ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል ስጋት ውስጥ መኖር
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል ግጭቶች በተደጋጋሚ ሲከሰቱ ቆይተዋል።
በተለይ በትግራይ፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ባለፉት ዓመታት የተካሄዱ ግጭቶች የነዋሪውን ሕዝብ የተረጋጋ ሕይወትን ከማወክ ባሻገር የዘወትር ስጋት እንደሆኑ ቀጥለዋል።
የሁለት ዓመታት ደም አፋሳሽ ጦርነት በተካሄደበት የትግራይ ክልል እና የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢ ሌላ ዙር ጦርነት ይከሰታል የሚል ስጋት እየተጠናከረ እየመጣ ነው።
በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ከታጣቂ ቡድኖች ጋር የሚከሰቱት ግጭቶችም ብልጭ ድርግም እያሉ ቀጥለዋል።
ይህም በአካባቢዎቹ በሚኖሩ ሰዎች መደበኛ ሕይወታቸው ላይ ከባድ ተጽእኖን ከማደሳር ባሻገር ከዛሬ ነገ ምን ሊከሰት ይችላል በሚል ጭንቀት ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል።
ግጭቶች በግለሰቦች ሕይወት እና እንቅስቃሴ ላይ የሚኖራቸው አሉታዊ ተጽእኖ ለስጋቱ ምንጭ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው።
በተደጋጋሚ ግጭቶች በሚከሰትባቸው አገራት የጦርነት ተጽእኖ የዕለት ተዕለት ሕይወት አካል፣ የጋራ ትውስታ እንዲሁም ተጽእኖው ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር ነው።
በእነዚህ አገራት ውስጥ የሚፈጠር ተደጋጋሚ የጦርነት እና የግጭት ስጋቶች የፍርሃት እና የጭንቀት ስሜትን አልያም ርህራሄን እንዲያዳብሩ ያደርጋል።
በግጭቶች ሳቢያ የሚከሰተው የምጣኔ ሀብት ቀውስ፣ የምግብ እና የነዳጅ ዋጋ መናር እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎቶች መቋረጥ ተደራራቢ ስጋትን ይፈጥራል።
ይህ ደግሞ በጦርነት ውስጥ ላለፈ ሕዝብ የቆየ ጭንቀትን የሚቀሰቅስ፣ የከረመ ቁስል እንዳይጠግግ የሚያደርግ ይሆናል።
ሳይኮቴራፒስት የሆኑት ማሪ ሜሶግ ለቢቢሲ ሰዎች ለረዥም ጊዜ በጦርነት ስጋት ውስጥ ሲኖሩ፣ የነርቭ ሥርዓታቸው በእውነተኛው ጦርነት እና ሊኖር በሚችል የጦርነት ስጋት መካከል ያለውን ልዩነት በሚገባ አይለይም ሲሉ ተናግረዋል።
"ሰውነታችን ምላሽ የሚሰጠው በቀጥታ ለሚጠብቀው አደጋ ነው" ይለሉ።
ግጭቶች በሰው ሕይወት እና አካል እንዲሁም በንብረት እና በመሠረተ ልማቶች ላይ ከሚያደርሱት ጉዳት ባሻገር በሰዎች አካላዊ እንዲሁም ሥነ ልቦናዊ ጤና እና ደኅንነት ላይ ከባድ ተጽእኖን እንደሚያስከትል ባለሙያዎች ይናገራሉ።
እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ስንሆን የሚከሰቱ ሥነ ልቦናዊ ለውጦች ምንድን ናቸው? ለመቋቋምስ ምን ማድረግ እንችላለን?
ሰውነታችን አደጋ ሲሰማው ምን ይሆናል?
የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ብሔራዊ ጤና አገልግሎት ውጥረትን (ስትረስ) "አእምሯችን የሚሰጠው ተፈጥሯዊ ምላሽ" ሲል ይበይነዋል። ይህም ብዙ ጊዜ በዙሪያችን የሚሆነውን መቆጣጣር ካለመቻል ስሜት ጋር የተያያዘ ነው።
አንድ ሰው ፍርሃት እና ጭንቀት ሲሰማው ሰውነቱ እንደ አድሪናሊን እና ኮርቲሶል ያሉ ሆርሞኖችን ያመነጫል።
ይህ ተፈጥሯዊ ምላሽ ትኩረት ለማድረግ፣ ንቁ ለመሆን እንዲሁም ነገሮችን ለመከወን እጅጉን አስፈላጊ ነው።
ነገር ግን ውጥረቱ በተራዘመ ቁጥር አሳሳቢ ችግር እየሆነ ይመጣል።
የሕክምና ባለሙያዎች ውጥረት አካላዊ ምልክቶችን እንደሚያስከትል ይናገራሉ።
የጡንቻ መዛል ወይም ሕመም፣ ራስ ምታት ወይም ብዥታ፣ የምግብ አለመፈጨት፣ የደረት ሕመም ወይም የልብ ምት መዛባት ከሚጠቀሱ ምልክቶች መካከል ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ ትኩረት አድርጎ ውሳኔ ለመስጠት አለመቻል፣ የድካም ስሜት፣ የማያቋርጥ ጭንቀት እንዲሁም ነገሮችን መርሳት ከሥነ ልቦና ምልክቶቹ መካከል ይጠቀሳሉ።
ቁጡ መሆን፣ የእንቅልፍ መዛባት፣ የምግብ ፍላጎት መጨመር ወይም መቀነስ፣ ወደ ተወሰኑ ቦታዎች መሄድ አለመፈለግ ወይም ሰዎችን ለማግኘት አለመሻት፣ የሲጋራ እና የመጠጥ አወሳሰድ መጨመር ከሚታዩ የባሕሪ ለውጦች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
ባለሙያዎች ውጥረት የእነዚህ ለውጦች ዋነኛ ምንጭ ነው ብሎ መደምደም እንደሚያስቸግር ይናገራሉ።
ማሪ ሜሶግ "በተደጋጋሚ ስለጦርነት የሚደረግ የፖለቲካ ውይይት አእምሯችን የቦምብ ፍንዳታ እንኳ በሌለበት በተደጋጋሚ አደጋን እንዲፈልግ ያደርገዋል" ይላሉ።
"አሁን በሆስፒታሎች ውስጥ እያየን ያለነው ትክክለኛው ጭንቀት አይደለም። ነገር ግን ሙሉ በሙሉ መረጋጋት ያልቻለ የሚረበሽ ስሜት ነው" ሲሉም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።
በግጭት በተጠቁ አካባቢዎች የሚኖሩ በርካታ ሰዎች በቋሚነት በጡንቻ ሕመም፣ በምግብ መፈጨት ችግር፣ በእንቅልፍ ማጣት፣ በራስ ምታት፣ በልብ ምት መዛባት እንዲሁም በከባድ የመሰላቸት ስሜት ይጠቃሉ ይላሉ ባለሙያው።
"እነዚህ አእምሮ የፈጠራቸው ምልክቶች አይደሉም። ከዚያ ይልቅ ሰውነታችን ለረዥም ጊዜ በቆየ እርግጠኝነት ማጣት ውስጥ የሚሰጣቸው ሥነ ሕይወታዊ ምላሾች ናቸው።"
ውጥረት የጤና አደጋ የሚሆነው መቼ ነው?
የአሜሪካ የሥነ ልቦና ማኅበር ውጥረት የጤና አደጋ የሚሆነው ግለሰቡ የተለመደ ተግባሩን ለረዥም ጊዜ መከወን ሳይችል ሲቀር ነው ይላል።
ውጥረት ለረዥም ጊዜ በቆየ ቁጥር በአካል እና በአእምሮ ላይ የሚኖረው ተጽእኖ ከፍተኛ ይሆናል።
ማኅበሩ ለረዥም ጊዜ ለቆየ ውጥረት/ጭንቀት የሚሰጥ ምላሽ እንዲሁም ኮሪስቶል ለተሰኘው ሆርሞን ለረዥም ጊዜ መጋለጥ የአካላችንን የተለያዩ ተግባራት ያስተጓጎላል።
እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ጭንቀትን እና ድብርትን፣ የምግብ መፈጨት ሥርዓትን ማዛባት፣ የራስ ምታት፣ የልብ ሕመም፣ የደም ግፊት፣ የእንቅልፍ መዛባት፣ የክብደት መጨመር፣ የትውስታ መደብዘዝን፣ ትኩረት ማጣትን እና የጡንቻ ሕመምን ያስከትላል።
ማኅበሩ አክሎም ከባድ የሆነ ጭንቀት የበሽታ የመከላከል አቅምን በማዳከም ከሕመማችን በቶሎ እንዳናገግም ያደርጋል ብሏል።
አንዳንድ ሰዎች ከዚህ የተነሳ አመጋገባቸው ላይ እንዲሁም የሚያጨሱት የሲጋራ መጠን ላይ ጭንቀታቸውን ለመቋቋም በሚል ለውጥ ያሳያሉ።
የሥነ ልቦና ምሑር የሆኑት ማዙቅ ሰውነታችን ምን ጊዜም "በጦርነት እና በግጭት" ውስጥ ለመቆየት የተሠራ አይደለም ይላሉ።
ኮሪስቶል ምን ጊዜም ንቁ ሆነን እንድንቆይ ያደርገናል ያሉት ባለሙያው፣ ይህ ሆርሞን በከፍተኛ መጠን ለረዥም ጊዜ በሰውነታችን ውስት መከሰት የእንቅልፍ መዛባት፣ በሽታ የመከላከል አቅም መዳከም፣ የባህሪ መለዋወጥ፣ የምግብ መፈጨት ችግር እና አጠቃላይ ጤና ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል ይላሉ።
በተደጋጋሚ ለጦርነት ዜናዎች መጋለጥ "አስከፊ የሆኑ ሃሳቦች" ወደ አእምሯችን እንዲመላለሱ በማድረግ አእምሯችን ራሱን እንዲከላከል ምን ጊዜም ለከፋ አደጋ ራሱን እንዲያዘጋጅ ያደርገዋል ይላሉ ባለሙያው።
ይህ ደግሞ ከፍተኛ ከሆነ የሥነ ልቦና ኪሳራ ጋር አብሮ አንደሚመጣ ባለሙያው ጨምረው አስረድተዋል።
"የግጭት ወሬ በሚበዛበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች የሚሰማቸው ስሜት የተጋነነ ሳይሆን ከሚኖሩበት ከባቢ ጋር የተመጣጠነ ነው" ሲሉም አጽንኦት ይሰጣሉ።
አክለውም "በግጭት እና በጦርነት በተጠቁ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች የአእምሮ ጤና ከዚህ ቀደም ከነበረ ትራውማ (የሥነ ልቦና ቁስለት) ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ከከባድ ኃላፊነት ወይም ሊሆኑ ወይንም ላይሆኑ የሚችሉ አደገኛ ክስተቶችን ከመጠበቅ ጋርም የተያያዙ ናቸው" ይላሉ።
ምን ልናደርግ እንችላለን?
