርጣል።

"'አባትህ አይፈልግህም' የሚለው ንግግር የትም ይሁን የትም መሄድ መሸሽ አባትህን መፈለግ ያስመኝሃል፤ ራስህን የማቆም ደግሞ ሌላ ብርቱ ጥያቄ አለ። ራስህን በሁለት እግር ስታቆም ነው አባትህንም ቤተሰብህንም የምትፈልገው እና የብዙ ምክንያቶች ጥርቅም ነው ወደ ስደት እንድወጣ ያደረገኝ።"

የስደት መንታ መልኮች

ዳንኤል በስደት ውስጥ መተሳሰብን፣ ፍቅርን ብቻ ሳይሆን ጭካኔንም ተመልክቷል።

በሕመም፣ በረሃብ ወቅት መተሳሰብ እና መተዛዘን እንዳለ ሁሉ፤ በሌላ ወቅት ደግሞ የራስን ነፍስ ብቻ ለማትረፍ ሌላውን ጨፍልቆ ማለፍን በሊቢያ በረሃ ውስጥ በጉልህ ተመልክቷል።

"አንዳንዴ ራስን ለማዳን አንዱ አንዱን ረግጦ የሚያልፍበት አጋጣሚ አለ። በተለይ ባሕር ላይ በነበርንበት ወቅት የጫነን ጀልባ ሚዛኑን መጠበቅ ሳይችል ሲቀር ስደተኛው የራሱን ነፍስ ለማዳን ሴትም ሕጻንም ምንም የማይመስለው ጊዜ አለ።"

ዳንኤል በሊቢያ በነበረባቸው ጊዜያት ውስጥ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያን፣ ሶማሊያውያን ሱዳናውያን፣ ቻዳውያንን ተመልክቷል።

እነዚህ ሁሉ ስደተኞች ከየትኛውም አገር ጫፍ ይምጡ፣ ከየትኛውም ከተማ ይፍለሱ የሚያመሳስሏቸው ነገሮች መኖራቸውን አስተውሏል። ሁሉም ከአገራቸው ከወጡ በኋላ 'ቢጭኗቸው አህያ፣ ቢጋልቧቸው ፈረስ' ሆነው ቀናቸውን ፈቅ ለማድረግ አንገታቸውን ደፍተዋል፤ አፋቸውን ሸብበዋል።

ስደት ሁሉንም እንደ አግዳሚ ወንበር እኩል ወደ ጎን ደርድሮ ያስቀምጣል። ከኢትዮጵያ ነው ከሶማሊያ፣ መምህር እና ወታደር፣ ምሁርና መሃይም፣ ከሱዳን ነው ከኤርትራ ሁሉንም እኩል ያሰቀምጣል።

"ስደት ለሁሉም እኩል ነው። ከአገርህ ከቀየህ ከወጣህ የሚገጥምህ ተግዳሮት የምታልፍበት ውጣ ውረድ ተመሳሳይ ነው። ለአገሬውም ፀጉረ ልውጥ ነህ። በቆዳ ቀለምም ነጣ ብትልም ጠቆር ብትልም የስደትን መልክ አትቀይረውም።"

በዚህ ጊዜ ውስጥ የስደተኛን የነገ ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ፣ መልኩን የሚያጠይሙ ወይንም የሚያደፈርሱት ደግሞ የሰው አዘዋዋሪዎች ናቸው።

ዳንኤል እንደሚለው በከፍተኛ ሁኔታ የስደተኞችን ቁጥር የሚመሩት ኤርትራውያን ናቸው ይላል። ከዚያ ሶማሊያውያን፣ በመቀጠል ቻዶች እንዲሁም ሱዳናውያን እና ኢትዮጵያውያን ይቀጥላሉ።

ዳንኤል መጽሐፉ ላይ ሊቢያ መርከብ ላይ ሲጫኑም በዚሁ ቅደም ተከተላቸው መሆኑን አስፍሯል።

ቅድሚያ የሚሰጠው "በሥራቸው ብዙ ስደተኛ ላላቸው ትላልቅ ደላሎች ነው።"

