ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ግምት፡ ቶተንሀም ከአርሰናል፤ ማን ያሸንፋል?
የቶተንሀም ስታድየም ዓመቱን ሙሉ ደስታ የራቀው ሆኗል ይላል የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ክሪስ ሱተን።
ሱተን እንደሚለው ስፐርስ ወደ ወራጅ ቀጣን የሚያደርገው ግስጋሴ አስጊ ነው። አዲሱ አሠልጣኝ ይህን መቀየር እንዳለባቸው ሱተን ይናገራል።
በ27ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በሰሜን ለንደን ደርቢ ቶተንሀም የሊጉን መሪ አርሰናል ያስተናግዳል።
ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ ከኒውካስል የሚያደርጉትም ፍልሚያም ይጠበቃል። ሱተን የጨዋታዎቹን ግምት እንዲህ አስቀምጧል።
አስተን ቪላ ከሊደርስ ዩናይትድ
በመጀመሪያው ጨዋታ ቪላ ሊደስን በሞርጋን ሮጀርስ ሁለት ግቦች ሲረታ ኤላንድ ሮድ ስታድየም ተገኝቼ ተመልክቻለሁ።
ሊድስ አሁን ያለው ነጥብ 30 ነው። ይህ ነጥብ አምና በሊጉ ሊያቆያቸው የሚችል ነበር። ነገር ግን ዘንድሮ ተጨማሪ ሥራ ይጠበቅባቸዋል።
ቪላ በቅርብ ሳምንታት በሜዳቸው በኤቨርተን እና በብሬንትፈርድ ተረትተዋል። ያልተጠበቁ ነጥቦችን ባይጥሉ ይሄኔ ከአርሰናል ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው ነበር።
በዚህ ጨዋታ ሊደስ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ባስብም የኡናይ ኤምሪ ቡድን ይረታል ብዬ አልጠብቅም።
ግምት፡ 2-1
ብሬንትፈርድ ከብራይተን
ከብራይተን ጋር ሲነፃፀር ብሬንትፈርድ በዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የተሻለ አቋም ላይ ነው የሚገኘው።
ብራይተን ካለፉት 13 ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ነው ማሸነፍ የቻለው። ወደ ወራጅ ቀጣና ስጋት አይገቡም ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው።
ይህ ጨዋታ በጠባብ የግብ ልዩነት የሚጠናቀቅ እንደሆነ እገምታለሁ። ነገር ግን ድሉ የብሬንትፈርድ የሚሆን ይመስለኛል።
ግምት፡ 1-0
ቼልሲ ከበርንሊ
ባለፈው የሊግ ጨዋታ ከኋላ ተነስተው ክሪስታል ፓላስን መርታት የቻሉት በርንሊዎች በኤፍ ኤ ዋንጫ ከታችኛው ሊግ በመጣው ማንስፊልድ ተረትተው ወድቀዋል።
በዚህ ጨዋታ ቼልሲ ያሸንፋል ከማለት ውጭ ሌላ ምንም ልገምት አልችልም። እርግጥ ነው ባለፈው የሊጉ ጨዋታ ቼልሲ 2 ለምንም እየረታ ቆይቶ ሊድስ ሁለት ግቦች አስቆጥሮ ከስታንፈርድ ብሪጅ ነጥብ ይዞ መመለሱ ይታወሳል።
የቼልሲው አሠልጣኝ ሊያም ሮዝኒዮር ይህ ድጋሚ እንዲሆን የሚፈቅዱ አይመስለኝም።
ግምት፡ 2-0
ዌስት ሀም ከቦርንመዝ
ዌስት ሀም አሁንም የወራጅ ቀጣን ውስጥ ቢሆኑም ባለፉት ሳምንታት ያሳዩት ተጋድሎ የሚደነቅ ነው።
ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር በነበራቸው ግጥሚያ ባለቀ ሰዓት በተቆጠረባቸው ግብ አቻ ቢወጡም ከዚያም ከዚህም ነጥብ መስብሰባቸውን ቀጥለዋል።
ቦርንመዝም ጥሩ የሚባል አቋም ላይ ነው። ካለፉት አራት ጨዋታዎች ሦስቱን አሸንፏል። ከብራይተን ጋር የዘንድሮው የሊጉ የአቻ ውጤት መለያ ሆነዋል። ሁለቱም ቡድኖች 10 ጊዜ አቻ ወጥተዋል።
ባለፈው ኅዳር ቦርንመዝ ዌስት ሀምን ባስተናገደበት ጨዋታ 2 እኩል መለያየታቸው ይታወሳል። በዚህኛውም ጨዋታ አቻ ይለያያሉ የሚል ግምት አለኝ።
ግምት፡ 1-1
ማንቸስተር ሲቲ ከኒውካስል
