ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዩክሬን ጦርነት ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ ዘመናዊ መሣሪያዎች ስለጦርነቱ ምን ይነግሩናል?
ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ወረራ አራት ዓመቱን ሊደፍን ቢቃረብም መቋጫ ያልተገኘለት ውጊያው አሁንም እንደ ቀጠለ ነው።
በአሜሪካ አሸማጋይነት በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል በአቡዳቢ የተደረገው ሌላ ዙር የሰላም ንግግርም ያለ ውጤት ተጠናቋል።
እየተደረጉ ያሉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ለውጥ ያመጡ አይመስሉም። ጦርነቱ ስላለበት ደረጃ በሁለቱ ተፋላሚ አገራት ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች ምን ይነግሩናል? ጦርነቱ ስላለበት ደረጃ ፍንጭ ይሰጡን ይሆን?
አዲስ ሚሳዔሎች፡ ፍላሚንጎ እና ኦርሽኒክ
የሩሲያም ሆነ የዩክሬን ጦር ክሩዝ እና ባሊስቲክ ሚሳዔሎችን ይጠቀማሉ። አንዳንዶቹ አዲስ እና ገና በሙከራ ላይ ያሉ ናቸው።
ባለስቲክ ሚሳዔሎች ሊገመት የሚችል ርቀት ድረስ መጓዝ የሚችሉ ቢሆንም ዒላማቸውን ከመምታታቸው በፊት በራዳር ዕይታ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ።
ክሩዝ ሚሳዔሎች ደግሞ በዝቅተኛ ከፍታ ለመሬት ቅርብ ሆነው ነው የሚጓዙት። ይህ ግን ለመነሳት አስቸጋሪ ያደርጋቸዋል።
ዩክሬን ብዙውን ጊዜ ከምዕራባውያን አጋሮቿ የተሰጧትን ሚሳዔሎችን ትጠቀማለች።
አሜሪካ ሠራሾቹን 'አታክምስ' ባሊስቲክ ሚሳዔሎችን እና ረዥም ርቀት ተወንጫፊ 'ስቶርም ሻዶው' ወይም 'ስካልፕ' የተባሉ ክሩዝ ሚሳዔሎችን ወደ ሩሲያ ግዛቶች ተኩሳለች።
ስካልፕ ክሩዝ ሚሳዔሎች በዩናይትድ ኪንግደም እና በፈረንሳይ በጥምረት የተሠሩ ናቸው።
ሆኖም ዩክሬን በአገር ውስጥ ያላትን የጦር መሣሪያ ኢንደስትሪዋን እያሳደገች ነው።
የቢቢሲ የመከላከያ ዘጋቢ ጆናታን ቤል እንደሚለው ዩክሬን በዋነኛነት የምትጠቀመው የጦርነቱ ስልት ወደ ጠላት ቀጠና ዘልቆ በመግባት ወታደራዊ መሠረተ ልማቶች ላይ ከባድ ጥቃት መፈፀም ነው፤ ለዚህም በዋናነት ረዥም ርቀት የሚጓዙ ድሮኖችን ትጠቀማለች።
ዩክሬን በጦርነት 1 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ቦታ በሩሲያ ተይዞባታል። ይህንን ግስጋሴዋን ለመግታት የሩሲያን የጦርነት ኢኮኖሚ ዒላማ ለማድረግ እየሞከረች እንደሆነ ዘጋቢው ያስረዳል።
'ፋየር ፖይንት' በተባለ የዩክሬን የመከላከያ ተቋም የተሠራው ፍላሚንጎ ክሩዝ ሚሳዔል በኪየቭ የአገር ውስጥ የጦር መሣሪያ ምርት ላይ ወሳኝ አስተዋፅኦ አድርጓል።
ሚሳዔሉ ወሳኝ የሆኑ ዒላማዎችን ለመምታት የሚያስችል የጦር መሣሪያ እንደሆነ ዘጋቢው ገልጿል።
ይህ ክሩዝ ሚሳዔል ምዕራባዊያን ለዩክሬን ከመስጠት ከተቆጠቡት የጦር መሣሪያ ጋር የሚመሳሰል ነው።
