ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጥንታዊቷን ደብረ ታቦር ከተማ ለዓመታት ወደኋላ መልሷታል የተባለው ያልተነገረው ውድመት
በአማራ ክልል ውስጥ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ ከሐምሌ 2015 ዓ. ም. ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ የመንግሥት ተቋማት ውድመት በደብረ ታቦር ከተማ ደርሷል።
በክልሉ ባለፉት ዓመታት የንፁሃን ግድያን ጨምሮ ንብረቶች መውደማቸውን የተለያዩ ሪፖርቶች ያመላከቱ ሲሆን፤ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ በከተሞች ላይ ግን ሰፊ ውድመት ሲደርስ የደብረ ታቦር የተቋማት ውድመት የመጀመሪያው ነው።
ቢቢሲ ያሰባሰባቸው መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በከተማዋ ረቡዕ የካቲት 4/2018 ዓ.ም. ከጠዋት 12 ሰዓት እስከ ቀኑ 10 ሰዓት ገደማ በዘለቀው ግጭት ውስጥ ከቀበሌ አስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች እስከ ዞን መምሪዎች ድረስ 20 የሚደርሱ ተቋማት እና ተሽከርካሪዎች መውደማቸውን መረዳች ችሏል።
ከአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር 100 ኪሎሜትር ገደማ ርቀት ላይ በሚገኘው በደቡብ ጎንደር ዞን ከጥር መጨረሻ አንስቶ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል "ከባድ ውጊያ" ሲደረግ እንደነበር ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የፋኖ ኃይሎች በበኩላቸው በአካባቢው ጠንካራ ጥቃቶችን ፈጽመው ወረዳዎችን ከመንግሥት ኃይሎች በማስለቀቅ መቆጣጠራቸውን አስታውቀው ነበር።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የፋኖ ታጣቂዎች የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና ከተማ የሆነችውን ደብረ ታቦር ከተማን ለመቆጣጠር የካቲት 4/2018 ዓ. ም. ማለዳ ጥቃት መክፈታቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ በወቅቱ ተናግረዋል።
በዕለቱ ከንጋት አንስቶ ታጣቂዎቹ በከፈቱት ጥቃት ከሁለቱም ወገን የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ አስካሁን የወጣ ይፋዊ አሃዝ ባይኖርም በከተማዋ ባሉ ተቋማት ላይ ሰፊ ቁሳዊ ውድመት ማድረሱን ቢቢሲ ከተለያዩ አካላት ያሰባሰባቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
በርካታ ነዋሪዎች በከተማዋ ዙሪያ በነበረው የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ስጋት እንዲሁም ግጭቱ ጠዋት ላይ በመቀስቀሱ አብዛኛው የከተማዋ ማኅበረሰብ እንቅስቃሴው በቤቱ ውስጥ ተገድቦ እንደነበር ተናግረዋል።
ረቡዕ ዕለት የተቀሰቀሰውን የሁለቱ ወገኖች ግጭት "ከፍተኛ ጦርነት" ሲሉ የገለጹት የከተማዋ ከንቲባ አቶ ደሴ መኮንን ውጊያው በፋኖ እና በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች መካከል መሆኑን ተናግረዋል።
አንድ የደብረ ታቦር ነዋሪ በማኅበራዊ የትስስር ገፆች ምሥሎችን ካዩ በኋላ ደጅ ላይ ወጥተው ጥቁር ጭስ ወደ ሰማይ "ሲግተለተል" መመልከታቸውን ገልጸዋል።
ጭሱን ሲመለከቱ "ተደንግጠናል፤ ሁሉም [ሰው] ደንግጧል። ጥሩ ስሜት አልነበረንም" ሲሉ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳሉ።
ሌላ ነዋሪ በከተማዋ ዳርቻ ላይ የሚገኙ ተቋማት ቀኑን ሙሉ ሲቃጠሉ እንደነበር ተናግረዋል።
ሌላ ነዋሪ ደግሞ ሁለት ፖሊስ ጣቢያዎችን ጨምሮ አምስት የመንግሥት ተቋማት "ሙሉ ለሙሉ አመድ" ሆነው መውደማቸውን በዐይናቸው እንዳዩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ከሌሎች ነዋሪዎች እና ከከተማው አስተዳደር ባገኘው መረጃ በአራት የመንግሥት መዋቅር ሥር የሚገኙ ተቋማት፣ አምቡላንሶች፣ ተሽከርካሪዎች፣ ማሽኖች እና ሰነዶችን ጨምሮ የቢሮ መገልገያ ቁሳቁሶች የቃጠሎው ሰለባዎች መሆናቸውን መገንዘብ ችሏል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ለወረዳዎች የሚከፋፈል መድኃኒት ማከማቻ ያለውን ጤና መምሪያ እና በጣሊያን የወረራ ጊዜ የተገነቡ የዞኑ መሬት፣ ሲቪል ሰርቪስ እና ፖሊስ መምሪያዎችን ጨምሮ ስድስት ቢሮዎች መቃጠላቸውን እማኞች ተናግረዋል።
