አይረን ዶም፣ ዴቪድስ ስሊንግ፣ አሮው እና ስለሌሎቹ የእስራኤል የሚሳዔል መከላከያ ጋሻዎች የምናውቀው

እስራኤል በዓለም ላይ ውጤታማነታቸው የተፈተኑ ናቸው ተብለው የሚታመኑ የሚሳዔል ጥቃት የመከላከያ ሥርዓት ያላት አገር ናት።

ነገር ግን ከኢራን ጋር በጋባቸው ግጭት ውስጥ በሚካሄዱ የሚሳዔል ጥቃት ልውውጦች ውስጥ እነዚህን የጥቃት መከላከያዎች ጥሰው በማለፍ በሰዎች እና በሕንጻዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው።

ከዚህ ቀደም እስራኤል ሐማስ ከጋዛ፣ ሔዝቦላህ ከሊባኖስ እንዲሁም ሁቲዎች ከየመን በኩል የሚሳዔል ጥቃት ሲፈጽሙባት ቆይተዋል። በእነዚህ ወቅቶች ጥቃቶች ለመመከት ሁሉንም የሚሳዔል መከላከያ ዘዴዎችን ተጠቅማለች።

እነዚህ የእስራኤል የሚሳዔል መከላከያ ሥርዓቶች የአጭር ርቀት ሮኬቶችን ከሚመክተው አይረን ዶም እስከ ባለስቲክ ሚሳዔል ድረስ የሚከላከለውን አሮው የተሰኘ ፀረ ሚሳዔል መሣሪያዎችን ያካትታሉ።

በእስራኤል የሚሳኤል መከላከያ ሥርዓት ውስጥ ያሉት የተለያዩ ፀረ ሚሳዔል መከላከያዎች የትኞቹ ናቸው? እንዴትስ ይሠራሉ?

እስራኤል በርካታ የአየር መከላከያ ዘዴዎች አሏት። እንደየአቅማቸው በተለያየ ከፍታ እና ርቀት ላይ የሚመጡ ሚሳዔል ጥቃቶችን ለማክሸፍ የሚውሉ ናቸው።

ከእስራኤል የሚሳኤል ጋሻዎች መካከል በጣም የሚታወቀው “አይረን ዶም” ሲሆን፣ የአጭር ርቀት ሮኬቶችን ለመከላከል የሚያስችል ነው። ይህ መሳሪያ ሞርታሮችን እና ከሚሳዔል ማስወንጨፊያ የሚተኮሱ ከአራት እስከ 70 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚጓዙትን ያከሽፋል።

የ“ዳዊት ወንጭፍ” (ዴቪድስ ስሊንግ) የተሰኘው ደግሞ እስከ 300 ኪ.ሜ ርቀት ርቀት የሚጓዙትን የረዥም ርቀት ሮኬቶችን፣ ክሩዝ ሚሳዔሎችን እና የመካከለኛ ወይም የረዥም ርቀት ባለስቲክ ሚሳዔሎችን ለመከላከል ያስችላል።

“አሮው 2” እና “አሮው 3” የሚባሉት ደግሞ እስከ 2400 ኪ.ሜ ርቀት የሚጓዙ መካከለኛ እና ረዥም ርቀት ሚሳዔሎችን ይከላከላሉ።

አይረን ዶም (የብረት ጉልላት) ፀረ ሚሳዔል

አይረን ዶም በጦርነት ውስጥ ተደጋግሞ የተሞከረ የዓለማችን የአየር መከላከያ ሥርዓት መሆኑ ይነገርለታል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሐማስ እና ሌሎች የጋዛ ታጣቂ ቡድኖች እንዲሁም ደግሞ ሄዝቦላህ ከሊባኖስ ሆኖ ወደ እስራኤል በተኮሷቸው የሚሳዔሎች ብዛት ነው መሳሪያው ተደጋግሞ የመሞከር ዕድል ያገኘው።

በመላው እስራኤል የሚገኙ የአይረን ዶም ማስወንጨፊያዎች (ባትሪዎች) አሉ። እያንዳንዱ ባትሪ ሦስት ወይም አራት ማስወንጨፊያዎችን ይዘዋል። እያንዳንዳቸው 20 ሚሳኤሎች የማክሸፍ ብቃት አላቸው።

አይረን ዶም ለጥቃት የሚመጡ ሮኬቶችን በራዳር ፈልጎ ይከታተላል። የትኞቹ ሮኬቶች ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ ሊወድቁ እንደሚችሉ ያሰላል። ባዶ ቦታ ላይ የሚወድቁትን በመተው አይረን ዶሙ ሚሳዔሎቹን ወደ እነዚህ ሮኬቶች በመተኮስ ያጨናግፋቸዋል።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት (አይዲኤፍ) እንደሚለው ከሆነ አይረን ዶም ካነጣጠረባቸው ሮኬቶች 90 በመቶ ያህሉን ያመክናቸዋል። “ታሚር” የሚሰኙት እያንዳንዳንዳቸው ሚሳዔሎቹ 50 ሺህ ዶላር ገደማ ያስወጣሉ።

