ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
መከላከያ ሠራዊት “በፋኖ ስም በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ እወስዳለሁ” አለ
የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት በአማራ ክልል በፋኖ ስም በሚንቀሳቀሱ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ሸኔ በተሰኘው ታጣቂ ኃይሎች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ገለጸ።
ባለፉት ዓመታት መንግሥት ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ክፍሎች ግጭቶች ውስጥ የቆየ ሲሆን፣ ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነትን ማብቃት ተከትሎ በአማራ ክልልም ተመሳሳይ ግጭቶች እያጋጠሙ መሆናቸው ሲዘገብ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 25/2015 ዓ.ም. የሰጡትን መግለጫ ጠቅሶ ብሔራዊው ቴሌቪዥን እንደዘገበው፣ ሠራዊቱ “በፋኖ ስም እየተንቀሳቀሱ ሰላም በሚያውኩ ላይ እርምጃ ይወሰዳል” ብለዋል።
ከወራት በፊት የፌደራል መንግሥቱ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደረጃት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በአማራ ክልል ተቃውሞ እና ግጭቶች ያጋጠሙ ሲሆን፣ በአንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች ታጣቂዎች ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ጋር መጋጨታቸው ተዘግቧል።
ይህንንም ተከትሎ የክልሉ እና የፌደራል መንግሥቱ የፀጥታ ኃይሎች ሕግ ማስከበር ባሉት እንቅስቃሴ ባለፉት ወራት በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ከታጣቂዎች ጋር በተካሄዱ ግጭቶች የሰው ሕይወት የጠፋ ሲሆን አሁንም ውጥረት አለ።
በጎንደር፣ በቆቦ፣ በወልዲያ፣ በሸዋ ሮቢት እና በሌሎችም አካባቢዎች ባለፉት ሳምንታት ታጣቂዎች ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር ከመጋጨታቸው በተጨማሪ ጥቃቶች ተፈጽመው ጉዳት መድረሱ ይታወቃል።
የመከላከያ ሠራዊቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው በሰጡት መግለጫ ላይም ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል በጎንደር በሠራዊቱ አባላት ላይ ጯሂት እና ቆላድባ በተባሉ አካባቢዎች ድንገተኛ ጥቃቶች ተከፍቶባቸው እንደነበረ ተናግረዋል።
ነገር ግን በእነዚህ ድንገተኛ ጥቃቶች ስለደረሰ ጉዳትም ሆነ ስለ ክስተቱ የሰጡት ዝርዝር መረጃ ስለመኖሩ ግልጽ ባይሆንም፤ ሠራዊቱ ከአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ከወጣቶች እና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር ውይይት አካሂዶ ክስተቱ “በይቅርታ ተዘግቷል” ማለታቸውን መንግሥታዊ የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ኮሎኔል ጌትነት በመግለጫቸው ላይ የአገሪቱ ሠራዊት ከአማራ ክልል በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልልም ታጥቆ በሚንቀሳቀሰው መንግሥት ሸኔ ብሎ በሚጠራው ኃይል ላይ “የመደምሰስ ሥራ ተጠናክሮ” መቀጠሉን ገልጸዋል።
የመከላከያ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ዛሬ ከሰዓት በሰጡት መግለጫ በአማራ ክልል በመሬት ላይ ካለው ግጭት የገዘፈ የሚዲያ ትግል ተከፍቷል ስለማለታቸው ተዘግቧል።
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የክልሉ እና የፌደራል መንግሥቱ የፀጥታ ኃይሎች ኢመደበኛ ባሏቸው ታጣቂ ቡድኖች ሕግን የማስከበር እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸው ባለፉት ወራት ሲነገር የቆየ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ፋኖ የተባለውን ታጣቂ ቡድን ትጥቅ ለማስፈታት መንግሥት የከፈተው እንቅስቃሴ ነው ይላሉ።
በዚህም ሳቢያ ባለፉት ወራት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰላማዊ ሰዎች፣ ታጣቂዎች እና የፀጥታ ኃይሎች ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱ የተዘገበ ቢሆንም፣ ከፌደራሉ መንግሥትም መሆነ ከክልሉ አስተዳደር በይፋ የተሰጠ አሃዝ የለም።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሚያዝያ ወር ማብቂያ ላይ አውጥቶት በነበረው መግለጫ ላይ በአማራ ክልል በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ውስጥ በመከላከያ ሠራዊት እና በታጣቂዎች መካከል ግጭት መኖሩን እና በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል።
ኮሚሽኑ መንግሥት በአማራ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች እያካሄደ ባለው “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” በሰሜን ጎንደር፣ በሰሜን ወሎ እና በሰሜን ሸዋ ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎች በመከላከያ ሠራዊት እና በታጣቂዎች መካከል “በከባድ መሣሪያ ጭምር የታገዘ” ግጭት መካሄዱን መልክቷል።
ባለፉት ወራትም ግጭቱ ቀጥሎ በተለያዩ አካባቢዎች ያጋጠመ ሲሆን ባለፈው ሳምንት በጎንደር፣ በወልዲያ እና በሸዋ ሮቢት ተመሳሳይ ሁኔታዎች እንደነበሩ ቢቢሲ ከአካባቢው ነዋሪዎች መረዳት ችሏል።
በዚህም ሳቢያ በተለያዩ ቦታዎች መደበኛ የትራንስፖርት እና የሥራ እንቅስቃሴዎች መስተጓጎል አጋጥሟቸው እንደነበር እና አሁን ስጋት እንዳለ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እናዳለ ከአማራ ክልል ከሁሉም ዞኖች የተወጣጡ የሃይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች በወቅታዊ ሁኔታዎች እንዲሁም በሠላም እና በፀጥታ ጉዳይ ላይ በክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር ስብሰባ መቀመጣቸው ተዘግቧል።