ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፊንላንድ ለሕፃናት የሚሆን ምቹ አልጋ በነጻ የምትሰጠው ለምንድነው?
ሱኪታ እና ባሏ ፕራሳድ ወደ ፊንላድን ሲመጡ መጀመሪያ የተሰጣቸው በካርቶን የታሸገ አልጋ ነው።
“እንዲሁ ሳጥን አልነበረም። ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሚባሉ ቁሳቁሶችን የያዘ ነው” ትላለች ሱኪታ። ለመጀመሪያ ጊዜ ካርቶኑን ስትከፍት የነበራትን ልዩ ስሜት አትረሳውም።
ጥንዶቹ ከስድስት ዓመታት በፊት ከሲንጋፖር ወደ ፊንላንድ ሲመጡ የመጀመሪያ ልጃቸውን እየተጠባበቁ ነበር።
መንግሥት የሰጣቸው አልጋ ሙቀት የሚሰጡ ልብሶች፣ ብርድ ልብስ እና ፍራሽ አለው። እናቶች የትኛውም ዓይነት የኑሮ ደረጃ ላይ ቢሆኑ እኩል ልጆቻቸውን እንዲያሳድጉ ለማበረታት የሚሰጥ ነው።
ይህ ብቻ አይደለም። ሱኪታ ከጤና ባለሙያ ምክር ተለግሷታል። ልጇ ገና የሁለት ሳምንት ጨቅላ ሳለች ውጭው አጥንት የሚበሳ ብርድ ነበር።
ነገር ግን አባቷ ፕራሳድ ልጁን በብርድ ልብስ ሸፋፍኖ በረንዳ ላይ ተቀምጦ ሙቀት ይሰጣታል። ይህ በፊንላንድ እና ብርዳማ በሆኑት በአካባቢው ሀገራት የተለመደ ነው።
ፕራሳድ ኢንጂነር ነው። ሱኪታ ደግሞ የስፖርት ፊዚዮቴራፒ ባለሙያ ናት። ስሪ ላንካዊያኑ ከሚኖሩበት ሲንጋፖር ነው የመጡት።
ጥሩ እንቅልፍ እንዴት ያለ ነው?
ሙያተኞች ጥሩ እንቅልፍ ማግኘት ለሕፃናት የአእምሮ ጤና፣ አካላዊ፣ ማኅበረሰባዊ እና የስሜት ዕድገት ወሳኝ ነው ይላሉ።
በዓለም ዙሪያ በርካታ ወላጆች ልጆቻችን በቂ እንቅልፍ እያገኙ አይደለም የሚል ስጋት ላይ ናቸው። ለዚህ ደግሞ ቁጥር አንድ ተጠያቂ እየሆነ የመጣው የሞባይል ስልክ መጠቀም ነው።
በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የእንቅልፍ ትምህርት ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ዳግማራ ዲሚትሩ እንቅልፍ ብዛቱ ብቻ ሳይሆን ጥራቱም ሊያሳስበን ይገባል ይላሉ። “እንቅልፍ ማለት እንደ ተመጣጠነ ምግብ ማለት ነው። ጥራቱም በጣም ወሳኝ ነው” ይላሉ ምሑሯ።
አክለው ጥራት የሌለው እንቅልፍ የሕፃናትን ትምህርት የመቀበል አቅም እና የአእምሮ ጤና ሊያዳክም እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።
የሕፃናት ማቆያ መምህርት የሆነችው ማሊካ ማካዳም በዚህ ትስማማለች። የተዛባ የእንቅልፍ ዑደት ያላቸው ሕፃናት ትምህርት ላይ እንደሚቸገሩ ታዝባለች።
“እኔ እንደማየው ጥሩ እንቅልፍ ያላገኙ ልጆች ትኩረት ያንሳቸዋል፤ ይነጫነጫሉ” ትላለች።
ፕሮፌሰር ዲሚትሩ በበኩላቸው ሕፃናት “ረባሾች” ናቸው በሚል የእንቅልፍ እጦት ችግራቸው ሳይፈታ እንዳያልፍ ያስጠነቅቃሉ።
“ባሕርያቸው ተበላሽቶ አይደለም። እንቅልፍ ማጣት ነው የሚያነጫንጫቸው” ሲሉ ያስረዳሉ።
“አንዳንድ ጊዜ ሕፃናት ተጨማሪ ትምህርት ይሰጣቸዋል፤ አስጠኚ ይቀጠርላቸዋል፤ ስክሪን ላይ ያፈጣሉ። እኔ ግን ሁሌም እንደምለው አስጠኚያቸው መሆን ያለበት እንቅልፍ ነው። በቂ እንቅልፍ እንዲያገኙ ይሁን። ትምህርት አቀባበልን ማስተካከል ይቻላል።”
በቂ ያልሆነ እንቅልፍ እና አሉታዊ ጎኑ
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት እንቅልፍ ማጣት ለአካላዊ ጉዳትም ሊያጋልጥ ይችላል። ለምሳሌ ለደም ግፊት፣ ከመጠን በላይ ውፍረት እና ለልብ ሕመም ምክንያት የመሆን አቅም አለው።
የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) በርሚንግሀም ዩኒቨርሲቲ ጥናት እንደሚያሳየው ከጨቅላ ዕድሜያቸው ጀምሮ በተደጋጋሚ የእንቅልፍ እጦት የሚያጋጥማቸው ሕፃናት ሲያድጉ የአእምሮ ሕመም ሊገጥማቸው ይችላል። ሳይንቲስቶች የእንቅልፍ እጦት አእምሮ ዕድገት ላይ አሉታዊ ጉዳት እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
ሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ ያስደረገውም ጥናት ይህን ነው የሚያሳየው። በቂ ያልሆነ እንቅልፍ ሕፃናት አእምሮ ጤንነት ላይ ጉዳት ያስከትላል።
አጥኚዎቹ እንደሚሉት በቂ እንቅልፍ የሚያገኙ ሕፃናት በቂ እንቅልፍ ከሚያገኙት ሲነፃፀሩ የአአምሮ እና የባሕርይ ችግር ይስተዋልባቸዋል።
ባለሙያዎቹ አክለው እንደሚሉት በቂ እንቅልፍ አለማግኘት ሕፃናት ባሕርያቸውን ከመቀየሩም በላይ የምግብ ምርጫቸውንም ያውከዋል።
እንቅልፍ እና ቴክኖሎጂ
ፕሮፌርሰር ዲሚትሩ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ሕፃናት በቂ እንቅልፍ እንዳያገኙ እያደረገ ነው ይላሉ። ወላጆች ልጆቻቸው በተለይ ከእንቅልፍ በፊት የሚጠቀሙትን ስክሪን እንዲቆጣጠሩ ይመክራሉ።
ነገር ግን ቴክኖሎጂ ብዙም ዘልቆ ባልገባባቸው ክፍለ ዓለማት ይህ ችግር የለም።
ፕራሳድ እና ሱኪታ ሁለቱ ሴት ልጆቻቸው በቀን ቢያንስ 10 እንቅልፍ እንዲያገኙ ያደርጋሉ። የስክሪን ሰዓታቸውንም ይገድባሉ።
ስሪ ላንካ እና ሲንጋፖር የኖሩት ጥንዶቹ ከፊንላንድ በላቀ ሕፃናት ስክሪን ላይ ረጅም ጊዜ እንደሚያጠፉ አስተውለዋል።
“ባደግኩበት ስሪ ላንካ እንቅልፍ የምተኛው ቴሌቪዥን እያየሁ ነው” ትላለች ሱኪታ።
አሁን ልጆቻቸውን ለማስተኛት ከ30 ደቂቃ እስከ 1 ሰዓት የተለያዩ ተግባራት ይፈፅማሉ። ለምሳሌ መፅሐፍ እንዲያነቡ ማድረግ አሊያም ለልጆቹ መፅሐፍ ማንበብ።
ሕፃናቱ ከመተኛታቸው በፊት በነጋታው የሚለብሱትን ልብስ ያዘጋጃሉ፤ ጥርሳቸውን ይቦርሻሉ። አልጋቸው ላይ ከወጡ በኋላ ምግብ መጠየቅ ክልክል ነው።
የባሕል ተፅዕኖ
እንቅልፍ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ፍላጎት ነው። ነገር ግን ባሕልም የእንቅልፍ ዑደት ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል።
ለምሳሌ በረመዳን ጾም ወቅት ሕዝበ ሙስሊሙ ቀኑን ሙሉ ይጾማል። ይህ ምናልባት የእንቅልፍ ዑደትን ሊያዛባ ይችላል።
ነገር ግን እንደ ሳዑዲ አረቢያ ባሉ ሀገራት በዚህ ወቅት ሕፃናት ፈተና አይሰጣቸውም። ይህ ሊበረታታ ይገባል ይላሉ ፕሮፌሰር ዲሚትሩ።
በምሥራቅ እስያ ባሉት ሀገራት ደግሞ ጠንክሮ መሥራት ባሕል ነው። ሕፃናት በርካታ የቤት ሥራ ተሰጥቷቸው ሌሊቱን ሙሉ እያጠኑ ሊያደሩ ይችላሉ። ይህ የአእምሮ ዕድገት ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ሙያተኞች ያስጠነቅቃሉ።
ፕራሳድ እና ሱኪታ አሁንም ከጤና ባለሙያዎች ምክር ይጠይቃሉ። ገና ተምረን አልጨረስንም ይላሉ።
ፕሮፌሰሯ ለሕፃናትም ሆነ ለወላጆች ምክር አላቸው።
“ሁሌም እንደምለው ምንም ይሁን ምን በቂ እንቅልፍ ማግኘት ተገቢ ነው። ጥቅሙን ልንረዳው ይገባል። በቂ ምግብ እና በቂ እንቅልፍ ማግኘት አለብን። እኒህ ሁለቱ ነገሮች በሕይወታችን እጅግ ወሳኝ ናቸው።”