የመራቢያ አካልን በመውረር መካንነትን ጨምሮ የጤና መቃወስን የሚያስከትሉት ጥገኛ ተውሳኮች

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

እነዚህ ጥገኛ ተውሳኮች በቆዳችን ውስጥ ገብተው ደማችን ውስጥ ይደበቃሉ። ከዚያም እንቁላላቸውን ጉበት፣ ሳንባ እና መራቢያ አካላት ውስጥ በመጣል ቤታቸውን ይሠራሉ። ሳይታወቁ ለዓመታት እዚያው መቆየትም ይችላሉ።

ተመራማሪዎችም ብዙም ትኩረት ያልተሰጠው ከጥገኛ ተውሳክ የሚመጣ 'ስኔል ፊቨር' በሽታን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ በሚሆን መልኩ ሊለወጥ እንደሚችል እያስጠነቀቁ ነው።

በየዓመቱ በበሽታው ከሚያዙ 250 ሚሊዮን ሰዎች መካከል አብዛኞቹ የሚኖሩት የተለዩ ዓይነት ጥገኛ ተውሳኮችን የሚሸከሙ ቀንድ አውጣዎች በሚገኙበት አፍሪካ ውስጥ ነው።

ሆኖም የተውሳኩ ሥርጭት ቻይና፣ ቬንዙዌላ እና ኢንዶኔዥያን ጨምሮ በዓለም በ78 አገራት ውስጥ ተገኝቷል።

አንድ ጥናት በተውሳኩ ላይ ለውጥ መታየቱን እና ወደ ሌሎች ቀጣናዎች ሊስፋፋ እንደሚችል ካመለከተ በኋላ የዓለም ጤና ድርጅት ተውሳኩ "ዓለም አቀፋዊ ስጋት" እንደሆነ ገልጿል።

ተውሳኩን የተመለከተው ማስጠንቀቂያ የተሰማው የጤና ድርጅቱ በዓለም ችላ የተባሉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ቀንን ባከበረበት ወቅት ነው።

የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ቀን በድሃ አገራት የሚኖሩ አንድ ቢሊዮን ሰዎችን የሚያጠቁ እና በቫይረስ፣ በባክቴሪያ፣ በጥገኛ ተውሳኮች እና በፈንገስ የሚመጡ በሽታዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር።

'ስኔል ፊቨር' ምንድን ነው?

'ስኔል ፊቨር' በሽታ የሚከሰተው ሰዎች ወይም እንስሳት የቀንድ አውጣ እጭ (ላርቫ) ያለበትን ውሃ በሚጠጡበት፣ በሚታጠቡበት፣ በሚዋኙበት ወይም በውሃው በሚገለገሉበት ወቅት ነው። በዚህ ጊዜ እጩ ቆዳን የሚሰረስር ኤንዛይሞችን ስለሚያመነጭ በቀላሉ ወደ ሰውነት ውስጥ ይገባል።

ከዚያም እጩ ወደ ትልነት በማደግ በደም ሥሮች ውስጥ ተደላድሎ ይቀመጣል። ትሎቹ ሴቶች ከሆኑ እዚያው እንቁላል ይጥላሉ። እነዚህ እንቁላሎች አንዳንድ ጊዜ በሽንት ወይም በሰገራ አማካኝነት ይወጣሉ።

ሆኖም በሕብረ ሕዋሳት (ቲሹ) ውስጥ ሊቀሩም ይችላሉ። በዚህ ጊዜ የሰውነት በሽታ የመከላከያ ሥርዓት ዝም ብሎ አይቀመጥም። ለእነዚህን ባዕድ እንቁላሎች ምላሽ ይሰጣል። በዚህ ጊዜ ግን በአካባቢው ያሉ ጤናማ ሕብረ ሕዋሳትን ይጎዳል። ይህም የአካል ክፍል ጉዳትን ሊያስከትል ይችላል።

እንቁላሎቹ በመራቢያ አካላት ውስጥም ሊገቡ ይችላሉ። ይህ ሁኔታ የመራቢያ እና የሽንት ቧንቧዎችን የሚያጠቃ ሺስቶሶሚያሲስ ወይም በእንግሊዝኛ አጠራሩ 'ዩሮጀኒታል ሺስቶሶሚያሲስ' ይባላል።

