አሜሪካ ኢራን ላይ ጥቃት ብትፈፅም ሊከሰቱ የሚችሉ ሰባት ሁኔታዎች

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

አሜሪካ ግዙፉ የጦር መርከቧን ጨምሮ ወሳኝ የባሕር ኃይል ተዋጊ መርከቦቿን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ካስጠጋች ቀናት ተቆጥረዋል። በዚህም ከዛሬ ነገ በኢራን ላይ ጥቃት ልትፈጽም ትችላለች የሚል ስጋት ተፈጥሯል።

በእርግጥ አሜሪካ ፕሬዝዳንቷ ሲዝቱ እንደቆዩት ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ ዒላማ የምታደርጋቸው ቦታዎች በአብዛኛው የሚገመቱ ቢሆንም፤ የሚያስከትለውን ውጤት መተንበይ አይቻልም።

ሆኖም እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ ከቴህራን ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ኃይሎች ጥቃት እንዲፈፅሙ ለማዘዝ ወስነዋል። ይህ ከሆነ ምን ሊከሰት ይችላል?

1. የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር

የአሜሪካ የአየር እና የባሕር ኃይሎች የተወሰኑ እና የተለዩ ዒላማዎች ላይ ብቻ ጥቃት ከፈፀሙ ኢራን ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ልትሸጋገር ትችል ይሆናል።

ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ጥቃቱ የተወሰኑ፣ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ወታደሮች እና በአብዮታዊ ዘቡ ሥር በሚንቀሳቀሱ የባሲጅ ታጣቂዎች ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ እንዲሁም በባልስቲክ ሚሳዔሎች መተኮሻ እና ማከማቻ ቦታዎች እንዲሁም የኢራን የኒውክሌር ማዕከላት ላይ ብቻ ከተፈፀመ ነው።

በዚህ ምክንያት ቀድሞውኑ የተዳከመው አገዛዝ ወድቆ ኢራን ሌላውን ዓለም መቀላቀል ወደምትችልበት ትክክለኛ የዲሞክራሲ ሥርዓት ልትሸጋገር ትችላለች።

ይህ ብሩህ የሆነው መላምት ነው።

ምክንያቱም የምዕራቡ ጦር በኢራቅ እና በሊቢያ ጣልቃ መግባቱ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርን አላመጣም። ምንም እንኳም ጣልቃ ገብነቱ በሁለቱም አገራት የነበረውን አምባገነን ሥርዓት ማስወገድ ቢችልም ለዓመታት አለመረጋጋትን እና ደም መፋሰስን አስከትሏል።

የራሷን አብዮት ያስነሳችው ሶሪያም ብትሆን ያለ ምንም የምዕራባውያን የጦር ድጋፍ ነው በ2024 ፕሬዚደንት ባሻር አል አሳድን ከሥልጣን ማስወገድ የቻለችው።

2. አገዛዙ ይተርፋል፤ ፖሊሲዎቹን ያሻሽላል

ይህ " የቬንዙዌላ ሞዴል" ሊባል ይችላል። በቅርቡ አሜሪካ በቬንዙዌላ ላይ የወሰደችው ፈጣን እና ከባድ እርምጃ አገዛዙ እንዲቆይ፤ ነገር ግን ፖሊሲዎቹ እንዲቀየሩ አድርጓል።

ኢራን አሁን ባለችበት ሁኔታ ይህ ማለት በበርካታ ኢራናውያን ዘንድ የማይወደደው የእስላማዊ ሪፐብሊክ አገዛዝ ከውድቀት ተርፎ፤ ነገር ግን በመካከለኛው ምሥራቅ ላሉ ታጣቂዎች ድጋፍ እንዳያደርግ ወይም በአገር ውስጥ የኒውክሌር እና የባሊስቲክ ሚሳዔል ፕሮግራሞቹን ለማቋረጥ እንዲሁም ተቃውሞን ማፈኑን እንዲያቆም ይገደዳል።

ይህ ይሆናል ብሎ ማሰብ ግን ከባድ ነው። ምክንያቱም እስላማዊው ሪፐብሊክ አገዛዝ ለ47 ዓመታት ያህል ይህን ሲቃወም ነው የቆየው። አሁንም አቅጣጫውን የሚቀይር አይመስልም።

3. አገዛዙ ይወድቃል፤ በወታደራዊ አስተዳደር ይተካል

ይህ ብዙዎች ሊሆን ይችላል ብለው የሚያስቡት ነው።

አሁን ያለው አገዛዝ በብዙዎች ዘንድ የሚደገፍ ባለመሆኑ እንዲሁም ለዓመታት በአገሪቷ እየተካሄዱ ባሉ ተከታታይ ተቃውሞዎች እየተዳከመ መጥቷል። ሆኖም አሁንም ግዙፍ እና ሰፊ የደኅንነት ሥርዓት አለው።

