ኖስትራዳመስ፡ የፈረንሳያዊው ኮከብ ቆጣሪ ትንቢቶች ለምን አሁንም ድረስ ተቀባይነት አገኙ?

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በ16ኛው ክፍለ ዘመን የኖረው ኮከብ ቆጣሪ ሙሉ ስሙ ሚሼል ዴ ኖትረዳም ቢሆንም ዓለም የሚያውቀው ግን ኖስትርዳመስ በሚል ነው።

በወረርሽኝ የተጠቁ ሰዎችን የሚያክም የሕክምና ባለሙያ፣ መድኃኒት ቀማሚ እንዲሁም ኮከብ ቆጣሪ ነበር።

በአራት መስመር ስንኞቹ ስለሚመጣው እጅግ አስከፊ የአየር ንብረት መዛባት፣ ስለ የመጨረሻው የዓለም ጦርነት፣ የሰሜንና ደቡብ ዋልታዎች የበረዶ ተራሮች እንደሚቀልጡ ጽፏል።

ከዓመታት በፊት የጻፋቸው ትንቢቶች ዛሬም ድረስ ብዙዎች የሚጠቅሱት፣ እንደ ምልክት የሚጠቀሙበት እና ኖስትርዳመስ ብሎ ነበር የሚሉለት ሰው ነው።

አንዳንዶች ሟርት ነው ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ የለም እውነት የሚሆን የአዋቂ ሰው ትንቢት ነው ሲሉ ይከራከራሉ።

ይህ ፈረንሳዊ በአውሮፓውያኑ 1555 የታተመውን 'Les Prophéties'ን የጻፈ አማተር ኮከብ ቆጣሪ ነበር።

መጽሐፉ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚናገሩትን 942 ምሥጢራዊ ትንቢቶች (ባለአራት መስመር ግጥሞች) ይዟል።

ይህም ብዙውን ጊዜ ስለሚደርሱ አስከፊ ክስተቶች የሚተነብይ ነው።

በተደጋጋሚ ባለ አራት መስመር ግጥሞቹ ግልጽ ያልሆኑ እና ዐውድ የጎደላቸው ተብሎ የሚገለፁ ሲሆን፣ ከእነዚያም መካከል አንዱ በአንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ እና ድረ ገጾች ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ሞት ጋር ተያይዞ ተጠቅሷል።

ፈረንሳዊው ሐኪም ትንቢቱን ከጻፈበት ከአውሮፓውያኑ 1555 ጀምሮ በርካታ ሊቃነ ጳጳሳት በመሞታቸው የተነሳ፣ "በጣም ያረጀውን ጳጳስ ሞት" ተብሎ የተተረጎመው ትንቢት ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ጋር በቀጥታ እንደሚገናኝ ግልጽ አይደለም።

ኮከብ ቆጠራ ኮከቦች በሰው ልጅ ክስተቶች ላይ ተጽእኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ የሚገልጽ ሳይንሳዊ ድጋፍ የሌለው ልምምድ ነው።

ኮከብ ቆጠራ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ላይ እጅጉን ታዋቂ ለመሆን በቅቷል።

የኮከብ ቆጣሪዎች እዚህም እዚያም ሱቆችን በመክፈት ትንቢታቸውን ፈልጎ ለሚመጣ አገልግሎት መስጠት ጀምረው ነበር።

እነዚህ ኮከብ ቆጣሪዎች ስለ ሥራ፣ የፍቅር ግንኙነት፣ ጤና ያማክራሉ፤ ይተነብያሉ።

ከእነዚህ መካከል የኮከብ ቆጠራ አገልግሎትን ለሀብታሞች እና ለባለሥልጣናት የሚያደርገው ኖስትራዳመስ ይገኝበታል።

በወቅቱ የኮከብ ቆጠራ በትምህርት ቤት ገብተው የሚማሩት መስክ የነበረ ቢሆንም፣ ኖስትራዳመስ ግን በጊዜው በኮከብ ቆጠራ ላይ መደበኛ ሥልጠና አልወሰደም ነበር።

