ከአንድ ሺህ በላይ ኬንያዊያን በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ለመዋጋት መመልመላቸው ተነገረ

የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

በድምሩ አንድ ሺህ የሚሆኑ ኬንያዊያን ለሩሲያ ለመዋጋት መመልመላቸውን የኬንያ የደኅንነት ሪፖርት አመላከተ።

ረቡዕ ዕለት ለአገሪቱ ምክር ቤት የቀረበው የኬንያ ብሔራዊ የደኅንነት አገልግሎት (ኒስ) ሪፖርት እስከ ጎርጎሮሳዊያኑ አዲስ ዓመት ድረስ 89 ኬንያዊያን በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ግንባር ላይ መሆናቸውን አስታውቋል።

በጦርነቱ ቢያንስ አንድ ኬንያዊ የተገደለ ሲሆን፤ ሌሎች በርካታ ዜጎች ደግሞ ቆስለው ወደ አገራቸው መመለሳቸው ገልጿል።

መጀመሪያ ላይ 200 የሚሆኑ ዜጎቹ በጦርነቱ ለሩሲያ ለመዋጋት ተመልምለዋል ብሎ የገመተው የኬንያ መንግሥት፤ ሞስኮ ኬንያዊያን ወታደሮችን መመልመሏል እንድታቆም ይፈልጋል።

ሪፖርቱን ለምክር ቤቱ አባላት ያቀረቡት የምክር ቤቱ የአብላጫ ድምፅ መሪ የሆኑት ኪማኒ ኢችንጉዋ ሁኔታውን "በጣም የሚረብሽ" ሲሉ ገልጸውታል። የመንግሥት መኮንኖች መረብ ከሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ጋር በመሆን ኬንያዊያንን በመመልመል እና በጦርነቱ እንዲሳተፉ እያጓጓዝ ነው ብለዋል።

የስለላ ተቋሙ የስራ አገናኝ ኤጄንሲዎች ከአገሪቱ አየር ማረፊያ ሠራተኞች፣ የኢምግሬሽን ሠራተኞች፣ የወንጀል ምርመራ ባለሥልጣናት፣ የአደገኛ ዕፅ መኮንኖች እና ብሔራዊ የሠራተኞች ባለሥልጣን ሠራተኞች ጋር ምልመላውን እንዴት እንደሚያሳልጡት በዝርዝር አስቀምጧል።

የአብጫ ድምፅ መሪው የመንግሥት ተቋማት በናይሮቢ ከሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ባልደረቦች ጋር በመመሳጠር እንደሚሰሩ እና በሞስኮ የሚገኘው የኬንያ ኤምባሲ ምልምሎች የሩሲያ ቪዛ እንዲያገኙ እርዳታ ማቅረቡን ገለፀዋል።

ሐሙስ ዕለት በናይሮቢ የሚገኘው የኬንያ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ ውንጀላውን "አደገኛ እና አሳሳች" በሚል ውድቅ አድርጎታል።

የኤምባሲው ባልደረቦች "አፈንጋጭ እንቅስቃሴዎች" ወይም ሕገ ወጥ ምልመላ ላይ ተሳትፈው አያወቁም ብሏል።

ኤምባሲው የውጭ አገር ዜጎችን ለተዋጊነት እንደማይመለምል ገልፆ፤ የአገሪቱ ሕግ በሕጋዊ መንገድ ሩሲያ ውስጥ የሚገኙ የውጭ አገር ዜጎች በፈቃደኝነት የአገሪቱን ጦር እንዲቀላቀሉ እንደሚፈቅድ ግን ገልጿል።

በሞስኮ የሚገኙት የኬንያ አምባሳደር በወታደሮች ምልመላ ከወንጀለኞች ጋር ተባብረዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሠራተኞችን መለየት እንዳለባቸው ሪፖርቱን ያቀረቡት የምክር ቤት አባል ተናግረዋል።

ቢቢሲ የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተያየት እንዲሰጥ ጠይቋል።

ሪፖርቱ በአብዛኞቹ ምልምል ወታደሮች ምን እንደገጠማቸው አይጠቅስም። ግንባር ላይ ካሉት በተጨማሪ 35 ኬንያዊያን በሩሲያ የጦር ካምፕ ውስጥ መሆናቸውን፣ 39 ያህሉ መቁሰላቸውን እና 28ቱ ደግሞ መጥፋታቸውን ዘርዝሯል።

በምርመራው መሠረት ከ20 እስከ 50 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ የቀድሞ የኬንያ ጦር አባላት፣ የቀድሞ የፖሊስ አባላት እና ሥራ አጥ ኬንያዊያን የምልመላው ዋና ዒላማ ናቸው።

ምልምሎች 2,400 ዶላር ወርሃዊ ደሞዝ እንዲሁም ከ6,200 እስከ 8,300 ዶላር ጉርሻ ይከፈላችኋል ተብለው ቃል ይገባላቸዋል።

ይሁን እንጂ ከደረሱ በኋላ አብዛኞቹ ራሳቸውን የሚያገኙት በአነስተኛ የውትድርና ሥልጠና በጦርነቱ ግንባር ተሰልፈው መሆኑ ተነግሯል።