ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከሰሞኑ በደብረ ታቦር ከተማ የተከሰተው ምንድን ነው?
በአማራ ክልል የደቡብ ጎንደር ዞን መቀመጫ በሆነችው ደብረ ታቦር ከተማ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል በተካሄደ ግጭት የሕይወት እና የንብረት ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች ተናገሩ።
በከተማዋ ከፍተኛ ውድመት ያደረሰው ግጭት የተከሰተው በዞኑ በሚገኙ ሌሎች አካባቢዎች ጭምር ውጥረት ከነገሰ ከአንድ ወር ገደማ በኋላ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ እና ቢቢሲ ያነጋገራቸው አራት ነዋሪዎች፣ ረቡዕ የካቲት 4/2018 ዓ.ም. ከማለዳው 12፡00 ሰዓት እስከ 1፡00 ሰዓት በከተማዋ ውስጥ ተኩስ መሰማት እንደጀመረ ተናግረዋል።
እስከ ቀኑ 11፡00 ሰዓት ድረስ የዘለቀ ነው ባሉት በዚህ ግጭት "ፖሊስ ጣቢያዎች እና የመንግሥት ተቋማት ተቃጥለዋል እንዲሁም የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች ሞተዋል።" ብለዋል።
የሟቾቹ ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ባይጠቅሱም የደረሰውን ጉዳት "ከባድ" ሲሉ ገልጸውታል።
ሌላ ነዋሪም "የፋርጣ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ሙሉ በሙሉ ወድሟል፤ ቄስ አለማየሁ የሚባል አካባቢ የሚገኝ የከተማው ፖሊስ ጣቢያ እና የዞኑ ፖሊስ መመሪያ እንዲሁም ማኅበራት የሚባል መሥሪያ ቤት ተቃጥለዋል" ብለዋል።
"የሲቪል ሰርቪስ መምሪያ፣ የዞን ፖሊስ መምሪያ፣ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ የእንግዳ ማረፊያ እንዲሁም በርካታ የፖሊስ ጽ/ቤቶች መቃጠላቸውን" የገለጹ ነዋሪም በበኩላቸው በመንግሥት ተቋማት ላይ የደረሰው ውድመት መጠነ ሰፊ እንደሆነ ተናግረዋል።
"ከአርሶ አደሮች መሣሪያ ተሰብስቦ ተከማችቷል የሚባል ወሬ ስለነበር እርሱን ነው አቃጥለው ወጡ የሚባለው" ሲሉም ምክንያቱ ምን እንደሆነ ጠቁመዋል።
በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የድሮን ጥቃቶች መፈፀማቸውንም ነዋሪዎቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አንድ ነዋሪ "ጥቃቱ በከተማው ዳርቻዎች ላይ ነው የተፈፀመው፤ ኪዳነ ምህረት፣ አባ አረጋዊ አካባቢ የድሮን ጥቃት ተፈፅሟል። በአካባቢው የፋኖ ኃይል ነበር። በእነሱ ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት ተፈፅሟል" ሲሉ ድምጽ ይሰማቸው እንደነበር ገልጸዋል።
ከዚህም ባሻገር በወቅቱ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አራት የሚደርሱ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪው አክለዋል።
በግጭቱ ስለደረሰው የጉዳት መጠን ከአካባቢው መስተደዳር የተገለጸ ነገር የለም። ቢቢሲም ስለክስተቱ ከገለልተኛ ወገን አላረጋገጠም።
ከአካባቢው አስተዳዳሪዎች እና የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ዝርዝር መረጃ ለመጠየቅ ያደረገው ጥረትም አልተሳካም።
የከተማዋ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ "ወራሪ" ሲል የገለፃቸው ኃይሎች በመንግሥት እና በግለሰብ ንብረት ላይ ውድመት እና ዘረፋ መፈፀማቸውን ገልጿል።
ታጣቂ ኃይሎቹን በስም ያልጠቀሰው አስተዳደሩ ታጣቂ ቡድኑ "ብዛት ያላቸው የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት፣ የደቡብ ጎንደር ዞን እና የፋርጣ ወረዳ ተቋማት በእሳት እንዲቃጠሉ እንዲሁም የኤሌክትሮኒክስ ዕቃ እና ሌሎች ቁሳቁሶች እንዲወድሙ አድርጓል" ብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ አምቡላንሶች እና ተሽከርካሪዎችን እንዳቃጠሉም ገልጿል።
የከተማዋ አስተዳደር በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ በቃጠሎ የወደሙ ተቋማት እና ንብረቶችን ምሥል አጋርቷል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የካቲት 3/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች አገርሽቷል ብሏል።
አካባቢዎቹን በስም ያልጠቀሰው የፓርቲው መግለጫ ባለፉት ጥቂት ጊዜያት ታይቶ የነበረው አንጻራዊ መረጋጋት ከሰሞኑ ወደ ተባባሰ የትጥቅ እንቅስቃሴ መቀየሩን ገልጿል።
በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን ስለግጭቱም ሆነ ደረሰ ስለተባለው ውድመት እስካሁን ያለው ነገር የለም።
ግጭቱ እንዴት ተከሰተ?
