ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዘንድሮው የረመዳን ወር ረዥም እና አጭር የፆም ሰዓታት የሚኖራቸው አገራት የትኞቹ ናቸው?
በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ቅዱስ የሆነው የረመዳን ወር ረቡዕ ወይም ሐሙስ (የካቲት 11 ወይም 12/2018 ዓ.ም) ይጀምራል።
እምነቱ የጨረቃ ዑደት ላይ የተመሠረተ የቀን አቆጣጠር ስለሚጠቀም የረመዳን ወር የሚጀመርበት ጊዜ በየዓመቱ ይቀያየራል። በየዓመቱ በአስራ አንድ ቀናት ወደ ኋላ እየተገፋ ይሄዳል።ባለፈው ዓመት የረመዳን ወር የጀመረው የካቲት 23 ቀን ነበር።
በረመዳን ወር አብዛኛዎቹ የእምነቱ ተከታዮች በየቀኑ ጀምበር ወጥታ እስከምትጠልቅ ድረስ ከ29 እስከ 30 ለሚሆኑ ቀናት ይጾማሉ።
በቀን ውስጥ ለሰዓታት ያህል ምግብም ሆነ መጠጥ በአፋቸው አይዞርም። በአብዛኛው ጾምን መፍታት ወይም አለመጾም የሚቻለው ከጤና ጋር በተያያዘ ነው።
የእምነቱ ተከታዮች እንደሚኖሩባቸው የዓለም ክፍሎች እና ወቅቶችም በየቀኑ የሚያሳልፏቸው የጾም ሰዓታት ይለያያሉ። አንዳንዶች በቀን እስከ 20 ሰዓታት ድረስ መጾም ይኖርባቸዋል።
የአገራት መገኛና ወቅቶች ጾም ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩት እንዴት ነው?
በዘንድሮው የረመዳን ወቅት በደቡባዊ ንፍቀ ክበብ የሚገኙ አገራት በበጋ ወቅት ላይ ነው የሚገኙት።በዚህ ወቅት ቀኑ ከሌሊቱ ረዥም ነው። ይህም በክረምት ወራት ከሚውለው የረመዳን ወቅት በበለጠ ለብዙ ሰዓታት እንዲጾሙ ያደርጋቸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ የሚገኙት በክረምት ወቅታቸው ላይ ሲሆኑ፣ በበጋ ወቅት ከሚውለው የረመዳን ወቅት በተለየ በጾም የሚያሳልፉት ሰዓት አጭር ነው።
የቀን እና የሌሊት ርዝመትም ከቦታ ቦታ ይለያያል። በበጋ ወቅት ቀኑ ረዥም ሲሆን፣ በክረምት ደግሞ ከምድር ወገብ እየራቅን በሄድን ቁጥር ሌሊቱ እየረዘመ ይሄዳል።
ለምሳሌ በዚህ የረመዳን ወቅት በደቡባዊ ንፍቀ ክበብ ጥግ ላይ በምትገኘው የቺሊዋ ደሴት ፒዩርቶ ዊሊያምስ ጾም ከማለዳው 12፡30 እስከ ምሽት 3፡00 ድረስ ይዘልቃል።
በኖርዌይ የምትገኘው ሎንግይርባይን ደሴት ደግሞ በዓለማችን ሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ዳርቻ ላይ የምትገኝ ከተማ ወይም ቋሚ መኖሪያ ተደርጋ የምትታሰብ ሲሆን፣ የዘንድሮው የረመዳን ጾም በሚጀምርበት ጊዜ የቀኑ ርዝማኔ ከረፋዱ 4፡00 እስከ 7፡30 ድረስ የሚሸፍን ነው። በዚህም የሚኖራት የጾም ሰዓታት ሁለት ሰዓት ተኩል ብቻ ይሆናል።
በደሴቷ ቀኑ ረዥም እየሆነ በሚመጣበት የረመዳን መገባደጃ የመጾሚያ ሰዓታት ወደ 12 ሰዓት ከ50 ደቂቃ ገደማ ይዘልቃል።
በእንደዚህ ዓይነት ቦታዎች የሚኖሩ ሙስሊሞች ታዲያ የማፍጠሪያ ሰዓታት ከማጣት ወይም ጾማቸውን ከማቋረጥ ይልቅ የመካን ሰዓት አቆጣጠር ይጠቀማሉ።
በሰሜናዊ የዓለማችን ክፍል ደግሞ የረመዳን ወር ሰኔ ወር ላይ ሲውል የጾም ሰዓት ረዥም ሲሆን ታኅሣሥ ወር ላይ ሲውል አጭር ይሆናል።
ይህ ከደቡባዊው ክፍል ጋር ተቃራኒ ነው። በዚህ አካባቢ የረመዳን ወቅት በየዓመቱ ወደ ታኅሣሥ ወር እየተጠጋ ሲመጣ የጾም ሰዓቱ ረዥም እየሆነ ይመጣል።ወደ ሰኔ እየተጠጋ ሲሄድ ደግሞ ያጥራል።
በዓለም ዙሪያ ያሉ ሙስሊሞች በቀን ለስንት ሰዓታት ይጾማሉ?
