ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሲዳንስ፡ ሆሊውድን ያስደነገጠው በቀላሉ ፊልም 'መሥራት' የሚያስችለው የቻይና ኤአይ
የቻይናው የቴክኖሎጂ ኩባንያ ባይትዳንስ አዲስ ያስተዋወቀው መተግበሪያ ሆሊውድን አስደንግጧል።
ቲክቶክን የሠራው ባይትዳንስ ኩባንያ ለገበያ ያቀረበው አዲስ የሰው ሠራሽ አስተውሎት መተግበሪያ ሲዳንስ (Seedance 2.0) ይባላል።
ይህ መተግበሪያ ጥቂት ጽሑፍ ተሰጥቶት ወደ ቪድዮ የሚለውጥ ሲሆን፤ ማጀቢያ ሙዚቃ እና ንግግርም ይፈጥራል። ቪድዮ የሚሠራበት ጥራት ከሆሊውድ ፊልሞች የሚተናነስ አይደለም። በተዋንያን መካከል የሚደረግ ንግግርን በሙዚቃም ያጅባል።
በሲዳንስ ተሠርተዋል የተባሉ እና እንደ ማሳያ የቀረቡ ቪድዮዎች እንደ ስፓይደርማን ያሉ ታዋቂ የሆሊውድ ገጸ ባህሪያትን ያሳያሉ። በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከፍተኛ ዕውቅናም አግኝተዋል።
እንደ ዲዝኒ እና ፓራማውንት ያሉት ግዙፍ የአሜሪካ ፊልም ሠሪ ተቋማት ባይትዳንስ የቅጂ መብት ጥሰት ፈጽሟል ብለው ከስሰዋል።
ሲዳንስ እንዴት ይሠራል?
ሲዳንስ የሰው ሠራሽ አስተውሎት መተግበሪያ በአውሮፓውያኑ ሰኔ 2025 ሲተዋወቅ እምብዛም ታዋቂ አልነበረም። ከስምንት ወራት በኋላ መተግበሪያው ማሻሻያ ተደርጎበት ይፋ ተደረገ።
ቪድዮስቴት በተባለው የፈጠራ ተቋም ውስጥ የሚሠራው ጃን-ዊልያም ብሉም ሲዳንስን ሲገልጸው "በኤአይ የተሠራ ቢሆንም ቆንጆ ቪድዮ ነው ብዬ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰብኩበት ምክንያት ነው" ይላል።
በሲዳንስ የተሠሩ ቪድዮዎች በፕሮዳክሽን ተቋማት እንደሚሠሩት ያህል ጥራት እንዳላቸው ይናገራል።
በምዕራቡ ዓለም የተሠሩ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቪድዮዎች አስደናቂ ምሥሎች ቢኖሯቸውም፤ ሲዳንስ ሁለገብ መሆኑን ያስረዳል።
ጽሑፍን ወደ ቪድዮ የሚለውጡ እንደ ሚድጆርኒ እና ሶራ ያሉ መተግበሪያዎች አሉ። ሲዳንስ ከአጭር ጽሑፍም ቢሆን ከፍተኛ ጥራት ያለው ቪድዮ ይፈጥራል።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥነ ምግባር ባለሙያ ማርግሬት ሚሸል እንደምትለው፤ ሲዳንስ አስደናቂ የሆነው ጽሑፍ፣ ምሥል እና ድምጽ አንድ ላይ ስለሚያቀናጅ ነው።
ተዋናዩ ዊል ስሚዝ ፓስታ ሲመገብ የሚያሳይ ቪድዮ ተሠርቶ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ሲዘዋወር ነበር። ከእውተኛ ቀረጻ ጋር በእጅጉ የሚቀራረብ መሆኑ በርካቶችን አስገርሟል፤ አስደንግጧልም።
ሌላኛው በማኅበራዊ ሚዲያ በስፋት የታየው ዊል ስሚዝ ከፓስታ ከተሠራ አውሬ ጋር ሲታገል የሚያሳየው ቪድዮ ከፍተኛ ገንዘብ ወጥቶበት ከሚሠራ የሆሊውድ ፊልም ጋር የሚስተካከል ጥራት አለው።
የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች እና ፊልም ሠሪዎች እንደሚናገሩት ከሆነ ሲዳንስ ቪድዮ የሚሠራበትን መንገድ ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሯል።
ሲንጋፖር የሚገኘው የአኒሜሽን ፊልም ተቋም 'ታይኒ አይላንድ ፕሮዳክሽንስ' ባለሙያ የሆነው ዴቪድ ኮውክ እንደሚለው፤ ከዚህ ቀደም ለመሥራት ቀላል ያልነበሩ የድብድብ ትዕይንት የሚበዛባቸው ፊልሞች አሁን ላይ ቀላል እየሆኑ መጥተዋል።
"በእነዚህ ፊልሞች የተካነ ሲኒማቶግራፈር ወይም ዳይሬክተር አብሮን የሚሠራ ያህል ነው የሚሰማን" ሲል መተግበሪያዎችን ይገልጻል።
ሲዳንስ ከቅጂ መብት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ተነስተውበታል።
በሌላ በኩል የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የሚፈጥሯቸው መተግበሪያዎች ለሰዎች ቅድሚያ የሚሰጡ አይደሉም ተብለው ይተቻሉ።
