ሐማስ አዲስ ጊዜያዊ መሪ ለመምረጥ ድምጽ እየሰጠ መሆኑን አንድ ምንጭ ለቢቢሲ ተናገሩ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አብዛኛዎቹ ከፍተኛ አመራሮቹ በእስራኤል የተገደሉበት ሐማስ አዲስ ጊዜያዊ መሪ ለመምረጥ ምርጫ እያካሄደ መሆኑን ለቡድኑ ቅርበት ያላቸው አንድ የፍልስጤም ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናገሩ።

ድምጽ የመስጠት ስነ ስርዓቱ እየተካሄደ ያለው በጋዛ፣ በወረራ በተያዘው ዌስት ባንክ እና በሌሎች ስፍራዎች በሚገኙ የሃማስ አባላት መካከል እንደሆነም ተገልጿል።

በድህረ ጦርነት ስለሚኖረው የጋዛ አስተዳደር የመልሶ ግንባታ ጥረት እና በአካበቢው የሚገኙ ታጣቂ ቡድኖችን በተመለከተ አሜሪካ እና ሌሎች አሸማጋይ አካላት ንግግር እያደረጉ ባሉበት ወቅት የሚካሄደው የዚህ ምርጫ ውጤት ቡድኑ ምን አይነት አቅጣጫ ለመከተል እንዳለመ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል ተብሏል።

ሐማስ ምርጫውን የሚያካሄደው እስራኤል በጋዛ ጦርነት በወሰደችው እርምጃ በአብዛኛዎቹ ከፍተኛ አመራሮቹ መገደላቸውን ተከትሎ ነው።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ጋዛ ውስጥ የሚገኙት አብዛኛዎቹ ሰዎች ድምጻቸውን ሰጥተዋል። ሂደቱ በሌሎች ቦታዎችም ተመሳሳይ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደሆነ ግን እስካሁን አልታወቀም።

በዚህ ሂደት የሚመረጠው አዲስ መሪ ለአንድ ዓመት ሥልጣን ላይ ይቆያል።

የጋዛ ሰርጥን የሚያስተዳድረው ሐማስ ካለፉት ዓመታት ወዲህ ዌስት ባንክ ውስጥም ያለው ድጋፍ እየጨመረ ነው። ይሁን እንጂ ዌስት ባንክ ውስጥ ባሉት የእስራኤል ጦር እና የፍልስጤም አስተዳደር የጸጥታ ኃይሎች ምክንያት በስፍራው የሚያደርገው እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ የተገደበ ነው።

ከሁለት ዓመት ጦርነት በኋላ በአሜሪካ አደራዳሪነት ባለፈው ጥቅምት ላይ የተኩስ አቁም ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን የስምምነቱ ቀጣዩን ምዕራፍ በተመለከተ የሚደረገው ድርድር ቀጥሏል።

በአሜሪካ የሰላም እቅድ መሰረት፤ ወደፊት በሚቋቋመው የግዛቱ አስተዳደር ውስጥ ሐማስ ምንም ሚና አይኖረውም። በጊዜ ሂደት የጋዛ አስተዳደር ዌስት ባንክ ለሚያስተዳድረው የፍልስጤም አስተዳደር ተላልፎ ይሰጣል። ይህ ከመሆኑ በፊት ግን የፍልስጤም አስተዳደር በማሻሻያ ውስጥ እንዲያልፍ ታቅዷል።

የሐማስ ዋና መሪ የነበሩት ያህያ ሲንዋር በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2024 ጋዛ ውስጥ በእስራኤል መገደላቸው ይታወሳል። የቡድኑ የፖለቲካ መሪ የነበሩት ኢስማኢል ሃኒዬም ሦስት ወራትን አስቀድሞ በኢራን ውስጥ በእስራኤል ጥቃት ተገድለዋል።

የሐማስ ወታደራዊ አዛዥ መሐመድ ዴይፍም እስራኤል ጋዛ ውስጥ በተፈጸመችው የአየር ጥቃት የተገደሉት በተመሳሳይ ወር ነበር።

ሃኒዬ እና ሲንዋር ከተገደሉበት ጊዜ አንስቶ የሐማስ ዋና መሪነት ሥልጣን ማንም ሳይሾምበት ክፍት ሆኖ ቆይቷል። የቡድኑ እንቅስቃሴ ሲመራ የነበረው መቀመጫቸው ኳታር ውስጥ ባደረጉት መሐመድ ዳርዊሽ የሚመራ ጊዜያዊ ኮሚቴ ነበር።

በሐማስ ሕግ መሠረት የቡድኑ ዋና ኃላፊ የሚመረጠው ጋዛን፣ ዌስት ባንክን፣ በእስራኤል የሚገኙ ፍልስጤማውያን እስረኞችን እና በውጭ አገር የሚገኙ ባለሥልጣናትን በሚወክለው የአጠቃላይ ሹራ ምክር ቤት ነው። የሐማስ ከፍተኛው ውሳኔ ሰጪ አካል የሆነው ይህ ምክር ቤት 86 አባላት አሉት።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ምንጭ እንደሚገልጹት በአሁኑ ምርጫ ላይ ሁለት አመራሮች በዋና በተፎካካሪነት ቀርበዋል።

በቀዳሚነት የተጠቀሱት በጋዛ የሃማስ መሪ የሆኑት ካሊል አል ሀያ ናቸው። ግለሰቡ ከቀድሞዎቹ መሪዎች ሲንዋር እና ሃኒዬ ጋር የተሰለፉ ተደርገው ይቆጠራሉ።

ሁለተኛው ተቀናቃኝ በውጭ አገር የሃማስ መሪ የሆኑት አንጋፋው የቡድኑ ሰው ካሊድ መሻል ናቸው። መሻል፤ ከዚህ ቀደምም ለ20 ዓመት ገደማ ሐማስን በዋና መሪነት አገልግለዋል። በአሁኑ ሰዓትም የሚገኙት በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ ነው።

ቡድኑ ባደረጋቸው የውስጥ ውይይቶች ውስጥ የሌሎች ሰዎች ስሞችም የተነሱ ቢሆንም እስካሁን ድረም ይፋዊ የእጩዎች ዝርዝር አልወጣም።