ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዶ/ር ሲሳይ አውግቸው በዋስ ተለቅቀው እየወጡ ሳለ "በቁጥጥር ስር መዋላቸውን" ጠበቃቸው ተናገሩ
በአማራ ክልል ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ ድጋፍ በማድረግ የተከሰሱት ዶ/ር ሲሳይ አውግቸው በዋስ ተለቅቀው ከማረሚያ ቤት ሲወጡ ከማረሚያ ቤት በር ላይ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ጠበቃቸው ለቢቢሲ ተናገሩ።
በእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሠፋ የክስ መዝገብ ከሳምንታት በፊት አንቀጽ ተሻሽሎ ክስ የተመሠረተባቸው ዶ/ር ሲሳይ፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ምድብ ችሎት ፀረ ሽብር እና ሕገመንግሥታዊ ችሎት ሰኞ የካቲት16/2018 ዓ.ም. በ100 ሺህ ብር ዋስ እንዲፈቱ ብይን መስጠቱን ጠበቃቸው አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ተናግረዋል።
የዋስትና መብታቸው የተፈቀደላቸው ተከሳሹ ረቡዕ የካቲት 18/2018 ዓ.ም. ከሰዓት ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሲወጡ "በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን" ጠበቃቸው ተናግረዋል።
የካቲት 18/2018 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ባወጣው መግለጫ ዶ/ር ሲሳይ አውግቸው የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ከማረሚያ ቤት እየወጡ በነበረበት ወቅት "በታጠቁ እና ጭምብል በለበሱ የመንግሥት ኃይሎች መስታወቱ ጥቁር በሆነ መኪና ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በር ላይ ታፍኖ ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዱን ለማረጋገጥ ችለናል" ብሏል።
ጠበቃቸው አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ የዶ/ት ሲሳይ አውግቸው ቤተሰቦችም ተከሳሹ ከማረሚያ ቤት በር ላይ በመኪና መወሰዳቸውን እንዳረጋገጡላቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ጠበቃ ሰለሞን አክለውም በእነ ዶ/ር ወንደውሰን አሰፋ መዝገብ ሁለት ሳምንት በፊት ዐቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን የሰነድ ማስረጃዎች በሚመለከት አስተያየት ለፍርድ ቤቱ ማቅረባቸውን አስታውሰው፤ በዚያም መሠረት "ከ23 ተከሳሾች መካከል ስድስቱ በነጻ እንዲሰናበቱ ሁለቱ ደግሞ በዚያው መዝገብ ላይ አንቀጽ ተቀይሮ ይከላከሉ" የሚል ብይን ተሰጥቶ ነበር ብለዋል።
ዶ/ር ሲሳይ አውግቸው እና አቶ ሞላልኝ አውግቸው የተባሉ ተከሳሾች ላይ የተሻሻለው የክስ አንቀጽ "ዋስትና የማያስከለክል ስለሆነ. . . የዋስትና ይፈቀድልን አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ አቀርበን ነበር" ብለዋል።