በአረቡ ዓለም የጾም ሰዓታት በቀን ከ12 እስከ 13 ሲሆኑ፣ የዘንድሮው ረመዳን በቅርብ ዓመታት ውስጥ መካከለኛ ሰዓት ያለው የጾም ወቅት ሆኗል።
በቅዱስ ከተማዋ መካ በረመዳን መጀመሪያ ወቅት ጾም ማለዳ 12፡30 ጀምሮ ምሽት 12፡20 ላይ ያበቃል። በረመዳን ወር መጨረሻ አካባቢ ግን ሰዓቱ በግማሽ ሰዓት ይጨምራል።
አብዛኛው በደቡባዊ ንፍቀ ክበብ የሚኖሩ ሙስሊሞች ጾማቸውን ለመፍታት ወይም ለማፍጠር ብዙ ሰዓታትን መጠበቅ ይኖርባቸዋል።
ለምሳሌ በአርጀንቲና መዲና ቦይነስ አይረስ የሚኖሩ ሙስሊሞች በረመዳን የመጀመሪያ ቀናት በቀን ለ13 ሰዓታት ከ15 ደቂቃ ያህል መጾም ይጠበቅባቸዋል።
የኒውዚላንዷ ኦክላንድም የረመዳን የመጀመሪያ ቀናት በተመሳሳይ የጾም ሰዓታት ይኖራታል።
በሁለቱ ከተሞች በረመዳን ወር መገባደጃ ወቅት የጾም ሰዓታት በአንድ ሰዓት ያህል ይቀንሳል። ምክንያቱም በዚያ ወቅት በደቡብ ንፍቀ ክበብ ያለው የቀን ርዝማኔ ከሌሊቱ ስለሚያጥር ነው። ይህም ፀሐይ የምትቆይበትን ሰዓት ያሳጥራል።
በአብዛኞቹ ሰሜናዊ የዓለም ክፍሎችም በወሩ ውስጥ የሚኖሩ የጾም ሰዓታት ይለዋወጣሉ።
በግሪንላንዷ መዲና ኑክ ረመዳን ሲጀምር የጾም ሰዓታት 9 ሲሆን፣ ወሩ እያለቀ ሲመጣ ከ12 ሰዓት በላይ ይሆናል።
ሆኖም በከፍታ ቦታዎች ላይ ለሚገኙ የዓለም ክፍሎች የዚህ ዓመቱ ረመዳን የዋለበት፣ ቀኑ በረዘመበት በምዕራባውያኑ የበጋ ወራት [ሰኔ እና ሐምሌ] ላይ ከነበረው ጊዜ አንፃር የተሻለ ነው።
በኖርዌይ፣ በሩሲያ እና በግሪንላንድ ረመዳን በበጋ ወቅት በሚውልበት ወቅት ሙስሊሞች እስከ 20 ሰዓታት ሊጾሙ ይችላሉ።
በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ባሉ አካባቢዎች ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የጾም ሰዓታት አጭር ናቸው። ይህም ቅዱሱ ወር ታኅሣሥ ወር ላይ እስከሚውልበት እስከ አውሮፓውያኑ 2031 ድረስ በየዓመቱ እየቀነሰ ይሄዳል።
በደቡባዊ ንፍቀ ክበብ ደግሞ እስከ 2031 ድረስ የጾም ሰዓታት በየዓመቱ እየረዘሙ ይሄዳሉ።
ሙስሊሞች ለምንድን ነው የሚጾሙት ?
በረመዳን ወቅት መጾም ከእስልምና አምስት ምሰሶዎች አንዱ ነው። ጾም መንፈሳዊነትንም ያበረታታል።
በዚህ ወቅት ሙስሊሞች የዕለቱን ጾም ከመጀመራቸው በፊት ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት 'ስሁር' ወይም 'ሰሂር' ይመገባሉ። ስሁር ሌሊት ሶላት የሚሰገድበት ሰዓት ሲሆን፣ በዚህ ወቅት ጿሚዎች ምግብ ይቀምሳሉ።
ከዚያም ፀሐይ እስከምትጠልቅ ድረስ ውሃን ጨምሮ ምንም ዓይነት ምግብም ሆነ መጠጥ አይቀምሱም። ከዚያ ግን አመሻሽ ላይ ጾማቸውን ይፈታሉ ወይም ያፈጥራሉ።
ሁሉም የእምነቱ ተከታዮች እንዲጾሙ ግን አይገደዱም።
እስልምና በጤና ወይም በሌሎች ምክንያቶች ሰዎች ጾማቸውን እንዲፈቱ ወይም እንዳይጾሙ ይፈቅዳል።
ይህም ዕድሜያቸው ያልደረሰ ሕፃናት፣ ነፍሰጡሮች ወይም የምታጠባ ሴት፣ የወር አበባ ላይ ያለች ሴት፣ የታመሙ ሰዎች አሊያም ጤናቸው በጾም ምክንያት የሚታወክ እና በጉዞ ላይ ያሉ ሰዎችን ይጨምራል።
* የፀሐይ መውጫ እና መግቢያ ሰዓታት ምንጭ የአሜሪካ ብሔራዊ የውቅያኖስ እና ከባቢ አስተዳደር -ኤንኦኤኤ የዓለም አቀፍ የክትትል ላብራቶሪ ነው ።