ይህ በሽታ የሆድ ህመምን፣ ካንሰርን እንዲሁም በአንዳንድ አስከፊ ሁኔታዎች ደግሞ ሞትን ሊያስከትል ይችላል።

'ስኔል ፊቨር' በሽታ እንደ ታዳጊዎች እና በግብርና እና በዓሳ ማስገር ሥራ ላይ እንደተሰማሩ ሰዎች ያሉ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች እንዲወስዱ በዓለም ጤና ድርጅት በተመከረው ፀረ ተውሳክ መድኃኒቶች አማካኝነት ሊድን ይችላል።

ሆኖም አዲሱ የጥገኛ ተውሳክ ዝርያ አሁን ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው መድኃኒት ላያድነው እንደሚችል በማላዊ ሊቨርፑል ዌልካም ክሊኒካዊ ምርምር ፕሮግራም ተባባሪ ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ጃኔሊሳ ሙሳያ እና ሌሎች ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

'የታየው በጣም ጥቂቱ ነው'

ሰዎች እና እንስሳትን የሚያጠቁት የተውሳክ ዓይነቶች መዳቀላቸው 'አዲስ ዓይነት ዝርያ' እንዲፈጠር ማድረጉን ጥናት አረጋግጧል።

እነዚህ ዝርያዎች ሰዎችንም ሆነ እንስሳትን የሚያጠቁ ሲሆን፣ ይህም የበሽታውን ሥርጭት ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ያደርገዋል።

በእርግጥ ቀደም ብሎ ተመራማሪዎች እንስሳትን እና ሰዎችን የሚያጠቁ ተውሳኮች እርስ በርስ እየተዳቀሉ እንደሆነ ያውቁ ነበር።

ሆኖም እነዚህ በመዳቀል የተገኙ እንቁላሎች ቀድሞ ከተሸከማቸው እና ከሚያውቁት አካል ውጪ በተሳካ ሁኔታ በሕይወት መቆየት ይችሉ እንደሆነ እርግጠኞች አልነበሩም።

ይህንን ለማረጋገጥም በማላዊ በተመረጡ ማኅበረሰቦች ውስጥ ከሰዎች እና ከእንስሳት ናሙናዎችን ወስደው ነበር።

በዚህ ምርምራቸውም ከጠበቁት በላይ ሰባት በመቶ የሚሆኑት ጥገኛ ተውሳኮች ሰውን የሚያጠቁትን ጨምሮ ከተለያዩ ዝርያዎች የተገኙ ዘረመል እንዳላቸው ማረጋገጥ ችለዋል።

ይህ ማለት ከተለያዩ ዝርያዎች በመዳቀል የተፈጠሩት ተውሳኮች እራሳቸውን በማራባት መሠራጨት ይችላሉ ማለት ነው።

"ሥርጭቱ በተፈጥሮ መንገድ የሚቀጥል ከሆነ ብዙ ነው" ሲሉ ፕሮፌሰር ሙሳያ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ምክንያቱም ቡድናቸው ምርመራውን ያካሄደው በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ምርመራዎች ሁልጊዜ ይህንን በትክክል መለየት ስለማይችሉ "የተገኘው በጣም ኢምንቱ ነው" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

እነዚህ አዲስ ተውሳኮች ወደፊት ከዚህ ቀደም የነበሩ ጥገኛ ተውሳኮችን ሊበልጡ እንደሚችሉም ሙሳያ አክለዋል።

የጤና ባለሙያዎች በሽታውን የተሸከሙ ታካሚዎችን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ገና ስላላወቁም ከባድ ችግር ሊሆን ይችላል ብለዋል።

"ይህ ንቁ፣ ችግሩ ከመግዘፉ በፊት በፍጥነት የሆነ ነገር ማድረግ እንችላለን? ለማለት ከእኛ ለፖሊሲ አውጪዎች የቀረበ ጥሪ" እንደሆነም ገልጸዋል።

ምርመራዎች የመራቢያ አካላትን ኬዞችን ይስታሉ

እነዚህ የተዳቀሉ ዝርያዎች የሰው ልጅ የመራቢያ አካላትንም እንደሚበክሉ ጥናቱ አረጋግጧል። ሆኖም እንቁላላቸው በአጉሊ መነፅር ሲታይ የጥገኛ ተውሳክ እንቁላል ስለማይመስሉ በተዳቀሉ ተውሳኮች የሚመጣውን 'የስኔል ፊቨር' በሽታ ለማከም አስቸጋሪ ነው።

