የኢራን ተማሪዎች ፀረ መንግሥት ተቃውሟቸውን ቀጠሉ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በኢራን በሚገኙ በርካታ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች ባለፈው ወር ተቃውሞውን ለመቀልበስ መንግሥት አሰቃቂ እርምጃ ከወሰደ በኋላ በግዝፈቱ የመጀመሪያ ነው የተባለ ሠልፍ አካሄዱ።

ቢቢሲ በዋና ከተማው ቴህራን በሻሪፍ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ቅዳሜ ዕለት የተደረገ የተቃውሞ ሠልፍ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን አረጋግጧል።

በኋላ በተቃዋሚዎች እና በመንግሥት ደጋፊዎች መካከል ፀብ ተጀምሯል።

በሌላ የቴህራን ዩኒቨርስቲ ተቃዋሚዎች ቁጭ ብለው ተቃውሟቸውን ሲገልፁ፤ በሰሜን ምሥራቅ ደግሞ ሠልፍ መካሄዱ ተነግሯል።

ተማሪዎቹ ባለፈው ጥር በነበረው ተቃውሞ የተገደሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሠልፈኞችን እየዘከሩ ነበር።

ዩናይትድ ስቴትስ በኢራን አቅራቢያ ጦሯን እያጠናከረች ሲሆን፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መጠነኛ ወታደራዊ እርምጃ ለመወስድ እያሰቡ መሆኑን ተናግረዋል።

አሜሪካ እና አውሮፓውያን አጋሮች ኢራን የኒውክሌር መሳሪያ ለማልማት እየተሯሯጠች ነው ብለው ያምናሉ። ኢራን ሁሌም ይህን ክስ ታስተባብላለች።

ባለፈው ማክሰኞ አሜሪካ እና ኢራን በስዊዘርላንድ ተገናኝተው የኢራንን የኒውክሌር ፕሮግራም ለመቀነስ ተወያይተው ንግግሩ ለውጥ ማሳየቱን ተናግረዋል።

ምንም እንኳ ንግግሩ አዎንታዊ ለውጥ አለው ቢባልም ትራምፕ በሚቀጥሉት 10 ቀናት ኢራን ስምምነት ላይ ትደርሳለች ወይም አሜሪካ ወታደራዊ እርምጃ ስትወስድ ዓለም ይመለከታል ብለዋል።

የአሜሪካው መሪ ተቃዋሚዎችን የደገፉ ሲሆን፤ ተቃዋሚዎችን "እርዳታ እየመጣ ነው" በሚል ቃል ሲያበረታቱ ነበር።

በቢቢሲ የተረጋገጠ ተንቀሳቃሽ ምስል በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች አብዛኞቹ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓለማ ይዘው በሰላማዊ መንገድ ወደ ካምፓስ ሲተሙ ያሳያል።

ሠልፈኞቹ ዋና መሪውን አያቶላ አሊ ኻሚኒን በመጠቆም "ሞት ለአምባገነኑ" እና ሌሎች ፀረ መንግሥታዊ መፈክሮችን እያሰሙ ነበር።

ተቀናቃኝ መንግሥት ደጋፊ ሰልፈኞች ደግሞ በቅራቢያ የታዩ ሲሆን፤ ሁለቱ ሠልፈኞች በኋላ ላይ ፀብ ውስጥ ገብተዋል።

ቢቢሲ አሚር ካኒር በተባለ ሌላ የቴህራን ዩኒቨርስቲ የተካሄደን ሠልፍ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል አረጋግጧል።

በሰሜን ምሥራቅ ኢራን የአገሪቱ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ በሆነው ማሻድ ተማሪዎች "ነፃነት፣ ነፃነት" እና "ተማሪዎች ለመብታችሁ ጩሁ" የሚል መፈክር አሰምተዋል።

እስካሁን በቁጥጥር ስር የዋሉ ተቃዋሚዎች መኖራቸው ግልፅ አይደለም።

ባለፈው ወር በኑሮ ውድነት ምክንያት ተቃውሞ የተቀሰቀሰ ሲሆን፤ ከ1929 እስላማዊ አብዮት በኋላ ትልቁ ተቃውሞ ሆኗል።

በተቃውሞው ሕፃናትን ጨምሮ ከስድስት ሺህ ሰዎች በላይ መገደላቸውን የመብት ተሟጋች ቡድኖች አስታውቀዋል።