የዩኬ ብሔራዊ የጤና አገልገሎት የሚከተሉትን ተግባራት ይመክራል፦
- ከጓደኛ፣ ከቤተሰብ አባል ወይንም ከጤና ባለሙያ ጋር ስለ ስሜትዎ ማውራት
- የሚያረጋጋ አተነፋፈስን መለማመድ፣
- ስትረስ/ውጥረት ለሚያስከትሉ ጊዜያት ወይንም ክስተቶች ራስን ማዘጋጀት
- በዙሪያ ከሚገኙ ሰዎች የሚገኝ ድጋፍን መጠቀም
- አልኮል፣ ሲጋራ ወይንም ሌሎች አደንዛዥ እጾችን አለመጠቀም
- ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ከማድረግ ይልቅ በትንንሽ እና ልናከናውናቸው በምንችላቸው ነገሮች ላይ ማተኮር
የአሜሪካ የሥነ ልቦና ማኅበር በበኩሉ፦
- የውጥረት ምክንያት የሆኑትን በመለየት የሚኖር የስሜት ለውጥን መከታተል
- ውጥረት ን ለመቆጣጣር አስቀድሞ ማቀድ
- ጠንካራ ደጋፊ የሚሆን ግንኙነት መመሥረት
- የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በቋሚነት መሥራት
- ከሰባት እስከ ስምንት ሰዓት መተኛት
- በተደጋጋሚ ጭንቀት የሚሰማዎ ከሆነ የባለሙያ ምክር መጠየቅ
ማሪ ሜሶግ እንዲሁ መረበሽን እና የኮሪስቶል መጠንን ለመቆጣጣር የሚረዱ ተግባራዊ ልምምዶችን ይመክራሉ።
"የኮሪስቶል መጠንን መቀነስ ማለት እውነታን ገሸሽ ማድረግ አይደለም። ነገር ግን ለነርቭ ሥርዓታችን የሚያረጋጋ ምልክቶችን በመላክ ዳግም ጥንካሬውን እንዲያገኝ መርዳት ማለት ነው"
ትንፋሽን መቆጣጠር - ለጥቂት ደቂቃዎች በዝግታ መተንፈስ፤ ይህ ለነርቭ ሥርዓታችን የደኅንነት መልዕክት በማስተላለፍ "ከግጭት ወይም ጦርነት" ስሜት ለመውጣት ይረዳል።
ወጥነት ያላቸውን ተግባራት መከወን - በተወሰነ ሰዓት መንቃት፣ መደበኛ የምግብ ሰዓት መኖር ወይም በተወሰነ ሰዓት የእግር ጉዞ ማድረግ ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም ወጥ የሆኑ ተግባራት አእምሯችን በየጊዜው ስጋትን በንቃት ከመጠበቅ እንዲታቀብ ያደርገዋል።
ዜና የምንከታተልበትን ጊዜ መቆጣጣር - ዜናን ያለማቋረጥ ከማየት እና ከመስማት በቀን አንዴ ወይንም ሁለቴ ብቻ መከታተል።
ትከሻን መታ መታ ማድረግ - ትከሻን ለአንድ ወይም ሁለት ደቂቃ ያህል ረጋ ብሎ መታ መታ ማድረግ የመረጋጋት ስሜትን ይፈጥራል።
በዝግታ መመገብ - በቀስታ እያንዳንዱን ጉርሻ ረጋ ብሎ ማላመጥ የሰውነትዎን ስልተ ምት በማረጋጋት ረገድ ካለው አስተዋጽኦ ባሻገር ትኩረትን ለመሰብሰብ ይረዳል።