የጤና ባለሙያዎችም ምልክቶችን በተሳሳተ መንገድ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች አድርገው ያነቧቸዋል።

በዚህም ምክንያት ሕክምና ሳያገኙ ይቆያሉ። የሽንት ቧንቧን እና የመራቢያ አካልን የሚያጠቃው ዩሮጀኒታል ሺስቶሶሚያሲስ ካልታከመ በመራቢያ አካል አካባቢ ሽፍታን፣ መካንነትን ሊያስከትል እንዲሁም ለኤችአይቪ የመጋለጥ ዕድልን ከፍ ሊያደርገው ይችላል።

በተለይ ለሴቶች የጤና፣ የማኅበራዊ እና የሥነ ተዋልዶ መዘዙ የከፋ እንደሚሆን በስፋት ይታሰባል።

"አንዲት ሴት ልጆች መውለድ ባትችል ብላችሁ አስቡት። በባህላችን የስም መጠሪያ ልጅ መውለድ በጣም ወሳኝ እንደሆነ ነው የሚታሰበው። በጣም መጥፎ እና አሳዛኝ በሽታ ነው" ብለዋል ሙሳያ።

በጫና ውስጥ ለውጥ

ቅይጥ ጥገኛ ተውሳኮች በሽታው ሌሎች አካባቢዎች እንዲከሰት ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተመራማሪዎች ደርሰውበታል።

የአየር ንብረት ለውጥ፣ ተጓዦች፣ ስደት 'ስኔል ፊቨር' እንዲሠራጭ ምክንያት ይሆናል። ቅይጡ ዝርያ ደግሞ በሽታውን ለመቆጣጠር አዳጋች ያደርገዋል። በዚህ በአዲሱ ዝርያ የመጣ በሽታ በደቡባዊ አውሮፓ ክፍል መከሰቱ ተመዝግቧል።

በዓለም ጤና ድርጅት ውስጥ የሺስቶሶሚያሲስ ቁጥጥር ፕሮግራምን የሚመሩት ዶክተር አማዶ ጋርባ ዲጂርሜይ "በሽታው ዓለም አቀፍ ስጋት ነው" ብለዋል።

ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት አዲሱ ዝርያ በሽታውን የመግታት ግቡ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ስጋት ገብቶታል።

"በሰዎች መካከል በሽታው ያልተላለፈባቸው አገራት አሉ። ሆኖም ጥገና ተውሳኩ በእንስሳት ላይ አለ። ይህ ለሰዎች አደጋ ሊሆን ይችላል" ብለዋል።

ድርጅቱ በአዲሱ የበሽታ ስጋት ላይ ለማተኮር አካሄዱን እየለወጠ ነው። በዚህ ዓመት በሽታውን በእንስሳት ላይ እንዴት መቆጣጣር እንደሚቻል አዲስ መመሪያ ያወጣ ሲሆን፣ ከአዲሱ ዝርያ ጋር ተያይዞ ማስጠንቀቂያ ወደተሰጣቸው አገራት ልኳል።

ከዚህም በተጨማሪ መጠነ ሰፊ የፀረ ተውሳክ መድኃኒት ሕክምና ፕሮግራሞች በ'ስኔል ፊቨር' የሚያዙ ሰዎች ከአውሮፓውያኑ 2006 እስከ 2024 ባሉት ዓመታት ውስጥ 60 በመቶ እንዲቀንስ አድርገዋል።

ሆኖም እንዲህ ዓይነት አመርቂ ለውጦች ዘላቂነት ያለው ድጋፍ እንደሚፈልጉ በመግለፅ፣ ችላ የተባሉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎችን ለመከላከል የሚደረገው ድጋፍ ከ2018 እስከ 2023 ባሉት ዓመታት 41 በመቶ እንደቀነሰ ጠቅሷል።

ሙሳያም በሽታው ብዙ ሳይሠራጭ ይቆማል የሚል ተስፋ አላቸው።

"ሥርጭቱን ልንቀንሰው እንችላለን፤ ሆኖም ይህ የአንድ ሰው ሥራ አይደለም። እኛ ምን ሊከሰት እንደሚችል እየተናገርን ነው። 'ይህ ችግር አለብን፤ አሁኑኑ መላ እንበለው እያልን ነው" ብለዋል።