በዘንድሮው የውድድር ዘመን ሁለት ቡድኖች ሲገናኙ ይህ አራተኛ ጊዜ ነው። በኤፍ ኤ ዋንጫ አምስተኛ ዙር ፍልሚያም ይገናኛሉ። ኒውካስል በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ በሳምንቱ አጋማሽ ረጅም ርቀት ተጉዞ አዘርባይጃን ደርሶ መጥቷል።
ኒውካስል በኤቲሃድ ያለው የማሸነፍ ክብረ-ወሰን ደካማ የሚባል ነው። በፕሪሚዬር ሊጉ ባለፉት 20 ጨዋታዎች ኤቲሃድ ላይ አሸንፈው አያውቁም።
ይህ ጨዋታ ለሲቲ ቀላል ይሆናል ባልልም እንደሚያሸንፉ ግን እገምታለሁ። ሲቲ ይህን ጨዋታ በመርታት ከአርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ሊያጠብ ይችላል።
ግምት፡ 3-1
ክሪስታል ፓላስ ከዎልቭስ
ዎልቭስ በሮብ ኤድዋርድስ አሠልጣኝነት የተወሰነም ቢሆንም ለውጥ ማሳየታቸው እሙን ነው። ያላቸው ነጥብ ከመውረድ የሚታደጋቸው ባይሆንም ከአርሰናል ጋር በነበረው ጨዋታ ያሳዩት ፍልሚያ የሚደነቅ ነው።
ከዎልቭስ በ48 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ ክሪስታል ፓላስ ያቀናው ዮርገን ስትራንድ ላርሰን በዚህ ጨዋታ ጎልቶ ሊወጣ ይችላል። ግብም ያስቆጥራል ብዬ ጠብቃለሁ።
ፓላስ ነጥብ መሰብሰብ አለባቸው። ከዚህ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ያገኛሉ።
ግምት፡ 2-1
ኖቲንግሀም ከሊቨርፑል
ቪክተር ፔሬይራ በያዝነው የውድድር ዓመት አራተኛው የኖቲንግሀም አሠልጣኝ ሆኖ ተቀጥሯል። እኔ ሾን ዳይች መባረር ነበረበት የሚል እምነት የለኝም። ነገር ግን በፎረስት ቤት የአሠልጣኝ መቀያየር አዲስ ነገር አይደለም።
ፎረስት ትልቁ ችግራቸው ግብ ማስቆጠር አለመቻላቸው ነው። ከሊቨርፑል ጋር በሚኖራቸው ጨዋታ ይህ ይቀየራል ብዬ አልገምትም።
ግምት፡ 0-1
ሰንደርላንድ ከፉልሀም
ሰንደርላንድ ባለፉት ጥቂት ሳምንት አቋሙ መዋዠቅ ጀምሯል። ቢሆንም በዘንድሮው የውድድር ዓመት ያሳዩን ነገር የሚወደስ ነው።
ባለፈው የሊጉ ጨዋታ ከሊቨርፑል ጋር በነበረው ፍልሚያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሜዳቸው የተሸነፉት ሰንደርላንዶች እንዴት ከዚህ አገግመው ከፉልሀም ጋር የሚደረገውን ግጥሚያ ይወጡታል የሚለው ትልቁ ጥያቄ ነው።
ፉልሀም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች በተከታታይ ሽንፈት ገጥሟቸዋል። ይህን ጨዋታ ይረታሉ ብዬ አልጠብቅም።
ግምት፡ 1-1
ቶተንሀም ከአርሰናል
አዲሱ የቶተንሀም አሠልጣኝ ኢጎር ቱዶር የክለቦችን አቋም በመቀየር ይታወቃሉ። ስፐርስ ይህ ያስፈልጋቸዋል። ከወራጅ ቀጣና ስጋት ለመውጣት አንድ አሊያም ሁለት ጨዋታዎችን ማሸነፍ አለባቸው።
ይህ ለስፐርስ ትልቅ ጨዋታ ነው። በአርሰናል የዋንጫ ተስፋ ላይም ውሀ ለመቸለስም ያስችላቸዋል። የከተማ ተቀናቃኛቸው ላይ ይህን ጫና ማሳደር ደስታ ይፈጥርላቸዋል።
አርሰናል ከዎልቭስ ጋር በነበረው ጨዋታ ሁለት ለባዶ እየመራ ቆይቶ ባለቀ ሰዓት አቻ መለያየቱ ለሚኬል አርቴታ መልካም ዜና አይደለም።
ስፐርስ አርሰናልን ለማስቆም የተቻላቸውን ለማድረግ ቆርጠው እንደሚነሱ ባውቅም መድፈኞቹ ግን ለዚህ ጨዋታ የሚረቱ አይመስለኝም።
ግምት፡ 0-3
ኤቨርተን ከማንቸስተር ዩናይትድ
ባለፈው ኅዳር ዩናይትድ በሜዳው በኤቨርተን ተሸንፏል። ኤቨርተን በዚህ ጨዋታ በቀይ ካርድ ምክንያት አብዛኛውን የጨዋታ ጊዜ በ10 ተጫዋች ተፋልሞ ነው ማሸነፍ የቻለው።
አሁን በማይክል ካሪክ የሚመራው ዩናይትድ ሌላ ቡድን ሆኗል። ባለፈው የሊጉ ጨዋታ ባለቀ ሰዓት ባስቆጠሩት ጎል ከዌስት ሀም አቻ ቢለያዩም ለማሸነፍ ያላቸው ጉጉት ግልፅ ነው።
ኤቨርተን ከሜዳቸው ካገኙት ነጥብ ይልቅ ከሜዳቸው ውጪ የሰበሰቡት ይበልጣል። ይህ ጨዋታ ለዩናይትድ ቀላል ባይሆንለትም የሆነ ነገር እንደሚያገኝበት እገምታለሁ።
ግምት፡ 1-1