ከሚለገሱ የወንዴ የዘር ፈሳሾች ተፈላጊዎቹ ከየትኛው አገር የሚገኙ ናቸው? ለምን?

አንዳንድ ወንዶች በለገሱት ዘር ፈሳሽ (ስፐርም) ምክንያት የበርካታ ሕፃናት አባቶች እየሆኑ ነው።

በቅርቡም የአንድ ለጋሽ የወንዴ ዘር የዘረመል ችግር እንዳለበት ሳይታወቅ ጥቅም ላይ ውሎ በአውሮፓ በርካታ ሕፃናትን በዘር ለሚተላለፍ ካንሰር መጋለጣቸው በምርመራ መረጋገጡን ቢቢሲ ዘግቧል።

ከምርመራው ግኝቶች መካከል አስገራሚው የግለሰቡ ዘር ወደ 14 አገራት መላኩ እና ቢያንስ 197 ልጆች እንዲወለዱ ማድረጉ ነበር።

የምርመራው ግኝት በወንዴ ዘር ፈሳሽ ልገሳ ዘርፍ እምብዛም የማያጋጥምን ክስተት ይፋ አድርጓል።

የዘር ልገሳ የትዳር አጋራቸው መካን በመሆናቸው፣ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ውስጥ በመሆናቸው አሊያም አጋር ስሌላቸው መውለድ ያልቻሉ ሴቶችን እናት እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው።

ያለውን ክፍተት በመሙላትም ትልቅ ንግድ ሆኗል። ይህ ንግድ ዋነኛ የዘር ፈሳሽ ላኪ የሆነችው ዴንማርክ በምትገኝበት አውሮፓ በ2033 ከ2 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ የገበያ ዋጋ እንደሚኖረው ይገመታል።

ለመሆኑ ለምንድን ነው አንዳንድ ለጋሾች የብዙ ልጆች አባት እየሆኑ ያሉት? "እጅግ ተፈላጊ" የሚባለውን የዴንማርካውያን የዘር ፈሳሽንስ ዝነኛ ያደረገው ምንድን ነው? ዘርፉስ ቁጥጥር ያስፈልገው ይሆን?

አብዛኛዎቹ ወንዶች ለዘር ልገሳ ብቁ አይደሉም

ይህንን የምታነቡ ወንዶች ይህንን ስንነግራችሁ እናዝናለን። ሆኖም የዘር ፈሳሻችሁ ጥራት ለጋሽ ለመሆን ብቁ ላያደርጋችሁ ይችላል። ለዚህ ብቁ የሚሆኑት ከ100 በጎ በፈቃደኛ ለጋሾች ከአምስት ያነሱት ብቻ ናቸው።

ወንዶች ለልገሳ ብቁ ለመሆን በመጀመሪያ በቂ ቁጥር ያላቸው የዘር ፈሳሽ ናሙና ማመንጨት ይኖርባቸዋል። እነዚህ የዘር ፈሳሾች ምን ያህል መዋኘት እንደሚችሉ እንዲሁም እንቅስቃሴ እና ቅርጻቸውን የተመለከተ ግምገማን ማለፍ የግድ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ በማቀዝቀዣ ውስጥ ሲቀመጡ ምን ያህል መቆየት እንደሚችሉ እና በዘር ባንክ መቀመጥ ይችሉ እንደሆነ መረጋገጥ አለበት።

መካን አለመሆን ወይም የስድስት ልጆች አባት መሆን የዘር ፈሳሽ ለመለገስ ብቁ የሚያደርግ መመዘኛ ነው።

የዘር ፈሳሽ ልገሳን በተመለከተ ያሉት ሕጎች እንደየ አገራቱ ይለያያሉ።

በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ለጋሾች ከ18 እስከ 45 የዕድሜ ክልል ውስጥ መሆን፣ እንደ ኤችአይቪ እና ቂጥኝ ካሉ በሽታዎች ነጻ መሆን አለባቸው።

እንዲሁም በዘር የሚተላለፉ በሽታዎችን ከሚያስከትሉ እንደ ሳንባ፣ የምግብ ልመት ሥርዓት ላይ ጉዳት የሚያስከትል - ሲይስቲክ ፋይብሮሲስ፣ የነርቭ ሥርዓት ላይ ጉዳት የሚያደርስ በሽታ እና ጤናማ ያልሆነ የደም ሴሎች - ሲክል ሴል ካሉ በሽታዎች ነጻ መሆን ይጠበቅባቸዋል።

