ኪም ጆንግ ኡን በድጋሚ ለሰሜን ኮሪያ ገዢ ፓርቲ መሪነት ተመረጡ
የደቡብ ኮሪያ ገዢ የሆነው የሠራተኞች ፓርቲ ኪም ጆንግ ኡንን በድጋሚ ዋና ጸሐፊው አድርጎ መምረጡን አገሪቱ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።
የኪም ቤተሰብ ከአውሮፓውያኑ 1940ዎቹ አንስቶ አምባገነኑን ሥርዓት ሲመራ የነበረ በመሆኑ፤ ሀሳቦችን ያለ ተቃውሞ የሚያጸድው የፓርቲው ምክር ቤት ይህንን ውሳኔ ማሳለፉ እምብዛም የሚያስገርም ነገር ሆኖ አልታየም።
በመንግሥት የሚመራው ‘ኬሲኤንኤ’ የተባለው ዜና ወኪል፤ ሰሜን ኮሪያ በኪም ጆንግ ኡን አመራር ሥር ሆና “መሠረታዊ ለውጥ አስመዝግባለች” ብሏል። “በኒውክሌር ኃይሎቹ” አማካኝነት ያሳየችው “ጦርነትን የመከላከል” እርምጃም “ወሳኝ” እንደሆነ የዜና ወኪሉ ገልጿል።
ሰሜን ኮሪያ ምንም እንኳ ለረጅም ጊዜ የቆየ ዓለም አቀፍ ማዕቀብ የተጣለባት ቢሆንም አሁንም የኒውክሌር አቅሟን መገንባቷን ቀጥላበታለች። በየጊዜውም ክልከላ ተጣለባቸውን የአገር አቋራጭ ሚሳዔሎች ሙከራ ታደርጋለች።
ይሁን እንጂ የአገሪቱ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ያለው ሚስጥራዊነት ሠራዊቱ ምን ያህል እድገት እንዳሳየ መገምገም እንዳይቻል አድርጎታል።
በአውሮፓውያኑ 2011 አባታቸው ከሞቱ በኋላ ሥልጣኑን የተረከቡት ኪም፤ በኒውክሌር ፕሮግራም ላይ በከፍተኛ መጠን ኢንቨስት አድርገዋል። ይህ እርምጃቸውም ሰሜን ኮሪያ ለምዕራቡ ዓለም በተለይም ለአሜሪካ ትልቅ ፈተና እንድትሆን አድርጓታል።
ኪም፤ አራተኛ ቀኑን በያዘው የገዢው ፓርቲ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የአገሪቱን የመሣሪያ ፕሮግራም ቀጣይ ምዕራፍ ይፋ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ስብሰባ ከመጀመሩ አስቀድሞ ሰሜን ኮርያ የኒውክሌር መሣሪያን መሸከም ይችላሉ ያለቻቸውን የሮኬት ማስወንጨፊያዎች ይፋ አድርጋለች።
ባለፈው አስር ዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜ ብቻ የተሰበሰበው የፓርቲው ምክር ቤት ስብሰባውን የጀመረው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ዕለት ነው። የዜና ወኪሉ እንደዘገበው አምስት ሺህ ገደማ የፓርቲው አባላት ተገኝተዋል።
ይህ ስብሰባ፤ ሰሜን ኮሪያን ጉዳይ በትኩረት ለሚከታተሉ አካላት እንኳ ግልጽ ስላልሆነው የአገሪቱ የፖለቲካ ሥልጣን አዋቃቀር ፍንጭ የሚሰጥ ሆኗል።
እጅግ ወሳኝ ፖለቲካዊ ኹነት ተደርጎ የሚቆጠረው ይህ ስብሰባ፤ ከውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እስከ የኒውክሌር ፍላጎቷ ድረስ አገሪቱ ቅድሚያ የምትሰጣቸው ጉዳዮች ምን እንደሆኑ ያመለክታል።