ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራን 'እጅ ከመስጠት' ይልቅ አሜሪካን እንድትጋፈጥ ሊያደርጓት የሚችሉ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
የአሜሪካ ጦር በመካከለኛው ምሥራቅ እያደረገ ያለው ወታደራዊ ኃይል የማሰባሰብ እንቅስቃሴ፤ ሊወስድ ስለሚችለው እርምጃ ምልክት ከመስጠት አልፎ ወደ ጥቃት ዝግጅትነት ተሸጋግሯል።
'የዩኤስኤስ አብርሃም ሊንከን' የተሰኘው ግዙፉ የአሜሪካ የአውሮፕላን ጫኝ መርከብ ወደ ኢራን የባሕር ዳርቻዎች እየተጠጋ መሆኑ ብቻውን ትልቅ እርምጃ ነው።
ከቀናት በፊት ደግሞ ሌላኛው የአውሮፕላን ጫኝ መርከብ "ዩኤስኤስ ጄራልድ አር ፎርድ' በጂብራልታር ወሽመጥ አቅራቢያ ሲቀዝፍ ታይቷል። በኢራን ላይ ሊፈጸም ለሚችል ወታደራዊ ጥቃት ድጋፍ ለመስጠት ወደ ምሥራቅ እየተጓዘ ነው።
ሌሎች የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይሎችም ወደ ቀጣናው መንቀሳቀሳቸው የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር፤ ያሉትን የተለያዩ አማራጮች እያሰባሰበ ነው የሚለውን ግምት አጠናክሯል።
እንደዚህ ዓይነት ወታደራዊ ስምሪቶች ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለመፍጠር ሊያግዙ ይችላሉ። የጦሩን እንቅስቃሴ በጥቅሉ ሲያስተውሉት ግን አሜሪካ እና ኢራን እያደረጉ ያሉት ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር ቅርቃር ውስጥ እንደገባም ሊያመለክት ይችላል።
ተደራዳሪዎቹ አቋማቸውን ለመቀየር የማይፈልጉ ከሆነ ደግሞ ቀጣዩ አማራጭ ወታደራዊ እርምጃ የመሆን ዕድሉን ያሰፋዋል።
መሠረታዊው ጥያቄ የሚነሳው እዚህ ጋር ነው። የዓለም ኃያል ወታደራዊ ኃይል ካላት አሜሪካ እና ከመካከለኛው ምሥራቅ ጠንካራ አጋሯ ጋር የተፋጠጡት የኢራን መሪዎች፤ ቢያንስ በሕዝብ ፊት እንኳ ቆራጥ አቋማቸውን ይዘው መቀጠል ይችላሉ?
የዚህ ጥያቄ መልስ የሚገኘው አሜሪካ ለንግግር ያስቀመጠቻቸው ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ ነው።
እጅ እንደ መስጠት የሚቆጠሩት የአሜሪካ ቅድመ ሁኔታዎች
አሜሪካ ያቀረበቻቸው ጥያቄዎች በኢራን መነጽር ሲታዩ የእጅ መስጠት እርምጃዎች እንጂ የድርድር ቅድመ ሁኔታዎች አይደሉም።
ከአሜሪካ ፍላጎቶች መካከል ኢራን ዩራኒየም የማበልጸግ ተግባሯን እንድታቆም ማድረግ እና የባሊስቲክ ሚሳዔሎቿ የሚወነጨፉበት ርቀት ለእስራኤል ስጋት በበማይፈጥር መልኩ እንዲቀንስ ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል።
ኢራን በመላ ቀጣናው ለሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች የምታደርገውን ድጋፍ ማቆም አለባት የሚለውን ከቅድመ ሁኔታዎቹ አንዱ ነው። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እንደሚናገሩት ኢራን የራሷን ዜጎች የምትይዝበትን መንገድ መቀየር አለባት የሚል ጥያቄም ቀርቧል።
ለኢራን አመራሮች እነዚህ ጥያቄዎች እምብዛም አስፈላጊ ያልሆኑ ፖሊሲዎች አይደሉም። የኢራን መንግሥት የአገር ደኅንነት ሥርዓቱን የዘረጋበትን መሠረት የሚንዱ ጉዳዮች ናቸው።
