ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት፤ ፑቲን ሦስተኛውን የዓለም ጦርነት አስጀምረዋል አሉ
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ፤ 'ፕሬዝዳንት ፑቱን ሦስተኛውን የዓለም ጦርነት አስጀምረዋል፤ ወደ ኋላ እንዲመለሱ ማድረጊያው ብቸኛ መንገድ ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና ነው' ሲሉ ለቢቢሲ ተናገሩ።
እየተሸነፉ አለመሆኑን፤ በመጨረሻም ጦርነቱን በዩክሬን አሸናፊነት እንደሚጠናቀቅ የሚገልጹት ዜሌንስኪ፤ ይህንን የተናገሩት ኪዬቭ ውስጥ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ነው።
"ፑቲን አሁንም ቢሆን እንዳስጀመረው ነው የማምነው። ጥያቄው ምን ያህል ግዛቶችን መያዝ ይችላል እና እንዴት ማሰቆም ይቻላል የሚለው ነው... ሩሲያ በዓለም ላይ የተለየ የአኗኗር ዘይቤ መጫን እንዲሁም ሰዎች ለራሳቸው የመረጡትን ሕይወት መለወጥ ትፈልጋለች" ብለዋል።
ሩሲያ አሁን በእጇ ስር ስለሆነው እና እስከ መጨረሻው ተላልፎ እንዲሰጣት ስለጠየቀችው 20% በላይ የሚሆነው የምሥራቃዊ ዩክሬን ግዛት እንዲሁም ሌሎች የአገሪቱ መሬቶች ተጠይቀዋል። የተኩስ አቁምን እስካስገኘ ድረስ ይህ ጥያቄ ምክንያታዊ አይደለም ወይ የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።
ዜሌንስኪ በምላሻቸው "እኔ ይህንን ጉዳይ የምመለከተው በተለየ መንገድ ነው። በቀላሉ መሬት አድርጌ አልመለከተውም። አሳልፎ እንደ መስጠት፣ አቋማችንን እንደማዳከም፣ በዚያ የሚኖሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሕዝቦቻችንን እንደመተው ነው የምመለከተው። እኔ የማየው እንደዚህ ነው። 'ለቅቀን መውጣት' ማኅበረሰባችንን እንደሚከፋፍል እርግጠኛ ነኝ" ብለዋል።
ይህ ጥያቄ መመለሱ ብቻው የፕሬዝዳንት ፑቲንን ፍላጎት በዘላቂነት ያሟላል የሚል እምነት እንደሌላቸውም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል። "ምናልባት ለተወሰኑ ጊዜ ያረካም ይሆናል... የሚፈልገው ፋታ መውሰድ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
"እኔ እንደማስበው፤ ከሁለት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሊያገግም ይችላል። ቀጥሎ ወዴት ይሄዳል? አናውቅም። ነገር ግን [ጦርነቱን] መቀጠል እንደሚፈልግ ግልጽ ነው" ሲሉ ስጋታቸውን አጋርተዋል።
ባለፈው ሳምንት ዩክሬን እና ሩሲያ በአሜሪካ አሸማጋይነት ጄኔቫ ውስጥ ድርድር አካሂደዋል። ይህ ድርድር ስምምነት ላይ ሳይደረስ ተጠናቅቋል።
ድርድሩ ሊካሄድ በዝግጅት ላይ እያለ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባደረጉት ንግግር "ዩክሬን በፍጥነት ወደ ጠረጴዛው ብትመጣ ይሻላታል" ብለው ነበር። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጦርነቱን ለመቋጨት በሚያደርጉት ጥረት ከሩሲያ ይልቅ ዩክሬን ላይ ጫና ማሳደር መርጠዋል።
ትራምፕ የተኩስ አቁም ላይ ለመድረስ ሩሲያ ከዩክሬን የምትወስዳቸውን ግዛቶች በተመለከተ ላይ ስምምነት ላይ መደረስ አለበት የሚል አቋም እንደያዙ የምዕራባውያን ዲፕሎማቶች ሲጠቁሙ ሰንብተዋል።
ከዋይት ሐውስ ውጪ ያሉ በርካታ ተንታኞችም ዩክሬን ለሞስኮ ግዛቷን ሳትሰጥ ጦርነቱን ማሸነፍ አትችልም፤ ትሸነፋለች የሚል ግምገማ አስቀምጠዋል።
ዜሌንስኪ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ትራምፕ እና ሌሎች አካላት ስለሚያቀርቡት ይህ ግምገማ ምን እንደሚያስቡ ተጠይቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ በሰጡት ምላሽ "አሁን የት ነው ያለኸው?" ሲሉ የቢቢሲውን ጋዜጠኛ ጀርሚ ቦውንን መልሰው ጠይቀዋል።
"ዛሬ ኪዬቭ ውስጥ ነው ያለኸው፤ የአገራችን ዋና ከተማ ውስጥ፤ ዩክሬን ውስጥ ነው ያለኸው። ይህ በመሆኑ በጣም አመስጋኝ ነኝ። እንሸነፋለን? በፍጹም፤ ምክንያቱም እየተዋጋን ያለነው ለዩክሬን ነጻነት ነው" ብለዋል።
ዜሌንስኪ ደጋግመው የሚናገሩት የዩክሬን ድል ምን ሊመስል እንደሚችል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። ፕሬዝዳንቱ እንደሚናገሩት፤ ድል ማለት የዩክሬናውያንን መደበኛ ሕይወትን መመለስ እና የሚፈጸመውን ግድያ ማስቆም ነው።
በጥቅሉ ድል ብለው የሚጠሩት ግን በፑቲን ምክንያት ዓለም ላይ ተደቅኗል የሚሉትን ስጋት ማስወገድ ነው።
"ዛሬ ፑቲንን ማስቆም እና ዩክሬንን እንዳይወርር ማድረግ ለመላው ዓለም ድል ነው። ምክንያቱም ፑቲን በዩክሬን ብቻ አያቆምም" ሲሉ ተናግረዋል።