የማኅፀን በር ካንሰርን ከወር አበባ በሚወሰድ ናሙና መመርመር የሚያስችል አዲስ ዘዴ ተገኘ

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የማኅፀን በር ካንሰርን ከወር አበባ ላይ በሚወሰድ የደም ናሙና መመርመር በሽታውን ለመለየት ትክክለኛው እና ቀላሉ መንገድ መሆኑን ተመራማሪዎች አስታወቁ።

በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የማኅፀን በር ካንሰርን ለመለየት የሕክምና ባለሙያዎች ከማኅፀን በር ላይ ህዋስን በመውሰድ ምርመራ ያደረጋሉ።

በአዲሱ የምርመራ መንገድ ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ናሙናውን በቤት ውስጥ በንጽህና መጠበቂያ ላይ በሚቀመጥ ጥጥ መሰብሰብ እንደሚቻል ያስረዳል።

በማኅፀን በር ካንሰር ላይ የሚሠሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በሽታውን ለመመርመር አዲስ እና የተሻሻለ አማራጭ መፈለግ አበረታች መሆኑን ይናገራሉ።

ምንም እንኳ ምርምሩ ያለበት ደረጃ ገና ቢሆንም እንደዚህ ዓይነት አዳዲስ የምርመራ መንገዶች የምርመራውን ተደራሽነት እንደሚያሻሽሉ ባለሙያዎች ተናግረዋል።

የዩኬ ብሔራዊ ጤና አገልግሎት በእንግሊዝ የተወሰኑ አካባቢዎች ለሚገኙ እና የማኅፀን በር ካንሰር ምርመራ ቀጠሯቸው ላለፋቸው ሴቶች በቤታቸው ምርመራ ማድረግ የሚያስችላቸውን ናሙና መሰብሰቢያ መላክ ጀምሯል።

ይህ ናሙና መሰብሰቢያ ከማኅፀን ፈሳሽ መሰብሰብ የሚያስችል መሳሪያ ያለው ሲሆን፣ በዚህ ዓመት በስፋት ይሠራጫል ተብሏል።

በዩናይትድ ኪንግደም የማኅፀን በር ካንሰር ምርመራ ለሁሉም ሴቶች የሚሰጥ ሲሆን፣ በየአምስት ዓመቱ ደግሞ ዕድሜያቸው ከ25 እስከ 64 ለሚሆናቸው ሴቶች የማኅፀን ምርመራ ይደረጋል።

ምርመራው ካንሰር አምጪ የሆነው ኤችፒቪን የተባለውን ቫይረስ በመለየት ላይ ያተኮረ ነው።

ምርምራውን ነርስ እና ዶክተር በጋራ በመሆን የሚያደርጉ ሲሆን፣ ስፔኩለም የተባለ መሳሪያ ማኅፀን ውስጥ በማስገባት የመለየት ሥራው ይከናወናል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዩኬ አምስት ሚሊዮን ሴቶች የማኅፀን በር ካንሰር ምርመራ አላደረጉም። ይህም ሊሆን የቻለው ከፍርሃት፣ ከሕመም እና ምቾት ከማጣት የተነሳ ነው።

'ዘ ኢቭ አፒል' የተባለው በጎ አድራጎት ድርጅት ባልደረባ የሆኑት አቴና ላምኒሶስ "ለአንዳንድ ሴቶች የማኅጸን ምርመራ በብዙ ምክንያቶች ከባድ ሊሆን ይችላል፤ ለምሳሌ ከዚህ ቀደም መጥፎ ልምድ ካጋጠማቸው፣ ካረጡ፣ የአካል ወይም የመማር እክል ያለባቸው ከሆኑ፣ የባህል ተጽእኖ ወይም ከፆታዊ ጥቃት የተረፉ ከሆኑ ነው" ሲሉ አብራርተዋል።

ወጣት ሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞች ወይም አነስተኛ ቁጥር ካላቸው ማኅበረሰቦች የሚመጡ እንዲሁም የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን የምርመራ ቀጠሯቸውን ከሚያሳልፉት መካከል መሆናቸውን ባለሥልጣናት ይናገራሉ።

