በርካቶች ‘ጭንቀታም’ የሚሆኑት ለምንድን ነው?

በጣም የሚመኙትን ሥራ ለማግኘት አመለከቱ አንበል።

መሥሪያ ቤቱ ለቃለ መጠይቅ ጠራዎት። ከዚያም ቃለ መጠይቁን አለፉና ለሁለተኛ ቃለ መጠይቅ ቀጠሮ ተሰጠዎት።

የመጀመሪያውን ቃለ መጠይቅ በማለፍዎ ይደሰታሉ? ወይስ ሁለተኛውን ቃለ መጠይቅ ልወድቅ እችላለሁ ብለው ይጨነቃሉ?

ሁለተኛውን ቃለ መጠይቅ ካላለፍኩ “ጎበዝ ሰው አይደለሁም ማለት ነው” ብለው የሚጨነቁ ዓይነት ሰው ነዎት?

ሌላ ምሳሌ እንስጥዎት።

ለጓደኛዎ አጭር የጽሑፍ መልዕክት ላኩ እንበል።

ጓደኛዎ ግን ለመልዕክትዎ መልስ ሳይሰጥ ዘገየ።

“አስቀይሜው ይሆን? ተጣልቶኝ ይሆን?”. . . ወዘተ እያሉ አእምሮዎን ያስጨንቃሉ ወይስ ጓደኛዎ ለመልዕክትዎ መልስ ያልሰጠው ጊዜ ስላላገኘ እንደሆነ ያስባሉ?

አሁንም ሌላ ምሳሌ እንስጥዎት።

ለሰዓታት የኒውክሌር ጦርነት ሊነሳ ይችላል ብለው ይሸበራሉ? እንደ ኮሮናቫይረስ ያለ ወረርሽኝ ቢነሳስ ብለው ይጨነቃሉ? ወይም ደግሞ የሸቀጦች ዋጋ አሁን ካለው በላይ ሊወደድ ይችላ፣ ወይም ሌላ ችግር ሊፈጠር ብለው ይሰጋሉ?

እንደው ብቻዎን ሆነው፣ ባልተፈጠሩ ወይም ባልሆኑ ነገሮች የሚብሰለሰሉ ሰው ነዎት?

አእምሮዎ መጥፎ ነገርን አግዝፎ ያሳይዎታል?

ከላይ ለተነሱት ጥያቄዎች መልስዎ አዎ ከሆነ እዚህ ጽሑፍ ውስጥ ብዙ ጠቃሚ መረጃ ያገኛሉ።

እንዲህ ያለ የሥነ ልቦና ሁኔታን ሳይንስ catastrophising [መአት ማሰብ ልንለው እንችላለን] ልይለዋል።

መጥፎ ነገር ሊፈጠር የሚችልበትን መጠን አጋኖ ማየት ማለት ነው።

አንድ ነገር አሉታዊ ውጤት ሊኖረው ይችላል ብሎ የመስጋት ባህሪም ነው።

በካናዳ፣ አልበርታ የሥነ ልቦና ባለሙያና አማካሪ ዶ/ር ፓትሪክ ኬለን እንደሚሉት፣ ይህ የሥነ ልቦና ሁኔታ ክፉ ነገርን አባብሶ የሚያሳይ ነው። የአእምሮ ጤናን ያቃውሳል።

ሕመምን፣ መጥፎ ስሜትን፣ ጭንቀትን የሚያባብስ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ።

ባለንበት ወቅት ኮቪድ-19 የፈጠረው ጭንቀት እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ፖለቲካዊና የምጣኔ ሀብት ቀውሶች ብዙዎችን ያሰጋሉ።

በተለይም ነገሮችን በአሉታዊ መንገድ ብቻ የሚያይ አእምሮ ያላቸው ሰዎች በዚህ ወቅት የተባባሰ ጭንቅ ውስጥ ገብተዋል።

ይህንን የሥነ ልቦና ሁኔታ ለማሸነፍ ባለሙያዎች የተለያዩ መፍትሔዎች ይጠቁማሉ።

እስኪ እነዚህን ምክረ ሐሳቦች እንመልከት።

ከጭንቀት ነጻ መውጣት

እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች የአእምሮ ሕመምን የሚቃኙት በሲግመንድ ፍሮይ እና ሌሎች የሥነ ልቦና ሊቃውንት በተነደፏቸው መላ ምቶች ነበር።

በተለይም Cognitive Behavioural Therapy በመባል የሚጠራው መንገድ ግንባር ቀደሙ ነው።

ይህ የሥነ ልቦና ትንታኔ መነሻው ያደረገው ሰዎች አፍነው የያዟቸውን ፍርሃቶች እንዲሁም የተጨቆኑ ፍላጎቶቻቸውን ነው።

እነዚህ ፍርሃቶች እና የተጨቆኑ ፍላጎቶች በብዛት የሚፈጠሩት ወይም የሚዳብሩት በልጅነት ወቅት እንደሆነ እና አብዛኛው ይዘታቸው ወሲባዊ እንደሆነ እነ ፍሮይድ ያምናሉ።