በዚህም ምክንያት በአጠቃላይ መለገስ የሚችሉ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ነው። ይህም በዩኬ ጥቅም ላይ ከሚውለው ግማሽ የሚሆነው የዘር ፈሳሽ ከሌላ አገር እንዲገባ አድርጓል።

የለጋሾች ቁጥር ማነስ ግን በርካታ ሕጻናት እንዲወለዱ ከማድረግ አልከለከለም። ምክንያቱም ከአንድ እንቁላል እንዲዋሃድ ለማድረግ የሚበቃው አንድ የወንዴ ዘር ቢሆንም በአንድ ጊዜ አንድ ወንድ የሚረጨው የዘር ፈሳሽ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠር ነው።

ወንዶች የዘር ፈሳሻቸውን ለመለገስ ወደ ክሊኒኮች መምጣት የሚጠበቅባቸውም በሳምንት አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ብቻ ነው። ይህንንም ለብዙ ወራት ሊያደርጉት ይችላሉ።

በመካንነት እና ዘረ መል ላይ የሚሠራው 'ፕሮግረስ ኢጁኬሽናል ትረስት' የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት ሳራህ ኖርክሮስ እንደሚሉት የለጋሾች እጥረት መኖር የዘር ፈሳሽ ባንኮች እና የመካንነት ሕክምና ክሊኒኮች ያለውን ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ መስፈርቱን ያሟሉ እና በእጃቸው ያሉትን ለጋሾች ደጋግመው እንዲጠቀሙ አስገድዷቸዋል።

'አንዳንድ የዘር ፈሳሾች እጅግ ተፈላጊ ናቸው'

ጥቂት ለጋሾች ቢኖሩም ካሉት ውስጥ ደግሞ የተወሰኑ ወንዶች የዘር ፈሳሽ ከሌሎቹ ተመራጭ ናቸው።

ለጋሾች በግምት አይደለም የሚመረጡት። ልክ መተግበሪያዎች ላይ የፍቅር አጋር ለመፈለግ ከሚደረገው ሒደት ጋር ተመሳሳይ ነው። መሥፈርታቸውን ተመልክተው የሚስማማቸውን ይመርጣሉ።

እንደ የዘር ፈሳሽ ባንኩ፤ የለጋሾቹን ፎቶዎች መመልከት፣ ድምጻቸውን መስማት፣ ምን ዓይነት ሥራ እንደሚሠሩ፣ ምን ሙያ ላይ እንደተሰማሩ እንዲሁም ቁመታቸውን፣ ክብደታቸውን እና ሌላም ሌላም ማየት እና ማወዳደር ይችላሉ።

በሸፊልድ የዘር ፈሳሽ ባንክን የሚያስተዳድሩት የወንዶች የመካንነት ባለሙያ ፕሮፌሰር አላን ፓሲ "ወርቃማ ፀጉር ካላቸው፣ አንድ ሜትር ከ93 ሴንቲ ሜትር ቁመት ካላቸው፣ ስፖርተኛ ከሆኑ፣ የሙዚቃ መሣሪያ የሚጫወቱ ከሆነ፣ ሰባት ቋንቋዎችን መናገር ከቻሉ፤ እጅጉን ተፈላጊ ናቸው" ሲሉ በምሳሌ ያስረዳሉ።

በመሆኑም ሰዎች የሚሆናቸውን እና የሚመርጡትን ለጋሽ ለማግኘት ገጾችን ያገላብጣሉ።

የዴንማርካውያን የዘር ፈሳሽ ለምን ተፈላጊ ሆነ?

ዴንማርክ በዓለማችን ትላልቅ የዘር ፈሳሽ ባንኮች የሚገኙባት አገር ናት። የዘር ፈሳሻቸው ጠንካራ ልጆችን ይፈጥራሉ የሚል ጥሩ ስምም አግኝታለች።

0.5 ሚሊ ሊትር የዘር ፈሳሽ ከ100 እስከ 1000 ዩሮ የሚያስከፍለው ስርዮስ ኢንተርናሽናል የተባለ የዘር ፈሳሽ ባንክ መሥራች የሆኑት የ71 ዓመቱ ኦል ሾው፣ በዴንማርክ የዘር ፈሳሽ ልገሳ ባህል ከሌሎች አገራት የተለየ እንደሆነ ይናገራሉ።

