ናሳ ከ50 ዓመት በላይ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰዎችን ወደ ጨረቃ ዙሪያ ሊልክ ነው

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካው የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ፤ ከ50 ዓመታት በላይ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በየካቲት መጨረሻ ጠፈርተኞች ወደ ጨረቃ ዙሪያ ለመላክ ማቀዱን ገለጸ። ናሳ ይፋ ያደረገው ይህ ዕቅድ የሰው ልጅ ወደ ጠፈር ካደረጋቸው ጉዞዎች ሁሉ ረዥሙ እንደሚሆን ይጠበቃል።

'አርቴሚስ ሁለተኛ' (Artemis II) የሚል ስያሜ በተሰጠው በዚህ ተልዕኮ አማካኝነት አራት ጠፈርተኞች ሩቅ ወደሆነው የጨረቃ ክፍል ያመራሉ።

ተመልሰው ወደ ምድር እስከሚመጡ ድረስም ጉዞው 10 ቀናትን እንደሚወስድ ተነግሯል። ጉዞው ወደፊት ጨረቃ ላይ ለማረፍ ለተያዘው ዕቅድ መንገድ የሚጠርግ እንደሆነ ተገልጿል።

በናሳ ዕቅድ መሠረት ሮኬቱ የካቲት 28/2018 ዓ.ም. ወደ ጠፈር ይወነጨፋል። ከዚህ አስቀድሞ ደግሞ ሮኬቱ በነዳጅ የሚሞላበት እና የማስወንጨፊያ የመጨረሻ ሂደቶች የሚታዩበት የቅድመ ውንጨፋ ሙከራ ይደረጋል።

የናሳ ተመራማሪ የሆኑት ሎሪ ግሌዝ፤ "በየምሽቱ ወደ ጨረቃ ቀና ብዬ እያለሁ፤ ስመለከታት እጅግ እደሰታለሁ። ምክንያቱም እየጠራችን እንደሆነ ይሰማኛል፤ እኛም ዝግጁ ነን" ሲሉ አርብ ዕለት በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

የመጀመሪያው ሙከራ በጥር ወር መጨረሻ የተካሄደ ሲሆን በማስወንጨፊያው ሥፍራ ላይ የሃይድሮጂን ነዳጅ መፍሰስ በማጋጠሙ ከታቀደለት ጊዜ አስቀድሞ ተቋርጧል።

ተመራማሪዋ ግሌዝ፤ በአሁኑ ሰዓት ከማሸጊያዎች እና ከማጣሪያዎች ጋር የተያያዙት ችግሮች መፈታታቸውን ገልጸዋል።

ጉዞውን ከሚያደርጉት ጠፈርተኞች ውስጥ ሦስቱ ሪድ ዊስማን፣ ቪክቶር ግሎቨር እና ክሪስቲና ኮክ የተባሉት አሜሪካውያን ናቸው። ሌላኛው የአርቴሚስ II ቡድን አባል ካናዳዊው ጄረሚ ሀንሰን ነው።

የቡድኑ አባላት በስኬት በተጠናቀቀው ልምምድ መደሰታቸውን የገለጹት ተመራማሪዋ ግሌዝ፤ ከአርብ ጀምሮ ወደ ለይቶ ማቆያ እንደሚገቡ አስታውቀዋል።

ጠፈርተኞቹን የሚይዘው ግዙፉ የናሳ የጨረቃ ሮኬት የሚወነጨፈው 98 ሜትር ቁመት ባለው የጠፈር ማስወንጨፊያ ሥርዓት አማካኝነት ነው።

ሮኬቱ ከዚህ ቀደም በአርቴሚስ አንድ ተልዕኮ ወቅት በአውሮፓውያኑ ኅዳር 2022 አንድ ጊዜ ብቻ ተወንጭፎ ነበር። ሮኬቱ በመጀመሪያ ጉዞው ሰው አልጫነም ነበር።

ጠፈርተኞቹ ጉዟቸውን የሚያደርጉት 'ኦሪዮን ካፕሱል' ተብሎ በሚጠራው የሮኬቱ አናት ላይ ታስረው ነው።

የመንኮራኩሩ ውስጠኛ ክፍል መጠኑ አነስተኛ አውቶቡስ ያህላል። በአሥሩ ቀናት ውስጥ አራቱ ጠፈርተኞች የሚኖሩት፣ የሚመገቡት፣ የሚሰሩት እና የሚተኙት በዚህ ክፍል ውስጥ ነው።

በጉዞው የመጀመሪያ ቀን፤ ሮኬቱ በምድር ምህዋር ዙሪያ ያልፋል። በዚህ ጊዜ ሁሉም የሮኬቱ ሥርዓቶች በጥሩ ሁኔታ እንደሚሠሩ ከተረጋገጠ ቀጥሎ ወደ ጨረቃ ያመራል።

የመሄጃው ጉዞ አራት ቀናት ገደማ የሚወስድ ሲሆን በዚህ ወቅት ጠፈርተኞቹ ሰዎች ምድር ላይ ሆነው በጭራሽ ሊያዩት በማይችሉት ሩቁ የጨረቃ ጎን በኩል ይዞራሉ።

ከጨረቃ ወለል በላይ ከ6,500 እስከ 9,500 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ይሆናሉ። በዚህ ርቀት ላይ ሆነው ጨረቃን ማጥናት እና ፎቶግራፍ ማንሳት እንዲችሉ በርካታ ሰዓታት ተመድቦላቸዋል።

ከዚህ በኋላ ወደ ምድር የሚያደርጉትን የአራት ቀናት ጉዞ የሚጀምሩ ሲሆን በመጨረሻም ፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ በማረፍ ጉዟቸውን ያጠናቅቃሉ።

ይህ ጉዞ የሚሳካ ከሆነ በቀጣይ ጨረቃ ላይ ለማረፍ ለሚደረገው የ'አርቴሚስ III' ጉዞ መንገድ ይከፍታል።

የሰው ልጅ ለመጨረሻ ጊዜ ጨረቃን የጎበኘው በአውሮፓውያኑ 1972 'አፖሎ 17' ተልዕኮ በተከናወነበት ወቅት ነው።

ናሳ፤ እስከ አውሮፓውያኑ 2028 ባለው ጊዜ ውስጥ ሰዎችን ጨረቃ ላይ ለማሳረፍ ዕቅድ የያዘ ቢሆንም የተቀመጠው ቀነ ገደብ እጅግ አጭር ነው የሚል ትችት ተነስቶበታል።