ፍላሚንጎ በ3000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለ ዒላማን መምታት የሚችል ሲሆን፣ በሰዓት 900 ኪሎ ሜትር ይምዘገዘጋል። ከዚህም በተጨማሪ 1150 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ተተኳሾችን መሸከም ይችላል።
ይህ ማለት ድሮኖች ወይም እንደ 'ኔፕቱን' ያሉ አጭር ርቀት ሚሳዔሎች የማይደርሱበትን የሩሲያን ወሳኝ ዒላማዎች መምታት ይችላል ማለት ነው።
ሚሳዔሉ የሚጓዘው ርቀት ከአሜሪካ ሠራሹ 'ቶማሃውክ' ጋር ተመሳሳይነት አለው። ቶማሃውክ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ለዩክሬን አልሰጥም ያሉት በጣም የረቀቀ እና ውድ የሆነ ጦር መሣሪያ ነው።
ፍላሚንጎ ዩክሬን ራሷ ያመረተችው በመሆኑ የፈለገችውን ዒላማ መምታት ትችላለች። በምዕራባውያን አጋሮቿም ገደብ የተጣለበት መሣሪያ አይደለም።
የዩክሬኑ ፕሬዚደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ፍላሚንጎ ስኬታማ ከሆኑ የአገራቸው ሚሳዔሎች አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል። ሆኖም ሚሳዔሉ ጥቅም ላይ ስለመዋሉ የሚያሳዩ ዝርዝር መረጃዎች የሉም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ ደግሞ ኦርሽኒክ የተባለ 5500 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚጓዝ አዲስ ሚሳዔል ሠርታለች።
ኦርሽኒክ በፍጥነቱ ከሌሎች ባሊስቲክ ሚሳዔሎች የላቀ ነው። የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን በ2024 ሚሳኤሉ በሰከንድ ከ2.5 እስከ 3 ኪሎ ሜትር ድረስ እንደሚጓዝ ተናግረዋል። ይህም ሚሳዔሉን ለማክሸፍ ለዩክሬን አስቸጋሪ ያደርግባታል።
ሩሲያ እስካሁን በጦርነቱ ኦርሽኒክ ሚሳዔልን ሁለት ጊዜ ተጠቅመዋለች።
መጀመሪያ ላይ በኅዳር 2024 በዲኒፕሮ ከተማ ላይ ሲሆን፣ ሌላኛው ባለፈው ጥር ወር በምዕራባዊቷ ከተማ ልቪቭ ላይ ነው።
ሚሳዔሉ የታቀደለት ስፍራ ላይ ሲደርስ በራሱ ለብዙ በመከፋፈል ዒላማዎችን መለየት እና መምታት እንዲሁም ተደጋጋሚ ፍንዳታዎች እንዲከሰቱ ማድረግ የሚያስችል ተተኳሾች እንዳሉት ይታሰባል።
ተዋጊ ጄቶች፡ ኤፍ -16 እና ሱኮይ
ዩክሬን ቤልጂየም፣ ዴንማርክ፣ ኔዘርላንድስ እና ኖርዌይን ጨምሮ ከሰሜን የጦር ቃል ኪዳን ማኅበር (ኔቶ) አባል አገራት ቃል ከተገባላት 90 የሚሆኑ ኤፍ -16 ተዋጊ ጄቶች ግማሽ ያህሉን ተቀብላለች ተብሎ ይገመታል።
እነዚህ ጄቶች ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ፣ በቀላሉ መጠገን የሚችሉ እና በአሜሪካ እና በኔቶ አገራት የተመረቱ ማንኛውንም የጦር መሣሪያዎችን መሸከም እንደሚችሉ ይታሰባል።