ተቃዋሚዎች አገዛዙን እስካሁን መገልበጥ ያልቻሉትም ከጎናቸው የሚቆሙ የፀጥታ ኃይሎች ባለመኖራቸው ነው።

እነዚህ ታማኝ የሆኑ ኃይሎች በተቃዋሚዎች ላይ በሚጠቀሙት "ጭካኔ የተሞላበት እና ያልተገደበ ኃይል" ምክንያት አገዛዙ ሥልጣን ላይ እንዲቆይ አድርገውታል።

በመሆኑም አሜሪካ ከምትፈፅመው ጥቃት በኋላ የሚፈጠረውን ግራ መጋባት ተከትሎ ኢራን በእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በተገነባ ጠንካራ ወታደራዊ አስተዳደር ትመራለች ተብሎ ይታሳበል።

4. ኢራን በአሜሪካ ኃይሎች እና ጎረቤቶቿ ላይ የአፀፋ ጥቃት ትሰነዝራለች

ኢራን "ጣቶቿ ቃታ ላይ" መሆናቸውን በመግለጽ ከአሜሪካ ለሚፈፀምባት ጥቃት የአፀፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ዝታለች።

ምንም እንኳን ያላት ኃይል ከአሜሪካ የባሕር እና የአየር ኃይል ጋር ሊወዳደር እንደማይችል ግልጽ ቢሆንም አሁንም በዋሻዎች፣ ከመሬት በታች ወይም ራቅ ባሉ ተራራዎች ውስጥ ተደብቀው በሚገኙ የባልስቲክ ሚሳዔሎች እና ድሮኖች የአፀፋ ምላሽ ልትሰጥ ትችላለች።

በአረብ ባሕረ ሰላጤ በኩል በሚገኙ በባህሬን እና በኳታር የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈሮች እንዲሁም መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ልትፈፅምም ትችላለች።

ከፈለገችም "የአሜሪካ ጥቃቶች ተሳታፊ ናቸው" ብላ በምታስባቸው እንደ ዮርዳኖስ ወይም እስራኤል ያሉ አገራትን አንዳንድ ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ማድረግ ትችላለች።

በአውሮፓውያኑ 2019 በኢራቅ ውስጥ በኢራን የሚደገፉ ሚሊሻዎች እንደተፈፀመ በተነገረው እና በሳዑዲ አራምኮ የፔትሮኬሚካል ተቋማት ላይ የተፈፀመው አውዳሚ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃት ሳዑዲዎች ለኢራን ሚሳዔሎች ምን ያህል ተጋላጭ እንደሆኑ አሳይቷል።

ሁሉም የአሜሪካ አጋር የሆኑት በአረብ ባሕረ ሰላጤ ላይ የሚገኙ የኢራን ጎረቤቶችም የአሜሪካ ወታደራዊ እርምጃ በእነሱ ላይ ጦስ ይዞ ሊመጣ ይችላል ብለው እየተጨነቁ ነው።

5. ኢራን በባሕረ ሰላጤው ቦምብ በመቅበር አጸፋ ትሰጣለች

ኢራን ከአውሮፓውያኑ 1980 እስከ 1988 ባሉት ዓመታት በተካሄደው የኢራን እና ኢራቅ ጦርነት ጀምሮ የመርከብ መስመሮች ላይ ቦምብ የቀበረች ሲሆን፣ በሮያል የባሕር ፈንጅ አምካኞች እስከሚፀዱ ድረስ ለዓለም አቀፍ የመርከብ ጉዞ እና የነዳጅ አቅርቦት ስጋት ሆኖ ቆይቷል።

በኢራን እና በኦማን መካከል የሚገኘው ጠባቡ የሆርሙዝ ሰርጥ ደግሞ ለዓለም ንግድ ወሳኝ ቦታ ነው።

በዓመት ወደ 20 በመቶ የሚሆነው የዓለም የተጣራ የተፈጥሮ ጋዝ እንዲሁም ከ20 እስከ 25 በመቶ የሚደርሰው ነዳጅ ዘይት እና የነዳጅ ተረፈ ምርቶች የሚያልፈው በዚሁ ወሽመጥ ነው።

ኢራን አሁን ላይ በፍጥነት የባሕር ቦምቦችን ለመቅበር ልምምድ ጀምራለች። ይህን ካደረገች የዓለም ንግድ እና የነዳጅ ዋጋ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ የማይቀር ነው።