ወሲባዊ ይዘት የሚያመዝንባቸው የተጨቆኑ ፍላጎቶች እና ፍርሃቶች ሥነ ልቦናዊ ቀውስ እንደሚፈጥሩም ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ።

እንደ አልበርት ኤሊስ እና አሮን ቤክ ያሉ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ግን ከእነ ፍሮይድ የተለየ የሥነ ልቦና ትንታኔ ፈጥረዋል።

የታፈነ የልጅነት ስሜትን ከመፈለግ ይልቅ አሁናዊ የአእምሮ ችግር ላይ ያተኮረ መላ ምትን ነድፈዋል።

የቅርብ ጊዜ ተመራማሪዎች ትኩረታቸውን ያደረጉት ወደ ጭንቀት የሚያመሩ ስሜቶች ላይ ነው።

ለምሳሌ ፍርሃትን እንውሰድ።

አንድ በአውሮፕላን የመጓዝ ፍርሃት ያለበት ሰው፣ በረራ ላይ ሆኖ በትንሹም ቢሆን አውሮፕላኑ ከተንገጫገጨ በከፍተኛ ጭንቀት ይዋጣል። ስለ ሞትም ደጋግሞ ያስባል።

ፍርሃት ውስጥ ያልሆነ ሰው በተቃራኒው፣ የበረራ አስተናጋጆች ላይ ምንም የሚረብሽ ነገር ካላየ መንገጫገጩ እምብዛም የከፋ እንዳልሆነ ይገነዘባል።

አሉታዊ ስሜትን የሚያጎሉ ሰዎች ለሌሎች ዓይነት የሥነ ልቦና መታወኮች እንደሚጋለጡ ጥናቶች ያሳያሉ።

ዶ/ር ፓትሪክ እንደሚሉት፣ እንደዚህ ያሉ ሰዎች ሥራ ላይ መጠነኛ ስህተት ቢሠሩ፣ “በቃ ልባረር ነው” ብለው ይሸበራሉ።

“ልባረር ነው” የሚለው ያልተጨበጠ ጭንቀት ጋር አያቆሙም።

“ከተባረርኩ በኋላ ቤተሰቤን ለማስተዳደር እቸገራለሁ” ወደሚል ስጋትም ያድጋል።

አንዳንዴ ጭንቀቱ ከቁጥጥራቸው ወጥቶ ሥራቸውን ማከናወን ሊሳናቸው ይችላል።

ጤናን እንደ ማሳያ ብንወስድ።

ጭንቀት የሚያጠቃቸው ሰዎች አንዳች የሰውነት ክፍላቸው ቢታመም “በቃ ካንሰር ይዞኛል” ብለው በሐዘን ሊዋጡ ይችላሉ።

ሰውነት ላይ የሚታይ ምልክትን ሁልጊዜ ከሕመም ጋር ማያያዝ ሌላው ችግር ነው።

ሰው በተሰበሰበበት ቦታ መናገር የሚፈራ ሰው ከፍርሃቱ የተነሳ ልቡ ቢመታ አይገርምም።

ይህ ሰው ጭንቀታም ከሆነ ግን ልቡ ሲመታ ፈርቼ ነው ከማለት ይልቅ “የልብ ድካም ይዞኝ ነው” ሊል ይችላል።

ፍርሃቱ ደግሞ ሌላ የሥነ ልቦና ቀውስ አስከትሎ ይመጣል።

በጀርመን የሥነ ልቦና ተመራማሪ የሆኑት ባርናባስ ኦስት እንደሚሉት፣ ሰውነት ላይ የሚታይ ቀላል ምልክትን በተጋነነ ሁኔታ የሚተረጉሙ ሰዎች ነገሮችን በእውን ካሉበት ደረጃ ያባብሳሉ።

ራስ ምታት ሲይዛቸው “ካንሰር ይዞኛል” ወደሚል ጭንቀት የሚገቡ ሰዎች ፍርሃታቸው በሕመሙ ምንጭ ብቻ አይገታም።

ከሕመሙ እስከወዲያኛው እንደማይፈወሱም ይሰማቸዋል።

ሰዎች ስለ ሕመማቸው በተጨነቁ ቁጥር አእምሯቸው ሕመሙን መቋቋም እየተሳነው፣ ሕመሙም እየተባባሰ ይሄዳል።

ሳይንቲስቶች ይህንን “እሳት ላይ ጋዝ መጨመር” ይሉታል።

ከሌላው ሰው በተለየ ለምን ይጨነቃሉ?

