የተጠባቂው አርሴናል ከቼልሲ እና የሌሎች የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ግምቶች

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዋንጫ ጉዞን ከሚወስኑ ጨዋታዎች አንዱ የሆነው የለንደን ደርቢን ጨምሮ የ28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች አርብ ቅዳሜ እና እሑድ እንዲካሄዱ መርሐ ግብር ወጥቶላቸዋል።

በለንደን ደርቢ አርሴናል ቼሊስን ኤምሬትስ ላይ የሚያስተናግድበት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል።

መድፈኞቹ የሊጉ ሻምፒዮን ለመሆን፣ ሰማያዊዎቹ ደግሞ በሚቀጥለው ዓመት በሻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ውጤት ለማግኘት ይፋለማሉ።

የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን ይህንን ጨምሮ የሳምንቱን ጨዋታዎች እንደሚከተለው ገምቷል።

አርብ

ዎልቭስ ከ አስቶን ቪላ

ዎልቭስ ከቀሪ ጨዋታዎች አንጻር በሊጉ የመቆየት ዕድል አለው ቢባልም ከወራጅነት የሚያመልጥ አይመስለኝም።

ዎልቭስ እየተሻሻለ ቢገኝም ይህንን ጨዋታ ቪላ እንደሚያሸንፍ እገምታለሁ።

ቪላ ባለፉት አራት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ በመሆኑ ለሊጉ ዋንጫ እንዳይፎካከር አድርጎታል።

ይህንን ጨዋታ ለማሸነፍ ትልቅ ሥራ ይጠብቃቸዋል።

ግምት፡ 0 - 1

ቅዳሜ

በርንመዝ ከ ሰንደርላንድ

ሰንድርላንድ በኅዳር ወር በርንመዝን አሸንፎ በሊጉ አራተኛ ደረጃ ላይ ቢቀመጥም ከዚያ ወዲህ የቡድኑ አቋም ወርዷል።

ግራኒት ዣካን አገልግሎት ማጣቱ ለውጤቱ መጥፋት አንደኛው ምክንያት ነው።

ተጫዋቹ ባለፈው ሳምንት ወደ ሜዳ መመለሱ በበጎ የሚሳ ይሆናል።

ይህንን ጨዋታ በርንመዝ እንደሚያሸንፍ እገምታለሁ።

ቡድኑ የጎል ዕድሎችን በመፍጠር በኩል ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ግምት፡ 2 - 0

በርንሌይ ከ ብሬንትፎርድ

የበርንሌይ ተጫዋቾች ተፎካካሪ ለመሆን ጥረት እያደረጉ ቢገኙም ቡድኑን በሊጉ ለማቆየት በቂ ላይሆን ይችላል።

ባለፈው ሳምንት ቼልሲን ማሸነፍ የሚችሉበት ዕድል የነበረ ቢሆንም አቻ መለያየታቸውም የሚያስከፋ አይደለም።

ካለፉት 27 ጨዋታዎች አራቱን ብቻ ያሸነፉ ሲሆን በሊጉ ለመቆየት ከቀሪ 11 ጨዋታዎች አምስቱን ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል። ይህንን ደግሞ ማሳካት የሚችሉ አይመስለኝም።

ባለፈው ሳምንት ብሬንትፎርድ በብራይተን ይሸነፋል ብሎ የጠበቀ ባይኖርም ቡድኑ በዚህ ሳምንት ወደ አሸናፊነት እንደሚመለስ እገምታለሁ።

ግምት፡ 0 - 1

ሊቨርፑል ከ ዌስት ሃም

ዌስት ሃም እየተሻሻለ ነው ቢባልም ባለፈው ሳምንት ከበርንመዝ ጋር አቻ መለያየቱ ጥሩ ውጤት አይመስለኝም።

ቡድኑ በኖቲንግሃም ፎረስት እና በቶተንሃም ደካማ ውጤት እየታገዘ ሲሆን ይህንን ጨዋታ ማሸነፉ ትልቅ ውጤት ይሆናል።

ሊቨርፑል ከፎረስት ጋር በነበረው ጨዋታ ጥሩ ባይሆንም ሦስት ነጥብ ማሳካት ችሏል።

ደጋፊዎች አሰልጣኝ አርን ስሎትን ቢጠራጠሩም ቡድኑ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል።

