ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ የሚጥሉትን አዲስ ታሪፍ ወደ 15 በመቶ ከፍ ሊያደርጉ ነው
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአገሪቱን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ በመቃወም ከሌላ አገር የሚገቡ ምርቶች ላይ የ15 በመቶ ታሪፍ እንደሚጥሉ ተናገሩ።
ትራምፕ አርብ ዕለት የጣሏቸውን ታሪፎች ወደ አሜሪካ በሚገቡ ማንኛውም ምርቶች ላይ በ10 በመቶ ቀረጥ እንደሚተኩ ተናግረው ነበር።
ነገር ግን ቅዳሜ ዕለት፣ ይህ ፈጽሞ ጥቅም ላይ ያልዋለ የአገሪቱ የንግድ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት በከፍተኛ መጠን እንደሚጨምር በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል።
ይህ ሕግ እነዚህ አዳዲስ ታሪፎች አስተዳደሩ የኮንግረሱን ይሁንታ ከመጠየቁ በፊት ለአምስት ወራት ያህል በሥራ ላይ ማቆየት ያስችላቸዋል።
የ10 በመቶ ታሪፍ ከማክሰኞ እአአ ከየካቲት 24 2026 ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ተወስኗል።
አሁን የተጨመረው የ15 በመቶ ታክስ ከመቼ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ግልጽ አይደለም።
ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ዋይት ሐውስን ማብራሪያ ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።
አዲሱ የ15 በመቶ የግብር ተመን እአአ በ1974 በወጣው የአገሪቱ የንግድ ሕግ አንቀጽ 122 መሠረት ጊዜያዊ መፍትሔ ሲሆን ከአሜሪካ ጋር የ10 በመቶ ታሪፍ የተስማሙ እንደ ዩኬ እና አውስትራሊያ ላሉ አገሮች ጥያቄ ያስነሳል።
ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፋቸው ላይ እንዳሉት አስተዳደራቸው የቀረጥ ጭማሪ ለማድረግ ውሳኔ ላይ የደረሰው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ባወጣው "አስቀያሚ፣ በደንብ ያልተጻፈ እና እጅግ በጣም ፀረ-አሜሪካዊ ውሳኔ" ላይ ግምገማ ካደረገ በኋላ ነው።
የጠቅላይ ፍርድቤቱ ዳኞች ውሳኔው የተላለፈው 6 ለ 3 በሆነ አብላጫ ድምጽ ነው። ትራምፕ እአአ በ1977 የወጣ ሕግን ተግባራዊ ለማድረግ ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ ተጠቅመዋል ሲል ኮንኗል።
በቅርብ ጊዜ የወጣ የመንግሥት መረጃ እንደሚያሳየው አሜሪካ በአዲሱ ታሪፍ መሠረት እስካሁን ድረስ ቢያንስ 130 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ሰብስባለች።
ትራምፕ ውሳኔውን ተከትሎ ወዲያውኑ "በአንዳንድ የፍርድ ቤቱ አባላት እንደሚያፍሩ" እና የንግድ ፖሊሲያቸውን ውድቅ ያደረጉትን ዳኞች "ሞኞች" ሲሉ ጠርተዋቸዋል።
የታሪፍ ቅነሳ ውሳኔን ውድቅ ለማድረግ የወሰኑት ሦስት ሊበራል ዳኞች፣ በጆርጅ ደብሊው ቡሽ የተመረጡት ወግ አጥባቂ ዋና ዳኛ ጆን ሮበርትስ፣ እና በትራምፕ የተመረጡት ሁለት ዳኞች፡ ኤሚ ኮኒ ባሬት እና ኒል ጎርሱች ናቸው።
ሦስት ወግ አጥባቂ ዳኞች፣ ክላረንስ ቶማስ፣ ብሬት ካቫናው እና ሳሙኤል አሊቶ ደግሞ ተቃውመዋል።