'ተዓምራዊ' የተባለው ከሞተች ሴት በተለገሰ ማሕጸን የተወለደው የመጀመሪያው ሕጻን

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ግሬስ ቤል በ30ዎቹ ዕድሜ ክልል ትገኛለች። የተወለደችው ያለ ማሕጸን ነው። ግሬስ እና የፍቅር አጋሯ ስቲቭ ፖዌል ልጅ እንዲኖራቸው ይመኙ ነበር።

አሁን 'ተአምራዊ' ልጅ አግኝተዋል። ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየች ሴት በተለገሰ ማሕጸን ልጃቸው ሁጎ ተወልዷል።

ሁጎ ከተወለደ 10 ሳምንቱ ነው። ግሬስ "በተአምር የተወለደ ልጅ ነው" ትላለች።

በዩናይትድ ኪንግደም ታሪክ ከሞተች ሴት በተለገሰ ማሕጸን ልጅ ሲወለድ ሁጎ የመጀመሪያው ነው።

ግሬስ እና ስቲቭ የሚኖሩት በኬንት ነው። ማሕጸኗን የለገሰችውን ሴት እና ቤተሰቦቿን ያመሰግናሉ።

"በጣም ደግ እና ለሰዎች የምታስብ" ሲሉ ለጋሿን ያሞካሻሉ። ቤተሰቦቿንም "ታላቅ ስጦታ ሰጥተውናል" ብለዋቸዋል።

ልጁ ሊወለድ የቻለው በኦክስፎርድ እና በለንደን በሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች ጥምረት ነው።

የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎቹ ልጁ "ታሪክ የሚለውጥ ነው" ብለዋል። እንደ ግሬስ ላሉ በርካታ ሴቶች ልጅ የማግኘት ተስፋ የሚሰጥ እንደሆነም ተናግረዋል።

ሁጎ ምዕራብ ለንደን በሚገኘው ክዊን ሻርለስ ኤንድ ቸልሲ ሆስፒታል ነው የተወለደው። ሲወለድ 3 ኪሎ ግራም ነበር።

ግሬስ የተወለደችው ያለ ማሕጸን ስለሆነ የወር አበባ አታይም። ይህ ሁኔታ ኤምአርኬኤች (MRKH syndrome) ይባላል። በዩናይትድ ኪንግደም ብቻ 5,000 ሴቶች ተመሳሳይ እክል ይገጥማቸዋል።

ግሬስ ልጅ መውለድ እንደማትችል የተነገራት በ16 ዓመቷ ነበር።

ጥንዶቹ ልጅ ለማግኘት እንደ አማራጭ የወሰዱት በልገሳ የተገኘን ማሕጸን ለእሷ በመስጠት (womb transplant) ነበር። አልያም የአባትየው የዘር ፍሬ እና የእናት እንቁላል ተደባልቀው በሌላ ሴት ማሕጸን ውስጥ ልጁ እንዲያድግ የማድረግ (surrogacy) መንገድን ለመከተል ሲያስቡ ነበር።

ግሬስ የሌላ ሴት ማሕጸን በቀዶ ሕክምና ሊሰጣት እንደሚችል ሲነገራት "በጣም እንደደነገጠች" እና "እጅግም ደስ እንዳላት" ታስታውሳለች።

የሞተችው ሴት ማሕጸን ለግሬስ በቀዶ ሕክምና እንዲሰጣት የወሰኑት የሟች ቤተሰቦች "ታላቅ ስጦታ አበርክተውልኛል" ትላለች። በተለገሰው ማሕጸን ልጇን እንድትወልድ አስችለዋታል።

"ለጋሼን እና ቤተሰቦቿን ሁሌም አስባቸዋለሁ። ልጃቸው በዚህ ምድር ትልቁ ስጦታ የሆነውን የሰው ልጅ ሰጥታኝ እንዳለፈች በማሰብ እንዲጽናኑ እጸልያለሁ። የእሷ ክፍል የሆነ አካል ከእኔ ጋር እስከወዲያኛው ይኖራል" ትላለች ግሬስ።

የማሕጸን ቀዶ ሕክምናው 10 ሰዓት የወሰደ ነው። በአውሮፓውያኑ 2024 በኦክስፎርድ በሚገኘው ቸርችል ሆስፒታል ነው የተከናወነው።

መጀመሪያ ላይ ጥንዶቹ እንቁላል እና የዘር ፍሬ በማቀላቀል የሚከናወን ሕክምና (IVF) አግኝተዋል። ከዚያም ግሬስ ለንደን በሚገኘው ዘ ሊስተር ፈርቲሊቲ ክሊኒክ ሽል (embryo) አግኝታለች።

ሁጎ የተወለደበትን ቅጽበት ግሬስ ሁሌም ታስታውሳለች። የአውሮፓውያኑ የገና በዓል ሰሞን ነው።

"ጠዋት ተነስቼ ትንሽዬ ፊቱን ስመለከት አስታውሳለሁ። ከሕልም የነቃሁ መሰለኝ። በጣም አስደናቂ ነበር።"