ዶክተሮች የማኅፀን ምርመራን እንዴት የበለጠ ምቾት የሚሰጥ ማድረግ እንደሚቻል ምክር ይሰጣሉ።

'ዘ ቢኤምጄ ጆርናል' ላይ የወጣው በዚህ አዲስ ጥናት ላይ የተሳተፉ ቻይናውያን ተመራማሪዎች ከወር አበባ በሚወሰድ የደም ናሙና ላይ የሚደረግ ምርመራ ቀላል እና ደኅንነቱ የተጠበቀ አማራጭ እንደሚሆን ገልጸው፣ አሁን ካሉት የምርመራ ዘዴዎችም "የተሻለ አማራጭ" ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

ጥናቱ ከ20 እስከ 54 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ከ3,000 በላይ ሴቶችን ያካተተ ሲሆን፣ በአነስተኛ የንጽህና መጠበቂያ ላይ የተሰበሰበው የደም ምርመራ ውጤታማነትን በክሊኒኮች ከተሰበሰቡ ናሙናዎች ጋር አነጻጽሯል።

ሴቶች ስለ ውጤቶቹ በልዩ ሁኔታ በተዘጋጀ መተግበሪያ በኩል ተነግሯቸዋል።

ናሙናዎቹ ወደ ላቦራቶሪ ሲላኩ፣ ተመራማሪዎቹ የደም ምርመራ እንደሌሎቹ ዘዴዎች በበሽታው የተያዙ ሰዎችን በመለየት ረገድ በጣም ጥሩ እንደሆነ እና ያልታመሙትን በመለየት ረገድ የተሻለ እንደሆነ አረጋግጠዋል።

ተመራማሪዎቹ ከወር አበባ የሚወሰድ የደም ናሙናን ተጠቅሞ ኤችፒቪን መመርመር "ምቹ" ብቻ ሳይሆን የሴቷን ግላዊ መብት ማክበር እንዲሁም ምቾት የሚነሱ ነገሮችን መቀነስ ጭምር ነው ብለዋል።

የኤችፒቪ ምርመራ ተደርጎ ቫይረሱ መኖሩ የሚረጋገጥባት ሴት ሌሎች ምርመራዎች እና ሕክምና እንድታገኝ ይደረጋል።

ይህም ልዩ የማጉያ መነጽር በመጠቀም ዶክተሮች የማኅጸን ጫፍን በቅርበት እንዲመረምሩ እና ከካንሰር በፊት የሚመጡ ሴሎችን እንዲፈልጉ ያስችላቸዋል።

ባለሙያዎች እንደሚሉት የወር አበባ የደም ምርመራዎች አሁን ካለው የማኅጸን ጫፍ ምርመራ ጋር ቀጥተኛ አማራጭ አይደሉም።

ምክንያቱም የወር አበባ ማየት የጀመሩ ሴቶች ብቻ ሊጠቀሙባቸው መቻላቸው ነው።

ሌሎች ደግሞ ጥናቱ የምርመራውን ውጤት አጋንኖ አቅርቧል ሲሉ ትችታቸውን ይሰነዝራሉ።

በዩኬ የካንሰር ምርምር ውስጥ የጤና መረጃ ሥራ አስኪያጅ የሆነችው ሶፊ ብሩክስ የማኅፀን ጫፍ ምርመራን "በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ" አዳዲስ መንገዶችን የሚዳስስ ጥናት ማየት "አበረታች" ነው ብላለች።

የወር አበባ ደምን ለኤችፒቪ መመርመር አስደሳች እና ደኅንነቱ የተጠበቀ አካሄድ እንደሆነ ተናግራለች።

ነገር ግን አሁን ባለው ምርመራ ውስጥ እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውል ለማወቅ በተለያዩ ቡድኖች መካከል ተጨማሪ ምርምር እንደሚያስፈልግ አፅንዖት ሰጥታለች።

ከዘ ኢቭ አፒል የመጡት አቴና ላምኒሶስ ሕይወት አድን ሊሆን የሚችል ምርመራ ለማቅረብ አዳዲስ እና የበለጠ ተቀባይነት ያላቸው መንገዶችን ማየት "አስደሳች" እንደሆነ ተናግረዋል።

"ሰዎች ስለ ምርመራው የተለያዩ አመለካከቶች እና ስጋቶች አሏቸው፤ ስለዚህ የተለያዩ ዘዴዎችን መምረጥ መቻል ለምርመራ ብቁ ለሆኑ፣ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ላልተገኙ ሰዎች በጣም አዎንታዊ ሊሆን ይችላል" ብለዋል።