ኤፍ -16 መጀመሪያ ላይ አገልግሎት ላይ የዋለው በአውሮፓውያኑ 1978 በአሜሪካ ነው። በርካታ የምዕራባውያን ጦሮች እነዚህን ተዋጊ ጄቶች ከአገልግሎት ለማስወጣት ሒደት ላይ ሲሆኑ፣ በ2015 በተዋወቁት አሜሪካ ሠራሽ ኤፍ - 35 እየተኳቸው ነው።
ሆኖም ከ1970ዎቹ ጀምሮ የሶቭየት ተዋጊ ጄት የሆነውን ሚግ-29ን ሲጠቀም ለነበረው ለዩክሬን አነስተኛ አየር ኃይል ኤፍ-16 ትልቅ ለውጥ አምጥተዋል።
አንድ ዩክሬናዊ የጦር ጄት አብራሪ ኤፍ-16 ለመጀመሪያ ጊዜ ሲተዋወቅ ያለውን አድናቆት በብሔራዊ ቴሌቪዥን ገልጿል።
አብራሪው "ኤፍ-16ን አሁን ከምንጠቀመው አውሮፕላን ጋር ስናወዳድረው ልክ መጀመሪያ ላይ ከመጣው የሞባይል ስልክ በኋላ እንደተፈጠረው ዘመናዊ ስልክ ማለት ነው" ብሏል።
ኤፍ-16 በዋናነት ጥቅም ላይ የሚውለው የአየር መከላከያን ለማጠናከር እና የምድር ጥቃቶችን ለመፈፀም ነው።
ዩክሬናዊው አብራሪ እንደሰጠው ምስክርነት ከሆነ ተዋጊ ጄቱ ጥሩ ስኬቶችን አስመዝግቧል።
ታኅሳስ 2024 በአንድ የውጊያ ተልዕኮ ወቅት አንድ የዩክሬን አብራሪ ስድስት የሩሲያን ክሩዝ ሚሳዔሎችን መምታቱን የአገሪቷ አየር ኃይል አስታውቋል።
እንዲህ ዓይነት የአየር ጥቃት መከላከያ ተልዕኮዎችን ለመፈፀም ኤፍ-16 ተዋጊዎች ለዩክሬን ወሳኝ ሚና አላቸው።
የሩሲያ ዘመናዊ የውጊያ አውሮፕላኖች መሠረታዊ ጥንካሬ የሱኮይ ቤተሰብ የሆኑ ሱ-30፣ ሱ-34 እና ሱ-35 የተባሉ አውሮፕላኖች ናቸው።
አምስተኛ ትውልድ የሆነው ሱ-57 በዚህ ዝርዝር ውስጥ ያልተካተተው በብዛት እየተመረተ ባለመሆኑ እንደሆነ የቢቢሲ የሩሲያ አገልግሎት ገልጿል።
የሩሲያ ሱኮይ አውሮፕላኖች ዘመናዊ ራዳሮች እና በአየር ላይ የሚጓዙ ረዥም ርቀት ሚሳዔሎች አሏቸው።
ለምሳሌ አር-37 ከ200 ኪሎ ሜትር በላይ እንደሚጓዝ የሚነገር ሲሆን፣ ትልቅ ሚሳዔል እና ተተኳሽ መሸከም ይችላል። ከሚግ-29 እና ኤፍ-16 በተሻለም ይበራል።
በዓለም ላይ ያሉ ዘመናዊ የጦር አውሮፕላኖችን የሚመዘግበው ተቋም እንዳለው የሩሲያ አየር ኃይል በዓለማችን ካሉ ጠንካራ አየር ኃይሎች ከአሜሪካ በመቀጠል ሁለተኛው ነው።
ባሏት ተዋጊ አውሮፕላኖች ብዛትም ሩሲያ በዩክሬን ላይ ሰፊ የሆነ የበላይነት አላት።
እነዚህ የሩሲያ አውሮፕላኖች ወደ ዩክሬን ግዛት የሚገቡት ግን አልፎ አልፎ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ለዩክሬን ከምዕራባውያኑ በተለገሰ እንደ ፓትሪዮት ባሉና በየትኛውም የአየር ጠባይ በሚሠሩ ከመሬት ወደ አየር በሚተኮሱ ሚሳዔሎች ላለመመታት በመስጋት ነው።
አሁን ላይ ባለው ግጭት የአየር በአየር ውጊያዎች የሚካሄዱትም አልፎ አልፎ እንደሆነ የቢቢሲ ኒውስ ሩሲያ ኢልያ አቢሽቭ ይናገራል።
አቢሽቭ እንደሚለው ሁለቱ ወገኖች ብዙውን ጊዜ በጠላት የአየር መከላከያ ቀጠና ውስጥ ሳይገቡ ለምድር ጥቃት ተዋጊ አውሮፕላኖቻቸውን፣ ለረዥም ርቀት ደግሞ ሚሳዔል እና ከርቀት የሚጣሉ ቦምቦችን ነው የሚጠቀሙት።
ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን)?