6. ኢራን የአሜሪካን ግዙፍ የጦር መርከብን በማስመጥ አፀፋ ትሰጣለች

አንድ የአሜሪካ መርከበኛ በባሕረ ሰላጤው በሚገኝ የጦር መርከብ ላይ ሆኖ ኢራን "የተቀናጀ ጥቃት" ትፈፅማለች የሚል ስጋት እንዳለው ገልጿል።

ኢራን በአንድ ወይም በብዙ ዒላማዎች ላይ በርካታ ፈንጂዎችን በድሮኖች እና በፈጣን ባሕር ሰርጓጅ የጦር ጀልባዎች የምትተኩስበት ቦታ ይህ ነው። በዚህም ምክንያት የአሜሪካ የባሕር ኃይል መከላከያዎች ሁሉንም በአንድ ጊዜ ማስወገድ አይችሉም።

የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጥበቃም ከዓመታት በፊት በባሕረ ሰላጤው ውስጥ የነበረውን ባህላዊ ባሕር ኃይል በሌሎች ተክቷል። የተወሰኑ አዛዦቹም በሻህ ወቅት በዳርትማውዝ ሥልጠና ወስደዋል።

የኢራን የባሕር ኃይል አባላት በሥልጠናቸው ያተኮሩት "ባልተለመደ ወይም ያልተመጣጠነ ጦርነት" ላይ ሲሆን፣ ዋናው ጠላታቸው የሆነውም የአሜሪካ የባሕር ኃይል አምስተኛውን የጦር መርከብ በማጥፋት ወይም በማሳለፍ ሊያገኛቸው የሚችላቸውን ቴክኒካዊ ጠቀሜታዎች እየተመለከተ ነው።

መርከበኞቹን በመያዝ የጦር መርከቡን ማስመጥ ደግሞ ለአሜሪካ ትልቅ ውርደት ነው የሚሆነው።

ምንም እንኳን ይህ የማይመስል ቢሆንም በአውሮፓውያኑ 2000 በቢሊዮን ዶላር የሚገመተው የሚሳዔል አውዳሚ የጦር መርከብ በባሕረ ሰላጤው ነዳጅ እየሞላ ሳለ በአል ቃኢዳ የአጥፍቶ ማጥፋት ጥቃት ተፈፅሞበት 17 የአሜሪካ መርከበኞች ተገድለዋል።

ከዚህም በፊት በአውሮፓውያኑ 1987 የኢራቅ ጄት አብራሪ ሁለት ኤክሶሴት ሚሳዔሎችን ዩኤስኤስ ስታርክ በተባለ የአሜሪካ የጦር መርከብ ላይ በመተኮስ 37 መርከበኞችን ገድሏል።

7. አገዛዙ ይንኮታኮታል፤ ቀውስ ይፈጠራል

ይህ ኢራን ላይ የተደቀነ እውነተኛ አደጋ ነው።የጎረቤቶቿ ኳታር እና ሳዑዲ አረቢያ ዋነኛ ስጋቶች ውስጥም አንዱ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ልክ በሶሪያ፣ በየመን እና በሊቢያ እንደታየው የእርስ በርስ ጦርነት ሊከሰት ይችላል።

በሚፈጠረው ትርምስ እና ሁከት ውስጥም የሚፈጠረውን የኃይል ክፍተት ተከትሎ ኩርዶች፣ ባሉች እና ሌሎች በቁጥር አናሳ ጎሳዎች ሕዝባቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ሊፈጠር የሚችለው ውጥረት ወደ የትጥቅ ግጭት ሊያመራ የሚችልበት አደጋ አለ።

ይህም በኢራን የውክልና ጦርነት በቀጣናው ጥቃቶችን ያስተናገደቸው እና በኒውክሌር ፕሮግራሟ የኅልውና ስጋት የገባትን እስራኤል ብቻ ሳይሆን አብዛኞቹን የመካከለኛው ምሥራቅ አገራትን ሊያስደስት ይችላል።

ነገር ግን ትልቋ እና 93 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት የመካከለኛው ምሥራቅ አገር ወደ ትርምስ ውስጥ እንዲሁም የሰብዓዊ እና የስደተኝነት ቀውስ ውስጥ እንድትገባ ማንም ሰው አይፈልግም።

አሁን ላይ ትልቁ አደጋ ፕሬዚደንት ትራምፕ ከፍተኛ ኃይላቸውን ወደ ኢራን ድንበር ካስጠጉ በኋላ እርምጃ ለመውሰድ ወይም ኪሳራቸውን ለመጋፈጥ መወሰናቸው ነው።

ጦርነት የሚጀመረው ግልጽ የሆነ መጨረሻው ሳይታወቅ ቢሆንም፤ ሊገመት የማይችል ጎጂ ውጤት ማስከተሉ የማይቀር ነው።