ከዚህ በተጨማሪም ዳንኤል በመጽሐፉ ላይ ስለሱዳናውያን ደላሎች በጎ ነገሮችን አስፍሮ እናነባለን።

ይህ ለምን እንደሆነ ቢቢሲ ሲጠይቀው መጽሐፉ ከእውነት አና ከሕይወት ቅስም መጠለሉን ይናገራል።

"እኔ የጻፍኩት ያየሁትን፤ ያጋጠመኝን እውነቴን ነው። እንግዲህ በወቅቱ እነዚያ ጥሩ ሰዎች፣ ጥሩ ደላሎች ሆነው ነው እንጂ የሱዳናውያንም ክፉ ሰዎች አሉ። መጋዘን ውስጥ በነበርኩበት ሰዓት፣ ጓንታናሞ የሚባለው ውሰጥ ሊቢያኖች የሚቀጥሯቸው ገራፊዎች ሱዳናውያን ነበሩ። እኔ ግን የገጠሙኝ ደግ ስለሆኑ ነው።"

ዳንኤል የሜዲትራኒያን ባሕርን ለመሻገር ጀልባ የሚሳፈርበት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ሆኖ ገንዘብ የከፈለው ሱዳናዊ ደላላ ግማሹን ቀንሶበት ተቸግሯል።

በዚህ ወቅት ደግሞ "ምህረት አድርጎ እንድሻገር ያደረገኝ ደላላ ሊቢያዊ ነው" ነው ሲል የነበረውን ዥንጉርጉር መልክ ያስረዳል።

ለመጽሐፉ አርትኦት የሠራው ቢኒያም አቡራ በበኩሉ ከአዲስ አበባ - ባሕርዳር፣ ከባሕርዳር - መተማ፣ ከመተማ - ሱዳን፣ ከሱዳን - ሊቢያ ለመድረስ የፈጀውን ጊዜ ሁለት ሳምንት ብቻ የወሰደ መሆኑን በማስታወስ የስደትን ሕይወት በጥድፊያ እና ውክቢያ የተሞላ መሆኑን ያሳያል።

". . . [ይህ የዳንኤል መጽሐፍ] እውነተኛ ታሪክ ባይኾን ኖሮ ኢ-ተአማኒ ጥድፊያ" በመባል ይተች እንደነበር የሚገልጸው ቢኒያም፤ "የሰው አዘዋዋሪዎች፣ የስደተኞቹን መቆየትን የመፈለግ መብት ጥሰው በአንዲት ቀን ሰሀራ በረሀ ላይ መጣላቸው" የስደተኞቹን ሕይወት በዚህ መልክ ለመበየኑ አስተዋጽኦ ማድረጉን ይናገራል።

'አበቃልኝ ያልኩባቸው ሰዓታት'

ዳንኤል ከ11 ዓመት በፊት ራሱን "እስላማዊ መንግሥት" ብሎ የሚጠራው ቡድን 34 ኢትዮጵያውያንን እና ኤርትራውያንን በሊቢያ በረሃ በጥይት ሲገድል፣ አንገታቸውን ሲቀላ እርሱ በአጅዳቢያ መጋዘን ውስጥ እስረኛ ነበር።

በወቅቱ በዚህ መጋዘን ውስጥ ከታጎረ ከሁለት ወር በላይ ሆኖታል። ይህ የሆነበት ምክንያትም የተወሰኑ ስደተኞች እና እርሱ ክፍያቸውን ባለማጠናቀቃቸው እንዲጓዙ ባለመፈቀዱ ነው።

ከአጅዳቢያ እስከ ትራብልስ ለመጓዝ ከሠላሳ በላይ ኬላ ማለፍ ግድ መሆኑን ዳንኤል በመጽሐፉ ላይ አስፍሯል። እነዚህን ኬላዎች ለማለፍ ደግሞ አደገኛ ስለሆነ ደላሎቹ ስደተኞቹን ይዘው ለመሄድ የሚመርጡት በበረሃው ነው።

ከዳንኤል ጋር በመጋዘኑ ውስጥ የነበሩ እና ክፍያቸውን ያጠናቀቁ የጨርቆስ ልጆች በመኪና ተጭነው ጉዟቸውን ጀመሩ።

እነዚህ ስደተኞች ግን እንዳሰቡት ወደ ሊቢያዋ ዋና ከተማ ትሪፖሊ አልደረሱም። በመሃል አይኤስአይኤስ እጅ ላይ ወድቀው ተገድለዋል።