በሁለቱ አገራት ጦርነት ለቅኝት፣ ዒላማን ለመምታት እና ሚሳዔሎችን ለመተኮስ እና አጥፍቶ ለመጥፋት ሰው አልባ አውሮፕላኖች በብዛት ጥቅም ላይ ውለዋል።
የቢቢሲ የመከላከያ ዘጋቢ እንዳለው አሁን ላይ ዩክሬን እንደ ሮቦት እና አብራሪ የሌላቸውና ከርቀት ሊቆጣጠሯቸው የሚችሉ ድሮኖች ያሉ ሥርዓቶችን በመሥራት አብዛኛውን ዓለም ትመራለች።
አገሪቷ በዓመት አራት ሚሊዮን ድሮኖችን እንደምታመርትም ኅዳር ወር ላይ ብሉምበርግ ዘግቧል።
ባለፈው ዓመት ዩክሬን ባካሄደችው ዘመቻ ከ110 በላይ ድሮኖቿ በድብቅ ወደ ሩሲያ ገብተው ከ40 በላይ ቦምብ ጣይ ጄቶች ላይ ጥቃት መፈፀማቸው የዩክሬን ድሮኖች ስኬታማነት ማሳያ ነበር።
ዩክሬን በጦር ግንባሮች ተዋጊ ድሮኖች፣ በባሕር ደግሞ የባሕር ድሮኖችንም የምትጠቀም ሲሆን በርካታ የሩሲያ የጦር መርከቦችን ለማስመጥ ረድተዋታል።
እንደ ኤፍፒ-1 እና ኤፍፒ-2 ያሉ አንዳንድ ዩክሬን ሠራሽ ድሮኖች ርካሽ ሲሆኑ፣ በፍጥነት የሚመረቱም ናቸው። ኤፍፒ-1 የሩሲያ መዲና ሞስኮ ድረስ መጓዝ ይችላል።
ከዚህም በተጨማሪ ዩክሬን በጦርነቱ መጀመሪያ ወቅት ከቱርክ ያገኘቻቸውን በመካከለኛ ከፍታ የሚበሩ ሚሳዔል ተኳሽ 'ባይራክታር ቲቢ2' ድሮኖችን፣ ከአሜሪካ ያገኘችውን በጣም ትንንሽ አጥፍቶ ጠፊ ድሮኖችን እንዲሁም ቻይና ሠራሽ 'ዲጄአይ ማቪክ 3' የቅኝት ድሮኖችን ተጠቅማለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ የምታመርታቸውን ርካሽ የሆኑ ተዋጊ ድሮኖችን ቁጥር በዓመት ወደ 10 ሺህ ማድረስ እንደምትፈልግ የቢቢሲ የሩሲያ አገልግሎት ዘግቧል።
ኅዳር ወር ላይ ሩሲያ ሰው የማይቆጣጠረው ኃይል ማቋቋሟን አስታውቃለች። አዲሱ ዕዝ ሁሉንም የድሮን ፕሮግራሞቿን የሚቆጣጠር እንደሆነም የሩሲያ የዜና ወኪል ታስ ዘግቧል።
ይህም በመከላከያ ስትራቴጂዎቿ ውስጥ ድሮን ማምረት ቅድሚያ የምትሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ያመለክታል ብሏል የቢቢሲ የሩሲያ ዘጋቢ።
ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት በሩሲያ ሚዲያ ዘገባዎች ውስጥ አርትሚስ-10፣ ቱቪክ፣ ሲሪስ እና ሌሎች በርካታ የድሮን ምርቶች ተጠቅሰዋል። በዘገባው እነዚህ ድሮኖች በጣም ዘመናዊ እና በብዛት ለመመረት ዝግጁ የሆኑ እንደሆነ ተገልጿል።
ሆኖም በጦርነቱ ጥቅም ላይ መዋላቸውን የሚያሳዩ ምንም ዓይነት ሪፖርቶች የሉም።
የቢቢሲ የሩሲያ አገልግሎት እንደዘገበው በሩሲያ ጦር ጥቅም ላይ የሚውሉ አዳዲስ ድሮኖች ቁጥር ያን ያህል ብዙ አይደሉም።
በ2025 ሩሲያ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ እና ለአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት የሚውሉ እንደ ሞልኒያ-2 ያሉ ድሮኖቿን ማዘመኗን ቀጥላለች ።