እአአ በ2006 በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል ከነበረው ጦርነት በኋላ የተሠራ መሣሪያ ነው። በወቅቱ ሄዝቦላህ ወደ እስራኤል 4 ሺህ የሚጠጉ ሮኬቶችን በመተኮስ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረስ ባለፈ በደርዘን የሚቆጠሩ ዜጎቿን ገድሏል።

ፀረ ሚሳዔል መሳሪያው የእስራኤል ኩባንያ በሆኑት ራፋኤል አድቫንስድ ዲፌንስ ሲስተም እና የእስራኤል ኤሮስፔስ ኢንዱስትሪስ የተነደፈ ሲሆን፣ የአሜሪካን መጠነኛ ድጋፍ በመጠቀም በ2011 ነበር የተመረተው።

አይረን ዶም ለመጀመሪያ ጊዜ በዘመቻዎች ላይ ጥቅም የዋለው በዚያው ዓመት ሲሆን፣ ከጋዛ የተተኮሱ ሮኬቶችን ማክሸፍ ችሏል።

የአይረን ዶም ሚሳኤሎች ከጥቅምት 2023 ወዲህ ብቻ ሐማስ እና ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ከጋዛ እንዲሁም ደግሞ ሄዝቦላህ ከደቡብ ሊባኖስ የተኮሷቸውን በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን አክሽፏል።

ዴቪድስ ስሊንግ (የዳዊት ወንጭፍ) ፀረ ሚሳዔል

በዕብራይስጥ “ተዓምረኛው ዘንግ” በመባል የሚጠራው የዳዊት ወንጭፍ (ዴቪድስ ስሊንግ) እስከ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ሚሳዔሎችን መከላከል ይችላል።

መስከረም 2024 ላይ ሄዝቦላህ ከሊባኖስ የተተኮሰውን የባለስቲክ ሚሳዔሎች ለመከላከል ጥቅም ላይ ውሏል። እንደ እስራኤል ጦር ገለጻ ከሆነ ኢራን የተሠራው ይህ ቃድር-1 የተሰኘ ባለስቲክ ሚሳኤል ከ700 እስከ አንድ ሺህ ኪሎ ግራም ክብደት ያለው የመካከለኛ ርቀት ባለስቲክ ሚሳኤል ነው።

ሄዝቦላህ ሚሳዔሉ ዒላማ አድርጎት የነበረው በቴል አቪቭ የሚገኘውን የሞሳድ ዋና መሥሪያ ቤትን እንደነበር ገልጿል። የእስራኤል ጦር ግን ሚሳኤሉ ወደ መኖሪያ መንደሮች እያመራ ነበር ብሏል።

የዳዊት ወንጭፍ በእስራኤሉ ራፋኤል አድቫንስድ ድፌንስ ሲስተምስ እና በአሜሪካው ሬይተን የጋራ ጥምረት የተሠራ ነው። በአውሮፓውያኑ 2017 ነው አገለግሎት ላይ መዋል የጀመረው።

“ስተነር” የተሰኙት ሚሳዔሎቹ የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረዥም ርቀት ባለስቲክ ሚሳዔሎችን በዝቅተኛ ከፍታ ላይ ለመምታት የተሠሩ ናቸው። እንደ አይረን ዶም ሁሉ የዳዊት ወንጭፍ ሚሳዔሎች የሚያነጣጥሩት መኖሪያ አካባቢዎች አደጋ ላይ የሚወድቁ ከሆነ ብቻ ነው።

እንደ አይረን ዶም ሁሉ የዳዊት ወንጭፍም አውሮፕላኖችን፣ ድሮኖችን እና ሚሳዔሎችን ይከላከላሉ።

እያንዳንዱ የዳዊት ወንጭፍ ሚሳኤል 1 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ዋጋ ወጥቶለታል።

በግንቦት 2023 በጋዛ የሚገኘውን የፍልስጤሙ እስላማዊ ጂሃድ ቡድንን ጥቃት ለመከላከል የዳዊት ወንጭፍ ጥቅም ላይ ውሏል። ቡድኑ ከአንድ ሺህ 100 በላይ ሚሳዔሎችን የተኮሰ ሲሆን፣ እስራኤል ስጋት ፈጥረዋል ካለቻቸው ውስጥ 96 በመቶውን ሮኬቶች ማምከኗን ተናግራለች።

አሮው (ቀስት) ፀረ ሚሳዔል

“አሮው 2” (ቀስት) የተነደፈው ከመሬት 50 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በመምዘግዘግ የአጭር እና የመካከለኛ ርቀት ባለስቲክ ሚሳዔሎችን ለመከላከል ነው።