አንድ ግቢ ውስጥ "የድሮው ከንቲባ ቢሮ" ተብሎ በሚጠራ ሥፍራ የሚገኙ የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር ስድስት ቢሮዎች እንዲሁም የገብርዬ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያን ጨምሮ ሁለት የአስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች መቃጠላቸውን ምንጮች ተናግረዋል።
ደብረ ታቦር በዙሪያዋ ያሉ ቀበሌዎችን በወረዳነት ያቀፈው የፋርጣ ወረዳ ዋና መቀመጫ ስትሆን፤ የዚህ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ እና ገቢዎች ቢሮን ጨምሮ በአጠቃላይ አራት ተቋማት እና በርካታ ተሽከርካሪዎች መውደማቸውን ቢቢሲ ተረድቷል።
በዚህ ወረዳ ዙሪያ የሚገኙ የግለሰብ ቤቶችም መቃጠላቸውን ነዋሪዎች ሲናገሩ፤ የከተማዋ ከንቲባ አቶ ደሴ መኮንን አራት የግለሰብ ቤቶች መቃጠላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አንድ ነዋሪ ማንነታቸውን መግለጽ ያልፈለጓቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊ የመኖሪያ ቤት እንዲሁም "የዞን አመራሮች መጠለያ" የተባለ እንግዳ ማረፊያም መቃጠሉን ጠቁመዋል።
የደብረ ታቦር ከተማ ከንቲባ አቶ ደሴ ውድመቱን "አሳዛኝ እና የማይጠበቅ" ብለውታል።
"ከባድ [ጉዳት] ነው የደረሰው። ማኅበረሰቡ አገልግሎት የሚያገኝባቸው ቦታዎች ናቸው፤ ፋይናንስም፣ ፖሊስም፣ ሚሊሻም። ማኅበረሰቡ ጥሩ ስሜት የለውም። ምክንያቱም የማኅበረሰቡ ሰነድ ነው የጠፋው፤ የተቃጠለው። የመረበሽ ስሜት አለ" ሲሉ አንድ ነዋሪ ስለ ውድመቱ ተናግረዋል።
ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው ውድመቱን "አሳዛኝ እና አሳፋሪ" ብለው የገለጹት ሲሆን፤ ከባድ መሣሪያዎች ጥቅም ላይ ቢውሉ ኖሮ ከዚህ የከፋ ውድመት ይከሰት ነበር ብለዋል።
ማኅበረሰቡ እንደ ከተማዋ ጥንታዊነት እና ታሪካዊነት ደብረ ታቦር አላደገችም የሚል "ቁጭት" እንዳለው ያስታወሱት ሌላ ነዋሪ፤ በዚህ ላይ ይህን ያህል ውድመት መድረሱ አሉታዊ ስሜት ማሳረፉን አክለው ገልጸዋል።
ሌላም ነዋሪ ይህኑ ሐሳብ በመደገፍ "ከተማው አሁን ካለበት ወደ ኋላ 10 ዓመት እና 15 ዓመት እንደተመለሰ ነው የታዘብነው። . . .ከዚህ በኋላ የትኛው መንግሥት ነው መልሶ የሚገነባው? ከተማዋን ወደ ነበረበት የሚመልሰው?" ሲሉ ጠይቀዋል።
የተቋማቱን ውድመት ወጥተው መመልከታቸውን የጠቆሙ ሌላ ነዋሪ ውድመቱ "ሆን ተብሎ" የተፈጸመ የእሳት ቃጠሎ ነው ብለዋል።
ለደብረ ታቦር ውድመት ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች እርስ በርስ እየተወነጃጀሉ ይገኛሉ።
ቢቢሲ ቃለጠሎው ሆን ተብሎ የተፈጸመ ይሁን፤ በማን ተፈጸመ የሚለውን በገለልተኝነት ማረጋገጥ አልቻለም።
ቢቢሲ ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ዕለት ጀምሮ ያነጋገራቸው በርካታ ነዋሪዎች ከስምንት እስከ 10 የገመቷቸው የድሮን ጥቃቶች መፈጸማቸውን ጠቁመዋል።
ሁለት ነዋሪዎች የድሮን ጥቃቶቹ ከተማ ውስጥ ሳይሆን ወጣ ባሉ አካባቢዎች ላይ መፈጸማቸውን ሲናገሩ፣ የከተማዋ ከንቲባም ጥቃቱ ከተማ ውስጥ አለመፈጸሙን ጠቁመዋል።
በከተማዋ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የደረሰውን ውድመት መጠን እንዲሁም ለመልሶ ግንባታ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማወቅ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን የደብረ ታቦር ከንቲባ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነዋሪዎች ውድመት ከደረሰ ከሳምንት በኋላ ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማት እየተጸዱ መሆኑን ተናግረዋል።
ደብረ ታቦር "የድንጋጤ እና የሐዘን" ስሜት ውስጥ ተውጣ እንደነበር አንድ ነዋሪ ተናግረዋል። "የሰው፣ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የተገታ ነበር። ሰው የመደንገጥ እና ያለመረጋጋት ስሜት ውስጥ ነበር። አሁን ወደ ሥራ የመግባት፤ የመረጋጋት ነገር አለ" ብለዋል።