ከእነዚህ ሟቾች መካከል የተወሰኑት ዳንኤል ከነበረበት መጋዘን ውስጥ አብረውት ነበሩ።

በወቅቱ በማኅበራዊ ድረ ገፆች የተሰራጨ ቪዲዮ የቡድኑ ታጣቂዎች ብርቱካናማ መለዮ የለበሱ ሰዎችን በጥይት ደብድበው ሲገድሉ እና አንገታቸውን በስለት ሲቀሉ አሳይቶ ነበር።

ዳንኤል በመጽሐፉ ላይ ሁኔታውን ሲያስታውስ "ከቲቪው ጋር ተፋጠጥን. . . ከአንድ ሳምንት በፊት አብረውን የበሉ. . . አብረውን የጠጡ . . .አብረውን መኝታ የተጋሩ እነ ሄብሮን ናቸው። ሦስቱን አየኋቸው ተመሳሳይ ቱታ ለብሰዋል። እጃቸው ወደ ኋላ ታስሯል። በሸላቾች ፊት እንደሚታረድ በግ ዝም ብለዋል። የተንበረከኩት ከአይ-ኤስ-አይ-ኤስ ታጣቂዎች ዘንድ እንደኾነ ለማወቅ በዚህ ሰዓት አጋዥ አላስፈለገኝም። አንድ በአንድ በታጣቂዎቹ ሲታረዱ ተመለከትኩኝ። ዞረብኝ።"

ዳንኤል በሊቢያ ውስጥ አለቀልኝ ከዚህ በኋላ ምንም ተስፋ የለኝም ያለባቸው አጋጣሚዎች መካከል አንዱ የእነዚህ ወጣቶች ግድያ ነው።

"አብረውኝ የነበሩ፤ አብረውኝ የተኙ፤ አብረውኝ ያደሩ፤ አብረውኝ የተራቡ ልጆች ሲታረዱ እኔም በቃ አብቅቶልኛል የመጨረሻዬ ነው ብዬ ተስፋ ቆርጬ ነበር።"

ይህ ብቻም ሳይሆን ከዚያ ደግሞ ወደ ሜዲትራኒያን ባሕር መሻገሪያው አካባቢ ተቃርቦ በነበረበት ወቅት "በጣም በሕመም ስሰቃይ የምሞት መስሎኝ የሕይወት ትርጉም ጠፍቶኝ፤ ሞት ናፍቆኝ ተስፋ ቆርጬ ነበር" ይላል።

ሊቢያ ውስጥ ከገጠሙኝ ራሴን የጠላሁባቸው፣ ራሴን እና ፈጣሪዬን አማርሬ የወቀስኩባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ የሚለው ዳንኤል "ትልቁን ቦታ የሚይዘው ግን ወንድሞቻችንን በአይኤስአይኤስ ያጣንበት ነው።"

የመጽሐፉ ርዕስ ለምን ሃያ ሦስት ተባለ?

የመጽሐፉን አርትኦት የሠራው ቢኒያም አቡራ እና ባለታሪኩ ዳንኤል መጽሐፉን ለምን ሃያ ሦስት ለማለት እንደወሰኑ ሲያስረዱ "ዳንኤል ከአዲስ አበባ የተነሳው ጥር 23 ነው" በማለት ነው።

በሊቢያ በረሃም ስደተኞቹ ፒካፕ መኪና ላይ ይጫኑ የነበሩት ሃያ ሦስት፣ ሃያ ሦስት እየሆኑ እንደነበር በመጽሐፉ ላይ ተገልጿል።

በሰዓቱ ለስደት የወጡ የጨርቆስ ልጆች አብዛኞቹ ዕድሜያቸው ከ23 ዓመት በታች ነበሩ የሚለው ቢኒያም፣ "የ 23 ቁጥር ትእምርታዊ (symbolic) ትርጓሜው ከዕጣ ፈንታ ጋር፣ ራስን ከመፈለግ ጋር፣ ከፈጣሪ እረኝነት ጋር ይቆራኛል" ሲል ያብራራል።

እነዚህ ደግሞ "መጽሐፋችን ውስጥ በዋነኝነት የሚንጸባረቁ ነገሮች ናቸው" በማለት መጽሐፉን ለምን 23 ማለት አንደመረጡ ያስረዳሉ።

