እስራኤል በሊባኖስ ላይ በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ 10 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

እስራኤል በሊባኖስ ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 10 ሰዎች መገደላቸውን የሊባኖስ መገናኛ ብዙኃን አስታወቁ። ከተገደሉት መካከል ከፍተኛ የሔዝቦላህ አመራር እንደሚገኙበትም ተገልጿል።

የእስራኤል መከላከያ እንዳለው ዒላማ ያደረገው በባካ ቫሊ የሚገኙ የሔዝቦላህ መቀመጫዎችን ነው።

ሔዝቦላህ በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል "የተደረሰውን መግባባት እያፈረሰ ነው" ሲልም ከስሷል።

በአውሮፓውያኑ 2024 በእስራኤል እና ሔዝቦላህ መካከል የተቀሰቀሰውን ጦርነት የሚያስቆም የተኩስ አቁም ከተፈረመ ወዲህ የደረሰ የከፋ ጥቃት ነው።

እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ የሚገኝ የፍልስጤማውያን ስደተኞች መጠለያ ላይ ጥቃት ካደረሰች ከሰዓታት በኋላ በባካ አካባቢ የአየር ጥቃት ፈጽማለች።

የእስራኤል መከላከያ በኤክስ ገጹ "በዐይን አል-ሄልዌህ አካባቢ አሸባሪዎች የሚንቀሳቀሱበትን የሐማስን ወታደራዊ ዕዝ መትተናል" ብሏል።

ከወደብ ከተማዋ ሲዶን ወጣ ብሎ በሚገኘው እና በርካታ ሰዎች በሚኖሩበት የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ላይ በደረሰው ጥቃት ሁለት ሰዎች ሞተዋል።

በእስራኤል እና በሔዝቦላህ መካከል ለ13 ወራት የዘለቀውን ወታደራዊ ግጭት ያስቆመው የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ እስራኤል በሊባኖስ ላይ በየዕለቱ በሚባል ደረጃ ጥቃት ስትፈጽም ቆይታለች።

አሜሪካ እና ፈረንሳይ በአሸማጋይነት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ማድረጋቸው ይታወሳል። በተኩስ አቁም ስምምነቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ የእስራኤል እና የሔዝቦላህ ወታደሮች ከደቡብ ሊባኖስ ለቅቀው መውጣት ነበረባቸው።

በአውሮፓውያኑ 2020 ታኅሣሥ ላይ እስራኤል እና ሊባኖስ ሰብአዊ የልዑካን ቡድን ወደ ድንበር ከተማዋ ናቆውራ ቢልኩም ጥቃቱ እንደቀጠለ ነው።

እስራኤል እና ሊባኖስ የላኩት ሰብአዊ የልዑካን ቡድን በሁለቱ ወገኖች በኩል የተደረገ የመጀመሪያ ቀጥተኛ ውይይት አካል እንደሆነ ተገልጿል።

ውይይቱን ተከትሎ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ "ውይይቱ በጥሩ መንፈስ ነው የተከናወነው" ብሏል።

በተጨማሪም "በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል የላቀ የምጣኔ ሃብት ትብብር ለመዘርጋት ስምምነት ላይ ተደርሷል" ተብሏል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ "የምጣሄ ሃብት ስምምነት ቢደረግም እንኳ ሔዝቦላህ ትጥቅ መፍታት እንዳለበት የእስራኤል ልዑካን በግልጽ ተናግረዋል" ብሏል።

የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋፍ ሳላም በበኩላቸው፤ አገራቸው ከእስራኤል ጋር ጤናማ ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ከመፍጠር "ርቃ እንደምትገኝ" ገልጸዋል።

የሁለቱ አገራት ልዑካን ቀጥተኛ ንግግር ትኩረት የነበረው "ውጥረት ማርገብ" መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

በኢራን የሚደረገፈው የሺአ ሙስሊም ቡድን ሔዝቦላህ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ክንፍ አለው። በሊባኖስ የሚንቀሳቀሰው ሔዝቦላህ እንቅስቃሴውን የሚገታው "የእስራኤል ኅልውና ሲጠፋ" መሆኑን አስታውቋል።

እስራኤል፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ እና ሌሎችም አገራት ሔዝቦላህን በአሸባሪነት ፈርጀዋል።