እና በዘመኑ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች አጭበርባሪ ሲሉ ያጣጥሉታል።

ይኹን እንጂ በወቅቱ ምሥጢራዊ መልዕክቶችን የያዙት አጫጭር ግጥሞቹ በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት አትርፈውለታል፤ በብዙ ቅጂም ተሸጠውለታል።

የ16ኛው ክፍለ ዘመን ጦርነት፣ የሰብል ውድመት እና ረሃብ ለገጠማቸው ለአብዛኞቹ አውሮፓውያን በጣም አሳዛኝ ጊዜ ነበር፤ ከተሞቻቸውም በወረርሽኝ ተጠቅተው ነበር።

በእንደዚህ ዓይነት የሕይወት ውጥንቅጥ መካከል፣ የኖስትራዳመስ ትንቢቶች ማስጠንቀቂያ እና የመጽናናት ስሜትን በመስጠት በወቅቱ ተወዳጅ ሆነዋል።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የማግዳለን ኮሌጅ የሳይንስ እና የሃይማኖት ታሪክ ምሁር የሆኑት ዶ/ር ሚሼል ፌፈር "በማኅበረሰቡ ላይ በጋራ የወረደው መከራ ከፍተኛ ነበር" ብለዋል።

"እንዲህ ዓይነት በጣም እርግጠኝነት በጠፋበት ወቅት ሰዎች መልስ፣ መመሪያ ይፈልጋሉ እና የበለጠ ደግሞ የተሻለ ነገር እየመጣ መሆኑን የሚያሳይ ማረጋገጫ ይፈልጋሉ።"

በዚህ ዘመን ሰዎች የሚገጥማቸውን ለማወቅ ወደ ሆሮስኮፕ እንደሚዞሩ ሁሉ፣ በዚያን ዘመንም የኖስትራዳመስ ተከታዮች የተመሰቃቀለውን ዓለም እና ለውጥ እየመጣ መሆኑን በእርሱ ትንቢቶች ውስጥ አጮልቀው ማየት ችለዋል።

በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ደጋፊዎቹ ሁለቱንም የዓለም ጦርነቶች፣ የሂሮሺማ እና የናጋሳኪ የኒውክሌር ፍንዳታዎችን፣ የሂትለርን መነሳት እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ጨምሮ ብዙ ታሪካዊ ክስተቶችን፣ ምንም እንኳን እነዚህን ክስተቶች በስም ባይጠቅሳቸውም እንደተነበየ ይናገራል።

በሮድ አይላንድ ዩኒቨርሲቲ የመካከለኛው ዘመን ታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ጆሌ ሮሎ ኮስተር የኖስትራዳመስ ትንቢቶች የተጻፉት "ከምንም ዓይነት ሁኔታ ጋር ሊጣጣም በሚችል እጅግ በጣም ግልጽ ባልሆኑ ቃላት ነው" ይላሉ።

"ትንቢቶቹ አሻሚ እና በበቂ ሁኔታ ግልጽ ባልሆኑበት ጊዜ ማንም ሰው የሚስማማውን ነገር ፈልጎ ማግኘት ይችላል።"

ይህ ቢሆንም እንኳ ስሙና ትንቢቶቹ በሕዝብ ምናብ ውስጥ ለረዥም ጊዜ መኖር ችለዋል።

ከብዙዎቹ ጊዜ ከማይሽረው ትንቢቶቹ በተጨማሪ፣ ጥቂቶች ብቻ የተወሰኑ ቀኖችን መያዛቸው የኖስትራዳመስን ትንቢቶች የሚተረጉሙ መጻሕፍት በከፍተኛ መጠን እንዲሸጡ አድርጓል።

በእንግሊዝኛ ብቻ ከ100 በላይ የተለያዩ ርዕሶች ያሏቸው መጻሕፍት በእርሱ ትንቢቶች ዙሪያ ታትመዋል።

የእሱን ትንቢቶች እንደ ዓለም አቀፍ የዜና ክስተቶች ማዛመጃ የተረጎሙ አዳዲስ ህትመቶች በ20ኛው ክፍለ ዘመን በሕዝብ አእምሮ ውስጥ ያለውን ቦታ እንዲያረጋግጥ ረድተውታል።