የማያባራው የሊቢያ የስደት መንገድ

ዳንኤል "ስደት ለየትኛውም ሰው የሚመከር አይደለም" ካለ በኋላ፣ ነገር ግን "ሰው ማጣፊያ ሳያጥረው ወደ ስደት አይወጣም" ይላል።

በተለያየ መንገድ ከአገር ወጥተው ኑሯቸውን በአውሮፓ እና አሜሪካ ያደረጉ ሰዎች ግን ስለስደት ታሪካቸው ሲናገሩ "መሃሉን አያሳዩህም" የሚለው ዳንኤል፤ "የስደት ዳር ዳሩ የፀደይ አበባ መሃሉ ግን እሳት፣ ስቃይ፣ ረሃብ አለው።"

ያኔ በወቅቱ አማራጮች በመጥፋታቸው የሊቢያን የስደት መንገድ መምረጡን የሚያስታውሰው ዳንኤል "አሁን ግን ከአገር ወጥቶ ራሱን ለመቀየር ለሚፈልግ ሰው በርካታ አማራጮች አሉ" ሲል ያብራራል።

አሁን ግን ሊቢያን መርጦ ለስደት እግሩን የሚያነሳ ሰው በገንዘብም፣ በአካላዊ ስቃይም የበለጠ ዋጋ እንደሚከፍል የሚያስረዳው ዳንኤል "ትሸጣለህ፤ ትለወጣለህ፤ አንተ ለየትኛውም ደላላ ገንዘብ ነህ፤ የትኛውም አጋች እያገተ አንተን እየሸጠ እና እየለወጠ እየመነዘረ ሃብቱን ሊያበዛብህ ነው ሚፈልገው" ይላል።

ሊቢያ ውስጥ "አሁን ሁሉም አጋች ሆኗል። ታጣቂውም፣ በመንግሥት ስም የተደራጀውም፣ ተራው ነዋሪም ያግታል። ገንዘብ ይጠይቅሃል" ሲል የሚያብራራው ዳንኤል፣ ስለዚህም የእርሱ መጽሐፍን የሚያነቡ እና የስደት ሃሳብ ያላቸው ሰዎች "ቆም ብለው እንዲያስቡ ያደርጋል ብዬ አስባለሁ" ሲል ተስፋውን ይገልጻል።

ስደትን ሲያስብ ከአእምሮው የማይጠፋ ጠባሳ መኖሩን የሚናገረው ዳንኤል "የደላሎች ጭካኔ፣ የአሸጋጋሪዎች ርህራሄ ማጣት ዘላቂ ጠባሳ ይጥላል" ይላል።

በስደት ዓለም "የምትደገፍበት፤ የምትተማመንበት ሕግም ሆነ ሰው የለም" በማለትም፤ እንደ ሊቢያ ያሉ የስደት መንገዶችን ከመምረጥ በፊት ሌሎች አማራጮችን መመልከት ተገቢ መሆኑን ያስታውሳል።

ታሪክህን ለምን በመጽሐፍ መልክ ማቅረብ ፈለግክ?

በርካቶች በሱዳን፣ በሊቢያ አድርገው ወደ አውሮፓ ተሻግረዋል። ነገር ግን ታሪካቸውን በመጽሐፍ መልክ ያካፈሉት እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው።

ዳንኤል "ይህ ታሪክ የእኔ ታሪክ ብቻ አይደለም። የብዙዎች ቁስል የብዙዎች ሕመም ነው" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

"በአውሮፓም፣ በአሜሪካም ያሉ እና ስደትን ያዩ ሰዎች ይህንን ሕመማቸውን ተሸክመው ተደብቀው እየኖሩ ነው። ብዙ አውርተነዋል፤ ብዙ ግን አልተጻፈም። ተሰንዶ የሚገኝ ብዙ ነገርም የለም።"

ዳንኤል ይህ የእርሱ የስደት ታሪክ በመጽሐፍ መልክ መቅረቡ "ለእኔ ታሪኬ፣ ጥናት እና ምርምር ማካሄድ ለሚፈልጉ፣ የሊቢያን የስደት መንገድ ማወቅ ለሚሹ ደግሞ የሚጠቅም ሰነድ ነው" ሲል የሚኖረውን አበርክቶ ያስረዳል።