በዩናይትድ ኪንግደም 10 የማሕጸን ቀዶ ሕክምና ሙከራዎች እየተካሄዱ ሲሆን፤ የግሬስ ከእነዚህ መካከል አንዱ ነው።

እስካሁን ሦስት ቀዶ ሕክምና ቢደረግም የመጀመሪያው ልጅ ሁጎ ነው።

በአውሮፓውያኑ በ2025 በሕይወት ካለች ሴት በተለገሰ ማሕጸን ኤሚ የተባለች ሕጻን ተወልዳለች።

በ2023 በተደረገ የማሕጸን ቀዶ ሕክምና አማካኝነት የኤሚ እናት ከታላቅ እህቷ የተሰጣትን ማሕጸን አግኝታለች።

ከቤተሰብ አባላት በተለገሱ ማሕጸኖች አምስት ቀዶ ሕክምናዎች ለማከናወን ዕቅድ ተይዟል።

ያለ ማሕጸን ለተወለዱ ሴቶች ተስፋ

ሁለቱ ሕጻናት ኤሚ እና ሁጎ በተመሳሳይ ሆስፒታል ነው የተወለዱት።

ሕጻናቱ እንዲወለዱ ያስቻሉት የሕክምና ባለሙያዎች ለዓመታት ምርምር አድርገዋል።

በኢምፔሪያል ኮሌጅ ኸልዝኬር የሚሠሩት የማሕጸን ሕክምና ባለሙያው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ስሚዝ የማሕጸን ቀዶ ሕክምና ላይ ጥናት የጀመሩት ከ25 ዓመታት በፊት ነው።

ፕሮፌሰር ሪቻርድ ከዓመታት ምርምር በኋላ ሁጎ ሲወለድ ማየት ችለዋል።

"በሒደቱ ብዙ ሰዎች ተሳትፈዋል። በማሕጸን ቀዶ ሕክምናው እንዲሁም ልጁ ሲወለድ አግዘዋል" ይላሉ።

ባለሙያው 'ቻሪቲ ውምብ ዩኬ' የተባለ ተቋም መሥርተዋል። ሁጎ እንዲወለድ ባደረጉት እገዛ ምክንያት የልጁ ወላጆች ደስተኛ ናቸው።

ለልጃቸው ከሰጡት ስም አንደኛው ዶክተሩን ለማመስገን በሚል ሪቻርድ ሆኗል።

ጥንዶቹ ሁለተኛ ልጅ ለመውለድ ከወሰኑ ሙከራው ይቀጥላል። ከዚያ በኋላ ለግሬስ የተሰጠው ማሕጸን በቀዶ ሕክምና ይወጣል።

የሰውነቷ በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት የተለገሳት ማሕጸን ላይ ጥቃት እንዳያደርሱ ለመከላከል ዕድሜ ልኳን መድኃኒት መውሰድ ይጠበቅባታል። ከዚህ የተሻለው አማራጭ ማሕጸኑን ከሰውነቷ በቀዶ ሕክምና ማውጣት ነው።

የቀዶ ሕክምና ባለሙያዋ ኢዛቤል ኩዊንጋ እንደሚሉት የሁጎ መወለድ "አስደሳች ዜና" ነው። በዘርፉ ለሚደረግ ምርምር አዲስ ምዕራፍ የከፈተ እንደሆነ ይገልጻሉ።

"በመላው አውሮፓ ከሞተች ሴት በተለገሰ ማሕጸን ልጅ መውለድ የቻሉ ሴቶች በጣም ጥቂት ናቸው" ይላሉ።

የማሕጸን ቀዶ ሕክምና ለሌሎችም ሴቶች መፍትሔ የሚሰጥ እንዲሆን ማድረግ ይሻሉ። ያለ ማሕጸን የተወለዱ ሴቶች፤ ልጅ የማግኘት ተስፋ እንዲኖራቸውም ይሠራሉ።

በተለገሰ ማሕጸን የሚወለዱ ልጆች ማሕጸኑን ከለገሰችው ሴት ጋር የሚያስተሳስር የዘረ መል መዋቅር የላቸውም።

በመላው ዓለም በተካሄዱ ከ100 በላይ የማሕጸን ቀዶ ሕክምናዎች ከ70 በላይ ሕጻናት ተወልደዋል።

ማሕጸን መለገስ እንደ ልብ እና ኩላሊት መለገስ አይደለም። በፈቃደኛነት ላይ የተመሠረተ መሆኑ የሚረጋገጥበት የራሱ ሒደት አለው።

በዩናይትድ ኪንግደም ሰዎች ከመሞታቸው አስቀድሞ የሰውነት ክፍላቸውን መለገስ እንደማይፈልጉ ካልተናገሩ ከኅልፈታቸው በኋላ ለጋሽ እንደሆኑ ተደርጎ ይወሰዳል።

ለግሬስ የልጃቸውን ማሕጸን የለገሱት ወላጆች ማንነታቸው እንዲገለጽ አልፈለጉም። ሆኖም "በጣም ደስተኛ ነን" ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል።

"ልጃችን የሰውነት ክፍሏን በመለገስ ለሌሎች ወላጆች ተስፋ፣ መዳን እና ጊዜን ሰጥታለች" ብለዋል።

ልጃቸው ሌሎች አራት የሰውነት ክፍሎቿንም ለተለያዩ ሰዎች ለግሳለች።