ከመስከረም 11 የኒው ዮርክ መንትያ ሕንጻዎች ጥቃት በኋላ፣ ተከታዮቹ ስለ ጥቃቱ ተንብይዋል በማለታቸው የኖስትራዳመስ መጽሐፍቶች በከፍተኛ ደረጃ እንዲሸጡ አድርጓል።

ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው ከጥቃቱ በኋላ ከኖስትራዳመስ የተለያዩ ምንባቦችን እና የእሱ ያልሆኑ ቃላትን በማቀናጀት 'ምን እንደሚፈጠር አስቀድሞ ተናግሯል' የሚል የኢሜል መልዕክቶችን ተቀብሏል።

ጽሑፉ "እሳት ወደ ታላቋ አዲስ ከተማ ቀረበ፤ በዮርክ ከተማ ውስጥ ታላቅ ውድቀት ይሆናል" የሚሉትን ቃላት አካትተው ይዘዋል።

ሌሎች የኮከብ ቆጣሪው ደጋፊዎቹ አፖሎ ጨረቃ ላይ እንደሚያርፍ ተንብይዋል፤ የቻሌንጀር የጠፈር መንኮራኩር አደጋ እንዲሁም የብሪታኒያ ንግሥት ኤልዛቤት ሞትን ጨምሮ ተንብይዋል ሲሉ ይናገራሉ።

በዚህ ዘመን አብዛኛው ሰው ወደ ኖስትራዳመስ ዋና ጽሑፎች በመሄድ ማመሳከር ትቷል።

ነገር ግን በኦንላይን ላይ በሚለቀቁ መጣጥፎች ወይም ለማኅበራዊ ሚዲያ ቀልዶች በሚሠሩ ልጥፎች ውስጥ ስለ እርሱ እና ስለትንቢቶቹ አሁንም ይገኛል።

በቅርብ ጊዜ ደግሞ ስለ ጳጳሱ የተነገሩ ሌሎች ትንቢቶች በኦንላይን እንደገና መታየት ጀምረዋል።

ጳጳስ ፍራንቼስኮ የመጨረሻው ሊቀ ጳጳስ ሊሆኑ እንደሚችሉ ለመጠቆም በቅዱስ ማላቺ የተነገረው ነው የተባለ ትንቢት በአንዳንዶች ዳግም ሲጋራ ታይቷል።

ምሁራኑ የዚህ ጽሑፍ ትክክለኛነት ላይ ያላቸውን ጥያቄ አቅርበው በፖለቲካዊ ምክንያቶች የተፈጠረ ነው ይላሉ።

በማያሚ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ጆሴፍ ኡስሲንስኪ እንደሚሉት "ትንቢት አስደሳች እና ማራኪ ነው። ስለዚህም አንዳንድ ሰዎች ከመደበኛው መገናኛ ብዙኃን ውጪ ወደሚገኙት ወደ እነዚህ ዓይነት ሀሳቦች ያዘነብላሉ። የሰው ልጅ የማንነቱ አካል ነው።"

እርግጠኛነት በጠፋበት ዘመን፣ የኖስትራዳመስ እና ሌሎች ኮከብ ቆጣሪዎች ትንቢቶች ተወዳጅ ሆነው መቆየታቸው ምንም አያስደንቅም ይላሉ ባለሙያዎች።

"በአስጨናቂ ጊዜ ኮከብ ቆጠራ እና ትንቢት [ወደፊት የሚፈጸሙትን ክስተቶች አስቀድሞ ለማየት ወይም ለመተንበይ መፈለግ ወይም የተደበቀ ዕውቀትን ለማግኘት መፈለግ] ትልቅ ትኩረት የሚስብ ነው" ብለዋል ዶክተር ፌፈር።

"የሰው ልጆች እርግጠኛነት በሌለበት ውስጥ ሁሌም ይናወጣሉ። እናም ኮከብ ቆጣሪዎች እና ትንቢት ተናጋሪዎች ከባድ ውሳኔዎችን እንዲወስኑ በመርዳት በታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ይሰጣቸዋል። ያ ብቻ ሳይሆን በሕይወት ውስጥ ትልቅ ዕቅድ እንዳለ በመግለጽ ሰዎችን ማጽናናት ይችላሉ" ብለዋል።