ግምት፡ 2 - 1

ኒውካስል ከ ኤቨርተን

ኤቨርተን ወጥ አቋም እያሳየ ካለመሆኑም በላይ ከሜዳ ውጭ ጥሩ መሆኑን ለመገመት አስቸጋሪ ቡድን ያደርገዋል።

አንቶኒ ጎርደን በጥሩ አቋም ላይ ይገኛል።

ኒውካስል በመጀመሪያው ዙሩ ከሜዳው ውጭ 4 ለ 1 ማሸነፍ ችሏል።

ኤቨርተን ባለፈው ዓመት ከሜዳው ውጭ በማሸነፉ ምክንያት ይህ ጨዋታ በአቻ ውጤት እንደሚጠናቀቅ እገምታለሁ።

ግምት፡ 1 - 1

ሊድስ ከ ማንቸስተር ሲቲ

ይህ ጨዋታ ሲቲ የሊጉ ሻምፒዮን መሆን ከፈለገ ሊያሸንፈው የሚገባው መርሐ ግብር ነው።

ይህንን ጨዋታ ለመገመት በጣም ከባድ ቢሆንም ሲቲ በበላይነት ያጠናቅቃል።

ሲቲ እንደዚህ ቀደሙ የመሐል ሜዳ የበላይነት ባይኖረውም የፊት መስመሩ ግን ድንቅ ነው።

ግምት፡ 1 - 3

እሑድ

ብራይተን ከ ኖቲንግሃም ፎረስት

ብራይተን ባለፈው ሳምንት አስፈላጊ የሚባል ድል ብሬንትፎርድ ላይ አስመዝገቧል።

ፎረስት ከሊቨርፑል ጋር መሸነፍ ያልነበረበት ቢሆንም የፊት መስመሩ ደካማ መሆን በዚህ ጨዋታም የሚጎዳቸው ይሆናል።

ግምት፡ 2 - 0

ፉልሃም ከ ቶተንሃም

ኢጎር ቱዶር በጥሩ ውጤት የቶተንሃም ቆይታቸውን አልጀመሩም።

አሰልጣኙ "መጥፎ ልማድ ያለው ጥሩ ስብስብ" ሲሉ ቡድናቸውን መጥራታቸው የቀድሞውን አሰልጣኝ ቶማስ ፍራንክን በቀጥታ ማጥቃት መስሎ ተሰምቶኛል።

ይህ ቀላል ጨዋታ እንደማይሆንላቸው እገምታለሁ።

ፉልሃም ባለፈው ሳምንት ሰንደርላንድ ከማሸነፉም በላይ በመጀመሪያው ዙር ከሰፐርስ ሦስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል።

ግምት፡ 2 - 1

ማንቸስተር ዩናይትድ ከ ክሪስታል ፓላስ

ማንቸስተር ዩናይትድ በአሰልጣኝ ማይክል ካሪክ ስር ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን አጥቂው ቤንጃሚን ሼሽኮ ተቀይሮ ሲገባ ውጤታማ መሆኑን እያሳየ ይገኛል።

ፓላስ ባለፈው ሳምንት ዎልቭስን ማሸነፍ ቢችልም ከአሰልጣኝ ኦሊቨር ጋልስነር ጋር በተያያዘ ያለው ስሜት አሉታዊ ነው።

ጋልስነር ቡድኑን መልቀቅ የሚፈልጉ ሲሆን ውጥረቱ በየዕለቱ እየጨመረ ይገኛል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ፓላስ ከሜዳ ውጭ ቢየዓሸንፍም አሁን ባለው ሁኔታ ባለሜዳው እንደሚያሸንፍ እገምታለሁ።

ግምት፡ 2 - 0

አርሴናል ከ ቼልሲ

ይህንን ጨዋታ አርሴናል ከማሸነፉ ውጭ ሌላ የሚታየኝ ውጤት የለም።

ቼልሲ የትኛውንም ቡድን መቅጣት የሚችሉ ተጫዋቾች ቢኖራቸውም ጎላቸውን የማስጠበቅ ክፍተት አለባቸው።

መድፈኞቹ ከዎልቭስ ጨዋታ መልስ ከቶተንሃም ጋር ባሳዩት አቋም ደስተኛ ነኝ።

ይህ ጨዋታም በተመሳሳይ አሸናፊ ይጠናቀቃል።

ግምት፡ 2 - 0