ኃያል ዓለም አቀፍ አጋር የሌላት ኢራን፤ ለዓመታት 'አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ' ስትል የምትጠራውን ራስን መከላከያ መዋቅር ስትገነባ አስርት ዓመታት አሳልፋለች።
ይህ መዋቅር የኢራን አጋር የሆኑ ታጣቂ ቡድኖች የያዘ መረብ ነው። ዋነኛ ግቡም ግጭቶች ከኢራን ድንበር እንዲርቁ እና እስራኤል ግፊት እንዲጨምርባት ማድረግ ነው።
የቴህራን የባለስቲክ ሚሳዔል ፕሮግራም እያረጀ ላለው የአገሪቱ አየር ኃይል እንዲሁም በአግባቡ መዘመን ላልቻለው የወታደራዊ ቴክኖሎጂ ዕድገት ምትክ ሆኖ አገልግሏል።
በይፋዊ መድረኮች ሰላማዊ ተብሎ የሚገለጸው የኒውክሌር ፕሮግራምም ቢሆን በስፋት የሚታየው ግጭትን ሳይከሰት ማስቀረት እንደሚችል ሀብት ነው።
ምንም እንኳን የበለጸገው ዩራኒየም ወደ የኒውክሌር መሣሪያነት ባይቀየርም፤ ስትራቴጂስቶች እንደሚናገሩት የማበልጸግ ሂደቱ በራሱ ኋላ ላይ በቀላሉ ወደ መሣሪያነት የመቀየር አቅም እንዲኖራት ያደርጋል።
ይህ ደግሞ ዩራኒየሙን ወደ ወታደራዊ መሣሪያነት ለመቀየር የሚያስችል መሠረተ ልማት እንዲኖር እና እዚህ ላይ ለመድረስ የሚቀረው ብቸኛ ነገር የፖለቲካ ውሳኔ እንዲሆን ዕድል ይከፍታል። ኢራን ይህንን አቅም መያዟ በራሱ የመደራደሪያ አቅሟ እንዲጨምር ያደርጋል።
ኢራን በዓመታት ሂደት የተገነቡትን እነዚህን ስልታዊ አቅሞች የምትነጠቅ ከሆነ ወታደራዊ እርምጃ እንዳይወሰድባት የዘረጋችው መዋቅር ከሥሩ እንደተናደባት ትቆጥረዋለች።
የኢራን ጠቅላይ መሪ ላይ የተጋረጠው ስጋት
ከኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ አንጻር ሲታይ፤ እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች መቀበል በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሚመራው የአሜሪካ መንግሥት ጋር ውስን ጦርነት ውስጥ ከመግባት የበለጠ አደገኛ ሆኖ ሊታይ ይችላል።
ምንም እንኳ ወታደራዊ ግጭት ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም፤ በሕይወት ተርፎ መውጣት የሚቻልበት እንደሆነ ሊታሰብ ይችላል። ሁሉንም ስትራቴጂያዊ ጥቅሞች፣ ተጽእኖዎች እና ወታደራዊ አቅሞች ማጣት ግን ምናልባትም ተርፎ የመውጣት ዕድልን አይሰጥም።
ይህ ዓይነቱ ስሌት የሚያመጣው ስጋት ግን እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። የሚያመጣው መዘዝም በኢራን ላይ ብቻ የሚያበቃ አይሆንም።
የትኛውም የአሜሪካ ወታደራዊ ዘመቻ በመጀመሪያው ምዕራፍ ዒላማ ሊያደርግ የሚችለው ከፍተኛ አመራሮችን ነው።
ጠቅላይ መሪው አያቶላህ ኻሜኒ የሚገደሉ ከሆነ ለሦስት አስርት ዓመታት የዘለቀው አገዛዝ እንዲያበቃ ብቻ አያደርግም። ሌላ መሪ ወደ ሥልጣን የሚመጣበት ሂደት እንዲናጋ ሊያደርግ ይችላል።
በእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ እና በሌሎች የደኅንነት ተቋማት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችም፤ በኢራን ታሪክ እጅግ ደም አፋሳሽ እና አስከፊ በሆነ እርምጃ ገና በቅርቡ ቁጥጥሩን መልሶ ያጠናከረውን የፀጥታ መዋቅር ሊያዳክም ይችላል።
ባለፉት ሳምንታት የኢራንን ጎዳናዎችን አጥለቅልቀው የነበሩት እና በተወሰደባቸው አስከፊ እርምጃ ምክንያት ብቻ ተቃውሟቸውን የገቱት ሰልፈኞች አሁንም ቅሬታ ውስጥ ናቸው።