ይህ የፀረ ሚሳዔል መከላከያው የተሠራው በ1991 ከመጀመሪያው የባሕረ ሰላጤው ጦርነት ማብቂያ በኋላ ነበር። በወቅቱ ኢራቅ በደርዘን የሚቆጠሩ የሶቪየት ሠራሽ ስከድ ሚሳዔሎችን ወደ እስራኤል ተኩሳለች። ይህንንም ተከትሎ አሮው 2 በአውሮፓውያኑ 2000 ላይ በእስራኤል ሠራዊት ጥቅም ላይ መዋል ጀመረ።

አሮው 2 ሚሳዔሎችን ከ500 ኪ.ሜ ርቀት ላይ መለየት ይችላል። ሚሳዔሎቹን የሚያጨናግፈው ግን ከማስወንጨፊያዎቹ 100 ኪ.ሜ ርቀት ገደማ ላይ ነው።

ሚሳዔሎቹ ከድምጽ ፍጥነት ከዘጠኝ እጥፍ በላይ ይጓዛሉ። በአንድ ጊዜም እስከ 14 ዒላማዎች ላይ ሊተኩስ ይችላል።

አሮው 2 በአውሮፓውያኑ 2017 የሶሪያን ሚሳዔልን ለመምታት ለመጀመሪያ ጊዜ በውጊያ ወቅት ጥቅም ላይ ውሏል ተብሏል።

የዚሁ ፀረ ሚሳዔል ዝርያ የሆነው አሮው 3 ደግሞ በዚያው ዓመት ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው። ይህ መሳሪያ ከከባቢ አየር ውጪ የሚጓዙ የረዥም ርቀት ባለስቲክ ሚሳዔሎችን ለመጥለፍ የተነደፈ ነው። 2400 ኪ.ሜ የመጓዝ አቅምም አለው።

በአውሮፓውያኑ 2017 አገልግሎት ላይ የዋለ ሲሆን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በውጊያ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው ደግሞ በ2023 ነው። በዚህም የመን ውስጥ ያሉት የሁቲ አማጺያን በደቡብ እስራኤል በሚገኘው በኤላት የባሕር ዳርቻ ከተማ ላይ የተኮሱትን ባለስቲክ ሚሳዔል ለማክሸፍ አገልግሏል።

አሮው 3 የተመረተው በመንግሥታዊው የእስራኤል ኤሮስፔስ ኢንደስትሪ ሲሆን፣ በአሜሪካ ቦይንግ ኩባንያ ድጋፍ ተደርጎለታል።

ሁሉም የእስራኤል የሚሳዔል መከላከያ ሥርዓቶች የኢራንን ግዙፍ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና ሚሳዔሎችን ለመመከት ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ጥቅም ላይ ውለዋል።

የሚሳዔል መከላከያዎቹን ጨምሮ የአሜሪካ፣ የዩናይትድ ኪንግደም እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬስ ተዋጊ ጄቶችም 300 የሚጠጉትን የኢራን ሚሳዔሎች መትተው ማክሸፋቸው መዘገቡ ይታወሳል።

ታድ ፀረ ሚሳዔል

ታድ የተባለው ፀረ ሚሳዔል ከሌሎቹ አዲሱ የሚሳዔል መከላከያ ሲሆን፣ የተሠራውም በእስራኤል የቅርብ ወዳጅ አሜሪካ ነው።

ይህን የሚሳዔል መከላከያን አሜሪካ ለእስራኤል የሰጠችው ባለፈው ጥቅምት ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ነው።

ይህ ታድ የተባለው ሚሳዔል እንደ ዴቪድስ ስሊንግ ፀረ ሚሳዔል ሥርዓት የጠላት ሚሳዔል ከ150 አስከ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ወደ ዒላማው በተቃረበበት በመጨረሻው ደረጃ ላይ ነው መትቶ የሚጥለው።

ይህ የሚሳዔል ማምከኛ መሳሪያ በጠላት የተተኮሱ ሚሳዔሎችን በመሬት ከባቢ አየር ውስጥ እና ከዚያም ውጪ መትቶ ማክሸፍ ይችላል።

ይህ መሳሪያ ስድስት ፀረ ሚሳዔል ማስወንጨፊያዎች ያሉት ሲሆን፣ እያንዳንዳቸው ስምንት ሚሳዔሎችን ስለሚይዙ በአንድ ጊዜ 48 ሚሳዔሎችን ይታጠቃል።

ታድ የተባለውን ፀረ ሚሳዔል ለማንቀሳቀስ አሜሪካ ወታደሮቿን እስራኤል ውስጥ አሰማርታለች።

የአሜሪካ ጦር ሠራዊት ይህንን ታድ የተባለ ፀረ ሚሳዔል ሥርዓት ከአውሮፓውያኑ 2015 ጀምሮ እየተጠቀመበት ሲሆን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ገዝተው ታጥቀውታል።