ፍርድ ቤቱ ይህንን የዋስትና ጥያቄ ለማየት ለየካቲት 16/2018 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይም ብይን መስጠቱን ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቱ በብይኑ ላይ "49ኛ ተከሳሽ ሞላልኝ ሲሳይን በተመለከተ አማራ ክልል ያለውን ቡድን ሄዶ ሊቀላቀል ይችላል በማለት ዋስትና ሲከለክል፣ ዶ/ር ሲሳይ አውግቸውን ግን የዋስትና ግዴታቸውን አክብረው ሊቀርቡ ይችላሉ በማለት የመቶ ሺህ ብር ዋስትና ፈቅዶ ነበር" ሲሉ ጠበቃው ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ብይኑ የተሰጠው ሰኞ ጠዋት እንደነበር ያስታወሱት ጠበቃው የዶ/ር ሲሳይ ቤተሰቦች እስከ ቀኑ ስድስት ሰዓት ድረስ የተጠየቀውን የዋስትና ገንዘብ ከፍለው የመፈቻ ትዕዛዝ በመያዝ ወደ ማረሚያ ቤቱ ማምራታቸውን ገልጸዋል።
ማረሚያ ቤቱ ሰኞ ዕለት ዋስትና የተፈቀደላቸው ዶ/ር ሲሳይ አውግቸው ከዚህ በፊት የተከሰሱበት መዝገብ መዘጋቱን እንዲሁም ምስክር ሆነው የቀረቡበት መዝገብን በተመለከተ "ምስክር ይሁን ተከሳሽ እንዲጣራ" በመጠየቁ ይህንን ረቡዕ ዕለት ከአራዳ ምድብ ችሎት አጣርተው ለማረሚያ ቤቱ ማሳወቃቸውን ተናግረዋል።
ይህንንም ተከትሎ ዶ/ር ሲሳይ አውግቸው በዋስ ከማረሚያ ቤት ሲወጡ ልብሶቻቸውን ለቤተሰቦቻቸው ሰጥተው እንደነበር የሚያስረዱት ጠበቃው፤ በር ላይ ሲወጡ ግን በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ቤተሰቦቻቸው እንደነገሯቸው ገልጸዋል።
"ከዚያ በኋላ ወደ 10 ሰዓት አካባቢ ደውለውልኝ ቤተሰቦቹ ዶ/ር ሲሳይ አውግቸው ወጥቶ ነበረ። ከበር ላይ ወጥቶ በሆነ መኪና ውስጥ አስገብተውት እንደወሰዱት ነገሩኝ።"
የዶ/ር ሲሳይ አውግቸው ቤተሰቦች ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በር ላይ እየጠበቁት ነበር ያሉት ጠበቃው "ከበር ሲወጣ መኪና ውስጥ አስገብተውት በመስኮት በኩል '...ወደ ፌደራል ፖሊስ እየወሰዱኝ ነው ብሎ አለን' ሲሉ ነገሩኝ"ብለዋል።
ጠበቃው ፌደራል ፖሊስ ጠበቆች ደንበኞቻቸውን ገብተው እንዲያነጋግሩ የሚፈቅደው ሰኞ፣ ረቡዕ እና አርብ መሆኑን በመግለጽ አርብ ዕለት ሄደው ዶ/ር ሲሳይ የዋስትና መብታቸው ተከብሮ እያለ ለምን በድጋሚ እንደተያዙ ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።
ኢህአፓ ረቡዕ ምሽት ባወጣው መግለጫ ገዢው ፓርቲን ብልጽግናን ሰላማዊ ዜጎች፣ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ላይ "የግፍ እስር" ይፈጽማል ሲል ወንጅሎ "በተደጋጋሚ አፈናዎችን" ያደርጋል ብሏል።
ፓርቲው አክሎም ዶ/ር ሲሳይ አውግቸው "በአስቸኳይ በሙሉ ደኅንነት እንዲለቀቁ"፣ በግፍ እስር ላይ ይገኛሉ ያላቸው ዜጎችም "ያለምንም ቅድመ ሁኔታ" በአስቸኳይ እንዲፈታ አሳስቧል።
በእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ ስር ዶ/ር ሲሳይ አውግቸውን ጨምሮ መስከረም አበራ፣ ዳዊት በጋሻው፣ ጎበዜ ሲሳይ፣ ገነት አስማማውን እና በአጠቃላይ 52 ተከሳሾች ተዘርዝረዋል።
ከእነዚህም መካከል 23ቱ በተገኙበት ቀሪዎቹ ግን በሌሉበት ጉዳያቸው እየታየ ነው። ከእነዚህ መካከል ስድስቱ በነጻ እንዲሰናበቱ ተወስኖላቸዋል።
ዶ/ር ሲሳይ አውግቸው ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር በመወገን "የአማራ ክልል ባለሥልጣናትን በመግደል" እንዲሁም "የክልሉን ቀጥሎም የፌደራል መንግሥቱን ሥልጣን በኃይል ለመቆጣጠር በማሰብ የሽብር ድርጊት ፈጽመዋል" በሚል በ2015 ዓ.ም. ክስ ተመሥርቶባቸዋል።