ሕዝቡ እንደ አንድ ትልቅ ቤተሰብ የሚመሰል ነው የሚሉት ሾው፣ "ልገሳ ማድረግ ያን ያህል ነውር አይደለም፤ ሲጋራ የሚያጨሱትም ጥቂት ናቸው፣ ራስ ወዳድ ሕዝቦች አይደሉም፤ ለሌላው ሰው ያስባሉ። በርካታ የዘር ፈሳሽ ለጋሾች ደምም ይለግሳሉ" ብለዋል።

አገሪቷን የዘር ፈሳሽ ወደ ውጭ ከሚልኩ ጥቂት አገራት መካከል አንዷ ያደረጋትም ይህ የሕዝቦቿ ባህርይ ነው ይላሉ ሾው።

ሆኖም የዴንማርካውያን የዘር ፈሳሽ ከዘር ጋር በተያያዘም በጣም ተፈላጊ እንደሆነ ይናገራሉ።

ስቹዎ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ዴንማርካውያን በተፈጥሮ ያላቸው ሰማያዊ የዐይን ቀለም እና ወርቃማ ቀለም ያለው ፀጉር ተፈላጊ ነው። ይህ ማለት ከሁለቱ ወላጆች የሚገኘው ዘር በልጆች እንዲወረስ ይፈልጋሉ።

ሾው እንደሚሉት የዘር ፈሳሽ ልገሳ ፈልገው የሚመጡት ያላገቡ፣ በከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ላይ ያሉ በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሴቶች ናቸው። ከሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች 60 በመቶውን የሚሸፍኑትም እነዚህ ሴቶች ናቸው።

ድንበር ተሻጋሪ የዘር ፈሳሾች

በቅርቡ የታተመው በዘር ፈሳሽ ልገሳ ላይ የተሠራው ምርመራ በዴንማርክ በሚገኘው ከአውሮፓውያን ባንክ የተሰበሰበ የአንድ ግለሰብ የዘር ፈሳሽ እንዴት እንደተሰበሰበ እና በ14 አገራት ወደሚገኙ 67 የመካንነት ክሊኒኮች እንዴት እንደደረሱ ያሳያል።

አገራት የአንድ ወንድ የዘር ፈሳሽ ምን ያህል ጊዜ ጥቅም ላይ መዋል እንደሚችል የየራሳቸው ሕጎች አላቸው።

እነዚህ ሕጎች አንዳንድ ጊዜ ከአጠቃላይ የልጆች ቁጥር ጋር የሚገናኙ ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የሚለገሱ እናቶችን ቁጥር ይወስናሉ። በመሆኑም እያንዳንዱ ቤተሰብ እስከሚፈልጉት ድረስ ከአንድ ለጋሽ ልጆች ሊኖራቸው ይችላል።

ሆኖም እነዚህ ወሰኖች የሚያከራክሩ ናቸው።

ገደቡ ያስፈልጋል የሚሉ ወገኖች ዋነኛ መከራከሪያ ዝምድና እንዳላቸው የማያውቁ ልጆች የፍቅር ግንኙነት መሥርተው ልጆች እንዳይወልዱ፣ እንዲሁም ከሌላ አባት የሚወለዱ ልጆች እንዳይኖሩ ያደርጋል የሚል ነው።

ሆኖም አገራት የየራሳቸውን ሕግ ብቻ ስለሚከተሉ የአንድ ለጋሽ የዘር ፈሳሽ በጣልያን፣ በስፔን እና በኔዘርላንድስ ጥቅም ላይ እንዳይውል የሚከለክል ምንም ዓይነት ዘዴ የለም።

ይህም አንድ ለጋሽ በሕግ የበርካታ ሕጻናት አባት ሊሆን የሚችልበትን ሁኔታ ፈጥሯል።

"በርካታ ተቀባዮች እና ለጋሾች፣ የአንድ ለጋሽ የዘር ፈሳሽ በሌሎች አገራት ሕጋዊ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል ግንዛቤው የላቸውም። ይህ እውነታ ሊብራራላቸውም ይገባል" ብለዋል- ሳራህ ኖርክሮስ።

