ናሳ ማርስ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሄሊኮፕተር በተሳካ ሁኔታ አበረረ

የአሜሪካ የህዋ ምርምር ተቋም ናሳ አንዲት አነስ ያለች ሄሊኮፕተርን በማርስ ፕላኔት ላይ በተሳካ ሁኔታ ማብረር ቻለ።

ናሳ 'ኢንጂኒዩቲ' በመባል የምትጠራውን ሰው አልባ ሄሊኮፕተር በፕላኔቷ ላይ ማብረር የቻለው ከአንድ ደቂቃ በታች ለሆነ ጊዜ ቢሆንም፤ በሌላ የዓለም ክፍል ላይ ከሚገኝ ስፍራ ቁጥጥር የሚደረግለትን የመጀመሪያውን በረራ ማድረግ በመቻሉ ታላቅ ደስታ ተፈጥሯል።

ሄሊኮፕተሯ በማርስ ላይ በረራ ማድረጓን በተመለከተ በፕላኔቷ ላይ ከሚገኝ ሳተላይት ወደ መሬት ከተላለፈ መረጃ ለማረጋገጥ ተችሏል።

የህዋ ምርምር ተቋሙ ከዚህ ሙከራው በኋላ ተመሳሳይ ያልተሞከሩ በረራዎችን ወደፊት እንደሚያከናውን ቃል ገብቷል።

በረራውን ያደረገችው ሄሊኮፕተር ወደ ማርስ የተወሰደችው 'ፐርሲቨራንስ' በተባለችው የናሳ መንኮራኩር ሲሆን፤ መንኮራኩሯ ባለፈው የካቲት ወር በቀይዋ ፕላኔት ላይ ማረፏ ይታወሳል።

"አሁን የሰው ልጅ በሌላ ፕላኔት ላይ ሄሊኮፕተር ማብረር ችሏል ብለን መናገር እንችላለን" ሲሉ ሚሚ አውንግ የተባላሉት የበረራው ዋና ሥራ አስኪያጅ ከፓሳዲና ካሊፎርኒያ ተናግረዋል።

"ለረጅም ጊዜ በማርስ ላይ ስለምናደርገው የመጀመሪያ በረራ ስናወራ ነበር፤ አሁን እነሆ እውን ሆነ።"

በማርስ ላይ በተደረገው በረራ ላይ ቁጥጥር ወደሚደረግበት ምድር ላይ ወደሚገኘው ማዕከል የመጀመሪያው ፎቶግራፍ በደረሰበት ጊዜ ከፍተኛ ደስታ ነበር። የበረራው ሥራ አስኪያጅም "ትክክለኛ ነው!" ስትል ይሰማ ነበር።

በማርስ ላይ የበረረችው ሄሊኮፕተር ለአርባ ሰከንዶች ያህል በተወሰኑ ሜትሮች ከፍታ ተነስታ ለአጭር ጊዜ አንዣባ ማረፏ ተነግሯል።

ቀይዋ ፕላኔት በምትባለው ማርስ ላይ በአየር ላይ መብረር አስቸጋሪ መሆኑን ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ይህም በፕላኔቷ ላይ ያለው ከባቢ አየር በጣም የሳሳ በመሆኑ እንደሆነ ይነገራል።

በመሬት ላይ ካለው የከባቢ አየር ይዘት ጋር ሲነጻጸር አንድ በመቶ በመሆኑ ይህም በራሪ ቁሶች ተነስተው ለመንሳፈፍ እጅግ አዳጋች ሁኔታን ይፈጥርባቸዋል።

አሁን በረራውን ያካሄደችው ሄሊኮፕተርም ይህንን የፕላኔቷን ተፈጥሯዊ ባህርይ እንድትቋቋም በሚያስችል ሁኔታ የተሰራችና እሽክርክሪቷም በከፍተኛ ፍጥነት እንዲሰሩ ተደርጎ የታነጸ ነው።

ሄሊኮፕተሯ ያደረገችው በረራ ቁጥጥር የተደረገበት በ300 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ርቀት ምድር ላይ ካለ ማዕከል ነበር።

'ኢንጂዩኒቲ' ሄሊኮፕተር በአካሏ ላይ ሁለት ካሜራዎች የተገጠሙላት ሲሆን አንደኛው ጥቁርና ነጭ ምስልን የሚያሳየው ካሜራ ወደ ታች በማርስ አካል ላይ የተነጣጠረና የጉዞ መስመሯን ለመመልከት የሚያግዝ ነው።

ሌላኛው ደግሞ ከፍተኛ ጥራት ያለው ምስል የሚያነሳና በፕላኔቷ አድማስ ላይ ያለውን ክፍል የሚቃኝ ነው።

በጥቁርና በነጭ ከተነሱ ምስሎች ለናሙናነት ወደምድር ከተላኩት መካከል ሄሊኮፕተሯ ለማረፍ ስትቃረብ ጥላዋን የሚያሳየው ይገኝበታል።

ማርስ ላይ ያለው ሳተላይት በረራውን በተመለከተ ተጨማሪ ምስሎች በሚቀጥለው ቀን እንደሚልክም ተነግሯል። በተጨማሪም የቪዲዮ ምስሎች በሂደት ይታያሉ ተብሏል።