ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሽብር ወንጀል ተከሳሾች “ገለልተኛ አይደሉም” ያሏቸው የመሃል ዳኛ እንዲነሱ ጠየቁ
በእነዶክተር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ የፍርድ ሂደታቸውን እየተከታተሉ ያሉ ተከሳሾች የመሃል ዳኛው ጉዳያችንን በገለልተኛነት ሊዳኙ አይችሉም በሚል በሌላ እንዲተኩላቸው ጠየቁ።
ዛሬ ሐምሌ 25/2015 ዓ.ም. የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ችሎት በዋለው ችሎት በሚዲያ ሥራ ላይ የተሰማሩትን መስከረም አበራ፣ ዳዊት በጋሻው እና ጎበዜ ሲሳይ ባከተተው መዝገብ የተከሰሱት ግለሰቦችን ጉዳይ ተመልክቷል።
ፍርድ ቤቱ በውሎው በዋናነት ይመለከተዋል ተብሎ ተጠብቆ የነበረው የምስክሮችን ጉዳይ ቢሆንም፣ ተከሳሾች ጉዳዩን ለመመልከት በመሃል ዳኝነት በተሰየሙት ግለሰብ ላይ ቅሬታ አቅርበዋል።
በዚህም የመሃል ዳኛው በሌላ እንዲተኩ መጠየቃቸው በተከሳሾች እና በችሎቱ መካከል “ከፍተኛ እሰጠገባ” መፍጠሩን ከተከሳሾች ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት ሄኖክ አክሊሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ሰብሳቢው ዳኛ ረቡማ ተፈራ በጉዳዩ ላይ ገለልተኛ ስላልሆኑ ሊዳኙን አይገባም በማለት በማስረጃ አስደግፈው ከችሎት እንዲነሱላቸው ጥያቄ ለችሎቱ አቅርበዋል” ብለዋል ጠበቃው።
ይሁን እንጂ ችሎቱ ጥያቄው በቃል ሳይሆን በጽሑፍ ይቅረብልኝ ማለቱ በችሎቱ ውስጥ ከፍተኛ አለመግባባት መፍጠሩን አቶ ሄኖክ ይገልጻሉ።
“ከፍተኛ ሊባል የሚችል እሰጣ አገባ ነበረ። ተከሳሾቹ ‘ልንደመጥ ይገባናል። ምን እንዳቀረብን እዚሁ የሚገኙ የሚዲያ አካላት፣ ቤተሰቦቻችን እና ጉዳዩን ሊታደሙ የሚመጡ ሰዎች በማያውቁበት ሁኔታ በጽሑፍ ብቻ ለችሎት መስጠቱ የመደመጥ መብታችንን ይጎዳናል’ በማለት ተከራክረዋል” ብለዋል ጠበቃ ሄኖክ።
ቅሬታ የቀረበባቸው ዳኛ፣ ተከሳሾች ጥያቄውን የማቅረብ መብት እንዳላቸው ገልጸው በጽሑፍ ያቀረቡት ጥያቄ ከክስ ወረቀቱ ጋር እንዲያያዝ መደረጉን ተናግረዋል።
ተከሳሾች የመሃል ዳኛው እንዲነሱላቸው ያቀረቡትን ጥያቄም ፍርድ ቤቱ ተመልክቶት በቀጣይ ቀጠሮ መልስ ይሰጣል ብለን እንጠብቃለን ብለዋል የተከሳሾች ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ።
በዶ/ር ወንደወሰን አሰፋ ስም እየታየ ባለው መዝገብ የተከሰሱት 51 ሰዎች ሲሆኑ፣ 23 ያህሉ የሚሆኑት ናቸው ባለፉት ጊዜያት ችሎት በመቅረብ ጉዳያቸውን እየተካታተሉ ያሉት። ሌሎቹን ፖሊስ መጥሪያ በማድረስ በችሎት ተገኝተው ክሳቸውን እንዲከታተሉ ማዘዙ ይታወሳል።
ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት እና ተሳታፊነት የሽብር ድርጊት በመምራት፣ በማደራጀት ከ200 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሕይወት ማለፉ ምክንያት መሆናቸውን ዐቃቤ ሕግ ክስ አቅርቦባቸው፣ የዋስትና መብት ጥያቄያቸው በፍርድ ቤት ውድቅ ተደርጓል።