ይህም ከአንድ ለጋሽ የሚወለዱ ሕፃናትን ቁጥር እንደሚቀንስ ያስረዳሉ።

ከአንድ የዘር ፈሳሽ ለጋሽ ከተወለዱ 197 ልጆች መካከል በአንዳንዶቹ ላይ ካንሰር ሊያስከትል የሚችል ዘር ማስተላለፉን በተመለከተ ለተካሄደው ምርመራ ምላሽ የሰጡት የቤልጂየም ባለሥልጣናት፣ ድንበር ተሻጋሪ የዘር ፈሳሾችን ለመቆጣጠር የአውሮፓ ኮሚሽን፣ አውሮፓን በአንድ የሚያካልል የለጋሾች ምዝገባ እንዲያቋቁም ጥሪ አቅርበዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫንድንብሩክ "ዘርፉ ፈር እየለቀቀ ነው፤ ቤተሰቦች ልጅ እንዲኖራቸው የሚያደርገው የዘርፉ ተልዕኮ ንግድ ሆኗል" ብለዋል።

የአውሮፓ የሥነ ተዋልዶ እና ጽንስ ማኅበር በበኩሉ በአውሮፓ ኅብረት አንድን ለጋሽ መጠቀም የሚችሉት 50 ቤተሰቦች እንዲሆኑ እንዲወሰን ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።

በዚህ ምክር ሃሳብ መሠረት አንድ ተቀባይ ቤተሰብ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ልጅ እንዲኖር ከፈለጉ አንድ ለጋሽ ከ100 በላይ ልጆች ይኖሩታል ማለት ነው።

በዘር ፈሳሽ ልገሳ የሚጸነሱ ልጆች ላይ የሚፈጠረው ተፅዕኖንም በተመለከተ ስጋቶች ሲገለጹ ቆይተዋል።

አንዳንዶቹ ደስተኛ ሊሆኑ ቢችሉም ሌሎች ደግሞ በዘር ፈሳሽ ልገሳ መፈጠራቸውን እና በመቶዎች የሚቆጠሩ በግማሽ የሚዛመዷቸው እህት እና ወንድሞች እንዳላቸው ሲያውቁ ሊጨነቁ ይችላሉ።

ይህ የዘር ፈሳሻቸው በስፋት እንደተሠራጨ ለማያውቁት ለጋሾቹም የሚሠራ ነው።

እነዚህ ጉዳዩች በይበልጥ ጎልተው የሚታዩት በዘረ መል ምርመራ ወቅት እና ሰዎች ልጆቻቸውን፣ እህት ወንድሞቻቸውን፣ ለጋሾችን ሊፈልጉ በሚችሉባቸው የማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ነው።

በዩናይትድ ኪንግደም ግን የለጋሾች ስም በድብቅ አይያዝም። በመሆኑም ልጆች የአባታቸውን ማንነት ማወቅ የሚችሉበት ይፋዊ አሠራሮች አሉ።

ሲርዮስ ሾው እንደሚሉት በዘር ፈሳሽ ለጋሾች ላይ ተጨማሪ ገደቦችን መጣል ቤተሰቦችን "ግላዊ መረጃ ከቁጥጥር ውጪ ወደ ሆነ እና ወደ ሌላ ገበያ ፊታቸውን እንዲያዞሩ" ሊያደርግ ይችላል።

በላንካስተር ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ሥነ ምግባር ባለሙያ የሆነት ዶክተር ጆን አፕልባይ በበኩላቸው የዘር ፈሳሽን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል በጣም ውስብስብ የሆነ የሥነ ምግባር ጉዳይ ነው ይላሉ።

ከማንነት ጋር፣ ከግላዊነት መረጃ፣ ከፈቃድ፣ ከክብር እና ከሌሎች ጋር የተያያዙ በርካታ ጉዳዮች አሉ የሚሉት ዶክተር አፕልባይ፣ በአንገብጋቢ ፍላጎቶች ውስጥም ቢሆን ይህንን ሚዛናዊ ማድረግ ይገባል ይላሉ።

ዶ/ር አፕልባይ የመካንነት ሕክምና ኢንደስትሪው የለጋሽ የዘር ፈሳሽ ለምን ያህል ጊዜ ጥቅም ላይ መዋል እንዳለበት የመቆጣጠር ኃላፊነት እንዳለበት ይናገራሉ።

"ሆኖም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚደረግ ቁጥጥር ላይ መስማማት በጣም አስቸጋሪ እንደሚሆን አይካድም" ይላሉ።

ከዓለም አቀፍ የዘር ፈሳሽ ለጋሾች ምዝገባ ጋር በተገናኘ ሌሎች የሥነ ምግባር እና ሕጋዊ ተግዳሮቶች ተከትለው እንደሚመጡ ዶ/ር አፕልባይ አክለዋል።