ጠፈር ሳይንስ፡ ዓለም አቀፉ የህዋ ምርምር ጣቢያ እአአ በ2031 ምድር ላይ ይወድቃል ተባለ

ዓለም አቀፉ የህዋ ምርምር ጣቢያ (አይኤስኤስ) እአአ 2031 መጀመሪያ ላይ ወደ ምድር ወድቆ ፓስፊክ ውቅያኖስ ውስጥ እንደሚገባ የአሜሪካ የህዋ ምርምር ተቋም ናሳ አስታወቀ።

ይሁን እንጂ የህዋ ጣቢያው እስከ 2030 ድረስ ሥራውን ይቀጥላል።

በዚህ ሳምንት የአሜሪካ የህዋ ምርምር ተቋሙ ባወጣው ሪፖርት ዓለም አቀፉ የህዋ ጣቢያ ፖይንት ኔሞ በሚባል በሚታወቀው የውቅያኖሱ ክፍል ላይ እንደሚወድቅ ገልጿል።

ይህ 'የህዋ መንኮራኩር መቃብር' ተብሎ የሚጠራው ፖይንት ኔሞ፤ ርቆ የሚገኝ የምድራችን ስፍራ ነው።

እአአ በ2001 የሩሲያን የህዋ ጣቢያ 'ሚር'ን ጨምሮ በርካታ ያረጁ ሳተላይቶች እና ሌሎች የህዋ ፍርስራሾች እዚያ ቦታ ላይ ወድቀዋል።

ናሳ የወደፊቱ ለምድር ቅርብ የሆኑ የህዋ እንቅስቃሴዎች የሚመሩት በንግዱ ዘርፍ ይሆናል ብሏል።

አምስት የህዋ ምርምር ኤጀንሲዎችን ያሳተፈው ዓለም አቀፉ የህዋ ጣቢያ ከአውሮፓውያኑ 1998 ጀምሮ በምህዋር ላይ የቆየ ሲሆን ከ2000 ጀምሮም በተከታታይ ሲሰራ ቆይቷል። በውስጡ ባለው ማይክሮግራቪቲ ቤተ ሙከራው ከ3 ሺህ በላይ ጥናትና ምርምሮችም ተካሂደዋል።

ሆኖም ቤተ ሙከራው እንዲሰራ የተፈቀደለት እስከ 2024 ድረስ ሲሆን ጊዜውን ለማራዘም ሁሉም አጋሮች ስምምነት ላይ መድረስ ይጠበቅባቸዋል።

አይኤስኤስ ከሥራ ውጭ ሊደረግ የታቀደው ለምድር ቅርብ በሆነ ህዋ -በዝቅተኛ የመሬት ምህዋር ውስጥ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ወደ ንግዱ ዘርፍ ለማሸጋገር እንደሆነ ናሳ አስታውቋል።

በናሳ ዋና መሥሪያ ቤት የንግድ ህዋ ዳሬክተር የሆኑት ፊል ማክሊስተር " የግሉ ዘርፍ በናሳ እገዛ ዝቅተኛ የምድር ምህዋር መዳረሻዎችን ለማልማት እና ለመሥራት አቅሙ አለው" ብለዋል።

እአአ በ2020 ናሳ ከአይኤስኤስ ጋር የተገናኘና መታጠቢያ ቤት፣ መጸዳጃ ቤትና ሌሎች መሠረታዊ ነገሮች ያሉት ቢያንስ አንድ መኖሪያ ጣቢያ እንዲገነባ ለቴክሳሱ ኩባንያ አክሲየም ስፔስ ውል ሰጥቶት ነበር።

ከዚህም በተጨማሪ ለሦስት ኩባንያዎች የህዋ ጣቢያ እንዲገነቡ እና በምህዋር ላይ ሌሎች የንግድ መዳረሻዎችን እንዲሰሩ ናሳ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።