መጽሐፉን የሚያነቡም በዝርዝር ያሰፈራቸውን የስደትን ቁስሎች እንዲረዱ፣ እያንዳንዱን የጉዞ እንግልት እንዲመለከቱ እንዲሁም "እውነቴን እንዲገነዘቡ፣ ለስደት ከተነሱም ይህንን አንብበው የሚገጥማቸውን ቀድመው እንዲያውቁት" መሆኑን ይናገራል።

የመጽሐፉ አርታኢ ቢኒያም በበኩሉ በተደራሲው ልብ ውስጥ ታትሞ ቢቀር የሚመኘው ሌላ ነው።

"እነ ዳንኤል አጅዳቢያ መጋዘን ውስጥ በአንድ ሳህን ለአምስት ከሚቃመሷት መኮሮኒ የበለጠ የአንድ ወዳጃቸውን የስልክ ጥሪ ይናፍቃሉ። የዚያ ሁሉ ስደተኛ ምኞት እና ጉጉት 'ተደውሎልሃል' መባል ነው። ዛሬ እኛ 'ውይ ደሞ ደወለብኝ' ብለን የሚያበሳጨን የስልክ ጥሪ የአንዳንዶች የመጨረሻው ምኞታቸው ነው። ተደራሲው ልቦና ላይ ይህ ቢታተም ደስ ይለኛል።"

አክሎም "ስደት፣ የግለሰቦች ከአገር አገር የመቀየር ሁኔታ ብቻ አይደለም" የሚለው ቢኒያም፣ "የየቀኑ ሕይወታችን የስደት ነው። ከእውነት እንሰደዳለን...ከሐቀኝነት እንሰደዳለን... ከማንነታችን እንሰደዳለን...ከሕሊናችን እንሰደዳለን...ከቅንነት እንሰደዳለን... ወዘተ። እናም በመጽሐፉ መጨረሻ ላይ ዳንኤል ያስቀመጠውን 'የስደት ሕይወቴ የሚያበቃው ወደ ትውልድ አገሬ ስመለስ አይደለም፤ ከእውነት ጋር የመኖር አቅም ሲኖረኝ እንጂ' የሚለውን ሐሳብ ተደራሲው ቢያስታውስልኝ ደስ ይለኛል ብሏል።

እኔን "ለታሪክ ለምስክርነት፣ ለእውነት ያስቀመጠኝ ይመስለኛል። ብዙዎች ተገድለዋል፤ ታርደዋል። አውሮፓ ውስጥ ገብተው ያልተሳካላቸው ብዙ ሰዎች ይኖራሉ፣ አሉም" የሚለው ዳንኤል፤ በዚህም የተነሳ ሳያሳካላቸው ቀርተው ተደብቀው የሚኖሩ በርካቶች መሆናቸውን ተናግሯል።

"የስደት ኑሮ በአውሮፓ ሁሌም በስኬት የታጀበ አይደለም" የሚለው ዳንኤል፤ የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ ማጣት፣ ከዚያ ደግሞ ያቀዱት አልሆን ሲላቸው ወደ ሱስ የሚገቡ መኖራቸውን ተመልክቷል።

በርካቶች ከዚህ በኋላ ራሳቸውን እስከማጥፋት ደርሰዋል የሚለው ዳንኤል አብርሃ "እኔ የምለው እነዚህን ሰዎች መረዳት እና መደገፍ ያስፈልጋል ነው" ሲል ሃሳቡን ቋጭቷል።

የመጽሃፉ አርታኢ እና አሰናኝ ቢኒያም በመጽሐፉ ውስጥ የቀረበው የዳንኤል ታሪክ 'የስቃይ እና የእንግልት ወይስ መከራን የማሸነፍ' ብቻ ሳይሆን በውስጡ ብዙ ነገሮችን እንደያዘ ይናገራል።

"የሰው ልጅ ጨለማ በዋጠው እና በውሃ በተሞላ ዋሻ ውስጥ በአንዳች አጋጣሚ ቢገኝ ምን ዓይነት ዋጋ እንደሚከፍል ይህ መጽሐፍ ያሳያል። አብሮ ያላቅሳል፤ ሕመምን ይጋራል። እንዴት መዋኘት እንዳለበት ይጠቁማል። ከቀቢጸ ተስፋ ወደ ጭላንጭል ብርሃን ይመራል። የፈጣሪን ሁነኛ ምርኩዝነት ያሳያል። ተስፋን ያጭራል።"