ከሁለት ዓመት በላይ በግጭት ውስጥ ባለው የአማራ ክልል ውስጥ የምትገኘው የደብረ ታቦር ከተማ አልፎ አልፎ በታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል በሚከሰት ግጭት እንዲሁም በሰላም እጦት ውስጥ ቆይታለች።
በአካባቢው ተሰማርቶ የነበረው የመከላከያ ሠራዊት በተወሰነ መልኩም ቢሆን በከተሞች አካባቢ ግጭቱ ጋብ ብሎ እንዲቆይ አድርጎ ነበር ይላሉ ነዋሪዎች።
ሆኖም የመከላከያ ሠራዊት ከደቡብ ጎንደር ዞን መውጣቱን ተከትሎ የፋኖ ታጣቂዎች ረቡዕ ዕለት ወደ ከተማዋ እንደገቡ ይናገራሉ።
አንድ ነዋሪ "ባለፈው ሳምንት አርብ (ጥር 29/ 2018 ዓ.ም) መከላከያ ከደቡብ ጎንደር ወጥቶ ነበር። ከዚያም ፋኖዎች በየወረዳው ገቡ። ከዚያም ወደ ዞኑ ገቡ" ብለዋል።
በከተማዋ ዙሪያ ለአንድ ሳምንት ያህል ውጥረት እንደነበር ያስታወሱት ነዋሪው፤ ማክሰኞ ዕለት በሥራ ላይ ሳሉ የፋኖ ታጣቂዎች በመኪና ተጭነው ወደ ከተማዋ እያመሩ እንደሆኑ ሲሰሙ እኩለ ቀን ላይ ሥራቸውን አቋርጠው ወደ ቤት መመለሳቸውን ተናግረዋል።
"በዙሪያው ውጊያ ከተጀመረ አንድ ሳምንት ሆኖታል። ሰኞ ዕለት ማታ ጀምሮ በደብረ ታቦር አለመረጋጋት ነበር። ከዚያ ረቡዕ ጠዋት 1፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ 11፡00 ሰዓት ድረስ ከተማው ግጭት ውስጥ ነበር። የድሮን ጥቃት ነበር። ከሁለቱም ወገን [በፋኖም በሚሊሻም] ብዙ ሰዎች ሞተዋል" ብለዋል።
አብንም ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ በዝርዝር ያለው ነገር ባይኖርም "የአገር መከላከያ ሠራዊትን መነቃነቅ ተከትሎ ሕዝባችንን ለዳግም ሰብዓዊ ቀውስ የሚዳርግ ሁከት ተከስቷል" ሲል የመከላከያ ሠራዊት እንቅስቃሴ እንደነበር አመልክቷል።
አሁን በከተማዋ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
ከተማዋ አሁንም ከስጋት የተላቀቀች ባይሆንም ከረቡዕ አመሻሽ 11፡00 ሰዓት በኋላ ተኩስ አለመኖሩን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የመከላከያ ሠራዊት ወደ ከተማዋ እያመራ እንደሆነ ከተሰማ በኋላ ታጣቂዎቹ ከከተማዋ መውጣታቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
እንደ ነዋሪዎቹ ከሆነ ከተማዋ አሁን ላይ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ትገኛለች።
በግጭቱ ሕይወታቸው ያለፈ የፀጥታ ኃይሎች የቀብር ሥነ ሥርዓት [ሐሙስ] ላይ ይሰማ ከነበረ የተኩስ ድምጽ ባለፈ ምንም ዓይነት የመሣሪያ ድምጽ እንዳልነበር ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
ሐሙስ ዕለት ወደ ከተማ ወጣ ብለው እንደነበሩ የገለጹ ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው አልፎ አልፎ በከተማዋ ሰዎች እና ባጃጆች ሲንቀሳቀሱ እንደሚታዩ፤ ነገር ግን የመንግሥት እና የግል ተቋማት ዝግ ሆነው መዋላቸውን ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ከተማዋ ከረቡዕ አመሻሽ ጀምሮ "ወደ ቀደመ እንቅስቃሴዋ" መመለሷን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ አስታውቋል።
የንግድ ድርጅቶች እና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ሥራ መጀመራቸውንም ጠቅሶ፤ በከተማዋ የነበረውን ሰላም ለመመለስ እንደሚሠራ ገልጿል።
ከተማዋ ከሰሜኑ ጦርነት አንስቶ ሰላም አግኝታ አታውቅም ያሉ አንድ ነዋሪ ግን ኑሯቸው አሁንም የሰቆቃ እንደሆነ ተናግረዋል።
"ነገ ምን እንደሚሆን አናውቅም፤ የፋኖ ታጣቂዎችም የመንግሥት የፀጥታ አካላትም ናቸው የሚያስጨንቁን" ሲሉ አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸውን ገልጸዋል።
"አንደኛው ሲገባ፤ ሌላኛው ሲወጣ በሚፈጠረው ክፍተት የሚገቡ ዘራፊዎች እና ልጆችን ከእናታቸውን ነጥቀው ገንዘብ የሚጠይቁ አጋቾች" እንደሚያሰጓቸውም ነዋሪው አክለዋል።
"የእኛ የአደጋ ጊዜ ስልክ [911] መድሐኒዓለም ብቻ ነው" ሲሉም ለሰላማቸው እምነት የሚጥሉበት አካል እንደሌለ በተስፋ መቁረጥ ተናግረዋል።
በደብረ ታቦር ከተማ ስለተከሰተው ግጭት የአማራ ክልል አስተዳደር እስካሁን ያለው ነገር የለም።
ቢቢሲ እስከ ሐሙስ ምሽት ድረስ ከደቡብ ጎንደር ዞን እና ከደብረ ታቦር ከተማ አስተደዳር ኃላፊዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ስልካቸው ባለመነሳቱ አልተሳካም።