ናሳ እነዚህ አዳዲስ ፕሮጀክቶች አይኤስኤስ ሥራ ከማቆሙ በፊት በከፊል እንደሚሠሩ ተስፋ አድርጓል።

ናሳ "ጠንካራ፣ በአሜሪካ የንግድ ኢኮኖሚ የሚመራ በዝቅተኛ የመሬት ምህዋር ላይ የሚሠራ ጣቢያ መፍጠር እፈልጋለሁ" ብሏል።

የንግዱ ዘርፍ ለአሜሪካ የህዋ ፕሮግራም ወሳኝ ነው። የግል ኩባንያዎች ሠራተኞችን እና እቃዎችን የማድረስ ኃላፊነት አለባቸው። የሩሲያ ሶዩዝ እና የህዋ መንኮራኩርም ለዚህ አገልግሎት ይውላሉ።

እንደ ናሳ ከሆነ ይህንን ዘርፍ ወደ ግል በማሸጋገር በዝቅተኛ የመሬት ምህዋር ላይ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በጥልቅ ህዋ ላይ እንቅስቃሴ ለማድረግ ከሚወጣው ገንዘብ 1.3 ቢሊየን ዶላርን መቆጠብ ይቻላል።

ናሳ ለአይኤስኤስ ጥገና እና ሥራዎች ሳይሆን ለሚያስፈልገው አገልግሎት ብቻ ስለሚከፍል የሚያፈሰውን ገንዘብ መቆጠብ እንደሚቻል የገለጸ ሲሆን፤ የግሉ ዘርፍ የህዋ ጣቢያዎች አዳዲስ ስለሚሆኑም የሚያስፈልጋቸው አነስተኛ መለዋዋጫዎች እንደሆኑ ጠቁሟል።

ናሳ አክሎም የአይኤስኤስን የዓመት በጀት መተንተኑን ገልጾ፤ የቁጠባ ግምቱን ማጣራቱን እንደሚቀጥል ገልጿል።

በዚህ ሳምንት ናሳ ያሳተመው ሪፖርት የወጣው የጆ ባይደን አስተዳደር የህዋ ጣቢያ እንቅስቃሴዎችን እስከ 2030 ለማራዘም ቁርጠኛ መሆናቸውን ከተናገሩ በኋላ ነው።

ይሁን እንጂ የማራዘም ሂደቱ በአሜሪካ ብቻ የሚወሰን አይደለም። ሩሲያን ጨምሮ ሌሎች የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ አጋር ድርጅቶች ስምምነትን ይጠይቃል። የህዋ ጣቢያው እስከ 2024 እንዲሰራ የፈቀደውም የአሜሪካ ምክር ቤት ብቻ ነው።

የሩሲያው የህዋ ፕሮግራም ኃላፊ ዲሚትሪ ሮጎዚን ለሩሲያ የዜና ወኪል ኢንተርፋክስ በሰጡት ቃለ ምልልስ ከ2024 በኋላም ከናሳ ጋር ለመስራት ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሩሲያ የህዋ ኮርፖሬሽን ኃላፊ በበኩላቸው አሜሪካ በሩሲያ ላይ የጣለችው ማዕቀብ የአገሪቷን የህዋ ኢንደስትሪ ጎድቷል ያሉ ሲሆን ማዕቀቡ ካልተነሳ ሩሲያ በአይኤስኤስ ፕሮግራም ላይ ያላት ተሳትፎ ሊያከትም ይችላል ብለዋል።

አሜሪካ እና የምዕራብ አጋሮቿ ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ተጨማሪ ማዕቀብ እንደሚጥሉ እየዛቱ ነው፤ ነገር ግን ማዕቀቡ ምን ሊሆን እንደሚችል እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

ሩሲያ ቀደም ብሎ አይኤስኤስ ከ2030 በኋላ መስራት እንደሌለበት የገለጸች ሲሆን ጊዜ ያለፈባቸው መሣሪያዎች ወደ የማይጠገኑ ውድቀቶች ሊያመሩ ይችላሉ ስትል አስጠንቅቃለች።