የመገናኛ ብዙኃን ዘገባ
ችሎቱ በዛሬው ውሎው ከሁለት ሳምንት በፊት ተከሳሾቹን በተመለከተ መንግሥታዊ መገናኛ ብዙኃን ያቀረቧቸው ዘገባዎችን እንዲያነሱ የሰጠው ውሳኔ ውጤትን ተመልክቷል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ችሎት ረቡዕ ሐምሌ 12/2015 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የመንግሥት እና የፓርቲ መገናኛ ብዙኃን የተከሳሾችን ምስል ከጦር መሳሪያዎች ጋር አቀናብረው ያቀረቧቸው ዘገባዎች እንዲነሱ ውሳኔ ሰጥቶ ነበር።
ተከሳሾቹ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቲቪ)፣ ፋና ቴሌቪዥን፣ አማራ ክልል መገናኛ ብዙኃን (አሚኮ)፣ ኦሮሚያ ክልል መገናኛ ብዙኃን (ኦቢኤን) እና ዋልታ ቴሌቪዥን ያቀረቧቸው ዘገባዎች ነጻ ሆነን የመገመት መብታችንን ይጋፋል በሚል ነበር ዘገባዎቹ እንዲነሱ ጠይቀው የነበረው።
ቅሬታውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ዘገባዎቹ እንዲነሱ ትዕዛዝ ሰጥቶ የነበረ ሲሆን ከኦሮሚያ ክልል መገናኛ ብዙኃን (ኦቢኤን) በስተቀር ከላይ የተጠቀሱት መገናኛ ብዙኃን ትዕዛዙን መፈጸማቸውን ለፍርድ ቤቱ ማሳወቃቸውን ጠበቃው ሄኖክ አክሊሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ከኦቢኤን ውጪ መገናኛ ብዙኃኑ የሠሯቸውን ዘገባዎች እንዳነሱ ለፍርድ ቤቱ በጽሑፍ አስታውቀዋል። ኦቢኤንን በተመለከተ ግን የተባለ ነገር የለም። ተቋሙም የሰጠው ምላሽ የለም” ብለዋል ጠበቃ ሄኖክ።
ምስክሮች
በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ ሌላው መከራከሪያ የነበረው የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ጉዳይ እንደነበረ ሄኖክ አክሊሉ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎት ዐቃቤ ሕግ አሉኝ የሚላቸውን የምስክሮች ዝርዝር ተከሳሾች እንዲደርሳቸው ጠይቀው እንደነበረ ጠበቃው ያስታውሳሉ። ይሁን እንጂ ዐቃቤ ሕግ የምስክሮቼን ዝርዝር ለተከሳሾች ባደርስ ምስክሮቹ ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል የሚል መከራከሪያ አቅርቦ ነበር ይላሉ።
በጉዳዩ ላይ ዛሬ ፍርድ ቤቱ ብይን ይሰጣል ተብሎ ቢጠበቀም ችሎቱ ግን በመዝገቡ ከተከሰሱ 51 ተከሳሾች ውስጥ በችሎቱ ጉዳያቸውን እየተከታተሉ ያሉት 23 ስለሆኑ ለጉዳዩ ውሳኔ መሰጠት ያለበት በጠቅላላው እንጂ በተናጠል ሁኔታ ብይን አልሰጥም በማለቱ ጉዳዩን በቀጠሮ አሻግሮታል ብለዋል።
ችሎቱ ለጥቅምት 15/2016 ዓ.ም. የተቀጠረ ሲሆን፣ ችሎቱ ከተነሳ በኋላ ተከሳሾች ስሜታቸውን በዜማ ማሰማታቸውን ጠበቃ ሄኖክ ጨምረው ለቢቢሲ ተናግረዋል።