የሆሊውድ ባለሙያዎች እንደ ስፓይደር ማን ያሉ ታዋቂ ገጸ ባህሪያት በመተግበሪያው ጥቅም ላይ መዋላቸውን አልተቀበሉትም።
ዲዝኒ እና ፓራማውንት ባወጡት ደብዳቤ ሲዳንስ ይዘቶቻቸውን እንዳይጠቀም ከልክለዋል። ጃፓንም ታዋቂ የአኒሜሽን ገጸ ባህሪያት በሲዳንስ በመታየታቸው ምክንያት ባይትዳንስ ላይ የቅጂ መብት ጥሰት ምርመራ ከፍታለች።
የሲዳንስ ፈጣሪ የሆነው ባይትዳንስ "የደኅንነት ጥበቃ እርምጃዎችን እንደሚያጠናክር" አስታውቋል።
በአውሮፓውያኑ 2023 ኒው ዮርክ ታይምስ፤ ኦፕንኤአይ እና ማይክሮሶፍትን በቅጂ መብት ጥሰት መክሰሱ ይታወሳል።
ተቋማቱ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሞዴሎቻቸውን ለማሠልጠን የኒው ዮርክ ታይምስን ይዘት ተጠቅመዋል ተብለው ነው የተከሰሱት።
ሬዲት ደግሞ ፐርፕሌክሲቲ የደንበኞቹን ጽሑፍ እንዳወረደ በመገለጽ ከስሶታል። ዲዝኒም ተመሳሳይ ክስ ጉግል ላይ ከፍቷል።
ባለሙያዎች እንደሚሉት በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚሠሩ ይዘቶች የቴክኖሎጂ ውጤት መሆናቸውን በግልጽ ለሕዝብ ማሳወቅ አስፈላጊ ነው። ኤአይ ለሚወስዳቸው ገጸ ባህሪያት በስምምነት ከፍያ መፈጸምንም ይመክራሉ።
በዚህ መንገድ ይዘቶች ያለ አግባብ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ መከላከል ይቻላል።
ኦፕንኤአይ የሠራው ሶራ እና ዲዝኒ የ730 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ስለተፈራረሙ ከስታር ዋርስ፣ ፒክሳር እና ማርቭል ፊልሞች ይዘቶችን መውሰድ ተፈቅዶላቸዋል።
ቻይና የቴክኖሎጂ ፉክክሩን እየመራች ነው?
በሜልበርን ዩኒቨርስቲ የኮምፒውቲንግ ተመራማሪ ሻነን ኮኽኒ እንደምትለው፤ ሲዳንስ በምዕራቡ ዓለም የተሠሩ ፊልሞችን ይዘት ሲወድስ ከአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ሊነሱበት እንደሚችሉ ያውቃል።
"ሕግጋትን ለመጣስ ብዙ ማምለጫ መንገዶች አሉ" ትላለች።
ሲንጋፖር የሚገኘው የአኒሜሽን ፊልም ተቋም 'ታይኒ አይላንድ ፕሮዳክሽንስ' ባለሙያ የሆነው ዴቪድ ኮውክ በበኩሉ፤ በጥቂት በጀት የሚሠሩ ትናንሽ ተቋማት ሲዳንስን ሊጠቀሙበት ይችላሉ።
እንደ ምሳሌ የሚጠቅሰው እያደገ የመጣውን የእስያ አጭር ፊልም ኢንዱስትሪ ነው።
እያንዳንዳቸው ከሁለት ደቂቃ በታች የሆኑ 80 ምዕራፍ ያላቸው ፊልሞችን ለመሥራት 140 ሺህ ፓውንድ ያወጣሉ።
ትዕይንት የማይበዛባቸው እንደ የቤተሰብ ድራማ ያሉ ይዘቶችን የሚመርጡትም ብዙ ወጪ ስለማያስወጧቸው ነው።
ይህ ሲዳንስ የተሰኘው የሰው ሠራሽ አስተውሎት መተበግሪያ ቻይናን በቴክኖሎጂው ዘርፍ መነጋገሪያ አድርጓታል።
ተመራማሪዋ ሻነን "የቻይና ሞዴሎች አሁን የሚፈለገውን የቴክኖሎጂ ገጽታ እየተላበሱ ነው" ትላለች።
ባይትዳንስ በድንገት ሲዳንስን ይፋ ካደረገ፤ ሌሎች በጊዜ ሒደት ይፋ የሚያደርጋቸው ቴክኖሎጂዎች ምን ሊመስሉ እንደሚችሉ ለመገመት ያዳግታል።
ባለፈው ዓመት የቻይናው ዲፕሲክ ሲለቀቅ ከቻትጂፒቲ የተሻለ መሆኑ ምዕራባውያንን ማስደንገጡ አይዘነጋም።
ቻይና የተራቀቁ ቺፖች እያመረተች ሲሆን፣ በሮቦቲክስ ዘርፍም አስገራሚ ግኝቶች አሏት። ቻይና በቴክኖሎጂው ዘርፍ ከፍተኛ ገንዘብ በማፍሰስ አሜሪካ እና የተቀሩትን ምዕራባውያን አገራት ትገዳደራለች።
ሲዳንስ በዓለም መነጋገሪያ ቢሆንም ሌሎችም በቻይና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እየተሠሩ ያሉ መተግበሪያዎች አሉ።
በተለይ የቻይና አዲስ ዓመት አካባቢ "የኤአይ ክብረ በዓል" በሚመስል ሁኔታ አዳዲስ መተግበሪያዎች ይፋ እንደሚደረጉ የቻይና ጉዳዮች ተንታኝ ቢል ቢሾፕ ይናገራል።
የአውሮፓውያኑ 2026 በርካታ የቻይና የሰው ሠራሽ አስተውሎት መተግበሪያዎች ገበያውን የሚቀላቀሉበት እንደሆነም ይተነብያል።