ለዚህ ምክንያቱ የተለያየ ነው።

ጭንቀት በአንድ በኩል ከዘረ መል ጋር ይያያዛል።

በሌላ በኩል ከቤተሰብ ወይም ከአካባቢ ይወረሳል።

ቤተሰቡ ቀላል ችግርን ውስብስብ ሲያደርግ እያየ ያደገ ልጅ ችግሮችን አጋኖ ቢመለከት አይገርምም።

አንዳች ዓይነት ችግር ውስጥ ያለ ሰው በሕይወቱ ያሉ ሌሎች ነገሮችንም ከችግር አንጻር ሊመለከት ይችላል።

እንደ ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዓይነት አስጨናቂ ነገሮችን ተከትሎ ወደተባባሰ ስጋት መግባት አንዱ ማሳያ ሲሆን፣ ምንም ችግር ሳይፈጠር አእምሮ ውስጥ ባለ ፍርሀት ብቻ በጭንቀት መዋጥ ሌላው ነው።

ስለ ጦርነት ወይም ስለ ምጣኔ ሀብት ማሽቆልቆል ዜና ከሰሙ በኋላ ስለ ራስ ዕጣ ፈንታ መብሰልሰል የሚታይባቸው ጥቂት አይደሉም።

ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ውስጥ የተሠራ አንድ ጥናትን እንደ ማስረጃ እንጥቀስ።

30 ሰዎች ተመረጡ።

ሦስት የሚያስጨንቋቸውን ነገሮች እንዲጽፉ ተመረጡ።

ከዚያም ገሚሱ ጥሩ ዜና የተቀሩት ደግሞ መጥፎ ዜና እንዲመለከቱ ተደረገ።

ከዚያ ሰዎቹ ስለ ችግራቸው እንዲያወሩ ተጠየቁ።

መጥፎ ዜና ያዩት ሰዎች ችግራቸውን እጅግ አባብሰው ሲገልጹ፣ ጥሩ ዜና ያዩት በተቃራኒው የተመዛዘነ ምልከታ ሰጡ።

ከዚህ ጥናት የምንረዳው መጥፎ ዜና አብዝተን ስንሰማ፣ ከመነሻውም ያለብን ችግር ተባብሶ እንደሚታየን ነው።

መፍትሔው ምንድን ነው?

ከጭንቀት መላቀቅ እንደሚቻል የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ያስረግጣሉ።

የመጀመሪያው ደረጃ አእምሯችን በፈጠራቸው ፍርሃቶች ሲጎተት ማወቅ ነው።

“የሥራ ቃለ መጠይቁን እወድቃለሁ” ወይም “አውሮፕላኑ ይከሰካል” አልያም “ካንሰር ይዞኛል” የሚል ሐሳብ ሲመጣ ቆም ብሎ ማሰብ ያሻል።

አማራጩ መውደቅ፣ መከስከስ ወይም መታመም ብቻ ሳይሆን አወንታዊ ውጤት ሊመጣ እንደሚችል ለራስ መንገድ ያስፈልጋል።

አእምሮ በግምት ሳይሆን በምክንያት ተመርኩዞ እንዲያሰላስል ማለማመድም ግድ ይላል።

አንድን ነገር ሙሉ አቅማችንን ሰጥተን ካከናወነው፣ ለምን ስለ ውድቀት እናስባለን?

ለምንስ አእምሯችን ባልተጨበጡ ፍርሃቶች እንዲዋጥ እንፈቅድለታለን?

የተሳሳተ ድምዳሜ፣ የተጋነነ ጭንቀት፣ ምክንያት አልባ ፍርሃት መወገድ ያለባቸው አሉታዊ ስሜቶች ናቸው።

ሌላው ነጥብ ውድቀትን እንደ ሕይወት መጨረሻ አለመመልከት ነው።

አንድ ነገር ካልተሳካ፣ ነገሩን መማሪያ አድርጎ ማለፍና ወደቀጣዩ የሕይወት ምዕራፍ መሻገር ያስፈልጋል።

ትንሽ ጉሮሯችንን ሲከረክረን ኮሮናቫይረስ እንደያዘን ለምን ይሰማናል? የነገሮች አሉታዊ ጎን ብቻ ለምን ይታየናል? ለምንስ ለድምዳሜ እንቸኩላለን?

አእምሯችን ወደ አሉታዊ ድምዳሜ እንዲንደረደር መፍቀድ አያዋጣም።

አእምሯችን ችግርን ሳይሆን መፍትሔን እንዲያይ ማለማመድ አለብን።

ነገሮችን በተመዛዘመ ሁኔታ ማጤን ለተሻለ ሕይወት ይረዳል።

አእምሮ በዘፈቀደ ከሚፈጠሩ የፍርሀት ቅጥልጥሎች ወጥቶ ምክንያታዊ በሆኑ ቅደም ተከተሎች እንዲያስብ ማላመድ እንዳለብን የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ራስን ወደ አወንታዊ አስተሳሰብ ማምጣት ቀላል አይደለም። ነገር ግን በተደጋጋሚ ከተደረገ ይለመዳል።

በቀላሉ ማድረግ የሚችሉትን መፍትሔ እንጠቁምዎ።

ባለፈው ጊዜ ወደ ክፉ ደረጃ ያመራል ብለው አስበውት በተቃራኒው በአወንታዊ ሁኔታ የተገባደደ ሁነትን አስታውሰው ይመዝግቡ።

እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎችን ደጋግመው ሲመዘግቡ፣ አእምሮ ነገሮችን አክፍቶ ከማየት እንዲወጣ ያላምዱታል።

በቀጣይ አንዳች ነገር ከማድረግዎ በፊት ነገሩ ሊሰናከል እንደሚችል ከማሰብ ይቆጠባሉ።