ጉልበተኛ በሆነው የመንግሥት መዋቅር ላይ የሚፈጸም የትኛውም ድንገተኛ ጥቃት የአገር ውስጥ ሁኔታውን ወዳልተጠበቀ አቅጣጫ ሊወስደው ይችላል።
ቴህራን የዋሽንግተን ግብ የኒውክሌር እና የሚሳዔል አቅሟን በማዳከም ብቻ የተገደበ እንደሆነ ታስብ ይሆናል። ጦርነቶች አንዴ ከተጀመሩ በኋላ ግን ቀድሞ በተያዘላቸው አቅጣጫ የመጓዝ ዕድላቸው እምብዛም ነው።
ከወታደራዊ ዒላማዎች፣ ከጦርነት የቆይታ ጊዜ ወይም ከፖለቲካዊ ለውጦች ጋር በተያያዘ የሚፈጠር የተሳሳተ ስሌት ግጭቱ በፍጥነት እንዲስፋፋ የማድረግ ዕድል አለው።
ኢኮኖሚያዊ ጫናም ሌላው ስጋት የሚያጭር ጉዳይ ነው። በማዕቀብ፣ በዋጋ ግሽበት እና በአገሪቱ ገንዘብ የመግዛት አቅም መውደቅ ምክንያት ቀድሞውኑም የተጎዳው የኢራን ኢኮኖሚ ተጨማሪ ጫናዎችን ለመቋቋም ይቸገራል።
በነዳጅ ኤክስፖርት ላይ የሚፈጠር መስተጓጎል ወይም በመሠረተ ልማት ላይ የሚደርስ ጉዳት መፍትሔ ሳያገኝ፣ ታፍኖ የቆየውን የሕዝብ ቁጣ ያገነፍለዋል።
ከዚህ አንጻር ሲታይ ቆራጥ አቋም ይዞ መቆም በርካታ ዓላማዎችን ያሳካል። ለውጭ አካላት አይበገሬነትን፤ በአገር ውስጥ ደግሞ ጥንካሬን ያሳያል። በተቃራኒው ደግሞ ከአቋም ፈቀቅ ብሎ ስምምነት ላይ የመድረስ ዕድልን ያቀጭጫል።
የዋሽንግተን ስጋቶች
አሜሪካም ብትሆን የተጋረጡባት ስጋቶች ችላ የሚባሉ አይደሉም።
በወረቀት ላይ ሲታይ ውጥረቱ ይበልጥ የሚካረር ከሆነ የአገሪቱ ሠራዊት በጦር ኃይሎች ዋና አዛዡ የሚሰጠውን ትዕዛዝ የማሳካት አቅም አለው።
ውጊያ ግን የሚካሄደው ወቀረት ላይ አይደለም። ጦርነቶች አቅጣጫቸውን የሚይዙት በተሳሳቱ ስሌቶች፣ በሚባባሱ ውጥረቶች እና ባልተጠበቁ መዘዞች ነው።
ባለፈው ዓመት ከእስራኤል ጋር የተደረገው የ12 ቀናት ጦርነት በኢራን የዕዝ ሰንሰለት እና ወታደራዊ መሠረተ ልማት ያሉበትን ተጋላጭነቶች ይፋ አውጥቷል።
በተጨማሪ ግን እንዴት ራስን ከሁኔታዎች ጋር ማጣጣም፣ ጥቃቶችን መቋቋም፣ ራስን መልሶ ማደራጀት እና ምላሽ መስጠት እንደሚቻል ትምህርት ሰጥቷል።
ሁለቱ አገራት ሰፊ ግጭት ውስት የሚገቡ ከሆነ የትኛውም ወገን ያላሰበውን ነገር ሊከሰት ይችላል። ቴህራን ውስጥ ያለው ማዕከላዊ ሥልጣን መዳከሙ ብቻ በቀጥታ መረጋጋትን አልያም ከምዕራባውያን ፍላጎት መጣጣምን አያመጣም።
በዚህ መሃል የሚፈጠር የሥልጣን ክፍተት አዲስ፣ የተበታተነ እና አክራሪ እንዲወጣ ሊያደርግ ይችላል። ይህ ደግሞ በቀጣናው ያለውን ሚዛን ዋሽንግተን እና አጋሮቿ በማይፈልጉት መልኩ ያዛባዋል።
አያቶላህ አሊ ኻሜኒ በአሁኑ ሰዓት ፊታቸው የቀረቡት ጥሩ የሚባሉ አማራጮች ጥቂት ናቸው። አንዱ አማራጭ፤ የዋሽንግተንን ቅድመ ሁኔታዎች መቀበል፤ በሂደቱም አገዛዙ የገነባውን የመከላከያ ስትራቴጂን የሚያዳክመውን አደጋን መጋፈጥ ሊያስከትል ይችላል።
አልያም ደግሞ የአሜሪካ ፍላጎቶች ውድቅ አድርጎ የአገር ውስጥ ሁኔታው በተዳከመበት በዚህ ጊዜ ግጭት ውስጥ የመግባት ዕድሉ እንዲጨምር ማድረግ።
የኢራኑ ጠቅላይ መሪ፤ ስትራቴጂያዊ አቅምን አጥቶ እጅ መስጠትን "የከፋው" አማራጭ አድርገው ሊቆጥሩት ይችላሉ።
ውስን ግን ሊቋቋሙት የሚችሉት ጦርነት ውስጥ መግባት ደግሞ "ከመጥፎዎቹ አማራጮች የተሻለ" እንደሆነ ሊወስዱት ይቻላሉ። እስካሁን ባለው ሁኔታ ኢራን ቢያንስ በሕዝብ ፊት ወደዚህኛው አማራጭ እያዘነበለች ይመስላል።