ሩሲያ ቀደም ብሎ ሻሂድ የተባሉ ድሮኖችን ከኢራን አስገብታ የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ላይ እንደ ሻሂድ ያሉ ጅራን 2 የተባሉ ክንፍ ያላቸው እና የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት ለመፈፀም የሚያስችሉ የራሷን ድሮኖች እያመረተች ነው።
ጅራን ድሮኖች ብዙውን ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉት የዩክሬን ከተሞችን፣ የትራንስፖርት አውታሮችን እና የሲቪል እና ወታደራዊ መሠረተ ልማቶችን ለመምታት ረዥም ርቀት ጥቃቶችን ለመፈፀም ነው።
ሩሲያ አሁንም በወር ወደ 3000 የሚጠጉ ጅራን ድሮኖች ታመርታለች። መቀመጫውን በዋሽንግተን ያደረገ የሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ደኅንነት ተቋም ትንታኔ እንደሚያሳየው በ2025 የበጋ እና ፀደይ ወቅት በአማካይ 175 የሻሂድ ዓይነት ድሮኖችን አስመርቃለች።
በዚህ ሁሉ ውስጥ በሁለቱም ወገኖች ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድረው የግንኙነት መስመር ነው። አንዳንድ ድሮኖች ለማሰስ የሳተላይት የግንኙነት መስመሮች ያስፈልጋቸዋል።
ኤለን መስክ በቅርቡ ሩሲያ ለድሮን ጥቃቶቿ ስታርሊንክ ሳተላይቶቹን መጠቀሟን እንድታቆም ጥረት ሲያደርግ ነበር። የዩክሬን ባለሥልጣናትም ይህ ውጤት ማምጣቱን ተናግረዋል።
የሩሲያ የሳተላይት ሥርዓት ጋዝፕሮም ስፔስ ከስታርሊንክ ጋር ሲነፃፀር በጣም ውስን እንደሆነ የቢቢሲ የሩሲያ አገልግሎት ዘጋቢ ኢልያ አቢሽቭ ይናገራል።
ሌሎቹ አማራጮች ድሮኖችን ከፋይበር ኦፕቲክ ገመዶች ጋር ማገናኘት ወይም የራዲዮ ማሠራጫዎችን መጠቀም ነው። ነገር ግን እነዚህም የሚሸፍኑት ርቀት አጭር ሲሆን ውጤታማነታቸው እና አስተማማኝነታቸው ላይ ጥያቄ ይነሳል እንዱሁም ርካሽ አይደሉም ሲል አክሏል።
ወደፊትስ ምን ዓይነት መሣሪያዎች ልዩነት ሊፈጥሩ ይችላሉ?
በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል ሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) በቴክኖሎጂው ውድድር ሌላኛው ግንባር ሆኗል።
የቢቢሲ የዩክሬን ዘጋቢ ኦሌህ ችርንይሽ እንደሚለው ኤአይን የሚጠቀሙ አዳዲስ የጦር መሣሪያዎች አሁን በጦር ሜዳ ያለውን ሁኔታ ሊቀይሩት ይችላሉ።
እንዲህ ዓይነት ለውጦች በሒደት ላይ መሆናቸውንም የዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር ሚኪያሄሎ ፍዶሮቭ ተናግረዋል። ሆኖም እስካሁም ውጤታማ በሆነ መንገድ ኤአይን የሚጠቀሙ የጦር መሣሪያዎች የሉም።
ይህ ሙከራ ስኬታማ ከሆነ ግን አነስተኛ ድሮኖች ሳይቀሩ ውጤታማነታቸው በፍጥነት እንደሚጨምር ዘጋቢው ያስረዳል።
እንደ የቢቢሲ የሩሲያ አገልግሎት ከሆነ ክሬሚሊንም የኤአይን አልጎሪዝም በመጠቀም ዒላማዎችን የሚለዩ፣ የሚከታተሉ እና የሚመቱ ድሮኖችን እየሠራች ነው።